>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1239

ሸገርን በጨረፍታ፤ ተወልጄ ያደኩባት ከተማስ የማን ነች? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሸገርን በጨረፍታ፤ ተወልጄ ያደኩባት ከተማስ የማን ነች?
ያሬድ ሀይለማርያም
ተወልጄ ያደኩባትን ከተማ – ሸገርን ከ13 ዓመት ተኩል በኋላ ዳግም ለማየት እድሉ ገጠመኝ። ይሁንና የነበረኝ ቆይታ ከሁለት ሳምንት ያልዘለለና እሱም በሥራ እና በተለያዩ ስብሰባዎች የተሞላ ስለነበር የከተማዋን ሙሉ ገጽታ ለመቃኘት እድል፣ የቆዩ ወዳጆቼን ለማግኘትና የሆድ የሆዳችንን ለመጨዋወት፣ ከዘመድ አዝማድ ጋር ናፍቆቴን ለመወጣት እድል አላገኘሁም። በቆየሁባቸው ጥቂት ቀናት ግን ብዙ ነገሮችን ከላይ ከላዩ ለመታዘብ ችያለሁ። ያገኘሁት ሰው ሁሉ ‘አዲስ አበባን እንዴት አገኘሃት?’ የሚል ጥያቄ ያቀርብልኝ ስለነበር እንዴት እንዳገኘኋት ባጭሩ ላካፍላችሁ።
ከተማዋ የማን ነች?
አዲስ አበባ የሁላችንም ነች። አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን ነች። አዲስ አበባ እኔ ተወልጄ እንብርቴ የተቀበረባትም ሆንኩ ከየትኛውም የአገሪቱ ጥግ የሚመጣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ገበና ሸፋኝ፤ እናት ከተማ ነች። ማንም በአዲስ አበባ ላይ ያነሰ ወይም ከፍ ያለ መብት እና ጥቅም የለውም፤ ሊኖረውም አይገባም። ከሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት የተመመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የኑሮ ምህለቁን የሚጥለው ሸገር ላይ ነው። ያ ደግሞ አዲስ አበባን ልዩ ከተማ አድርጓታል። አዲስ አበባ ለሌሎች ከተሞች መቆርቆዝ እና አገሪቱ አማራጭ የሆኑ እና በእድገታቸው ተቀራራቢ የሆኑ ሌሎች ከተሞች እንዳይኖሩ አድርጋለች። በዚህም የተነሳ ከአራቱም አቅጣጫ ዜጎች ህልማቸውን እውን ሊያደርጉ የሚተሙት እና የሚከትሙት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን አድርጓል።
ብዙዎች የተወለዱበትን ሥፍራ እና አካባቢ እያቆረቆዙ ያፈሩትን ሃብት ሁሉ የሚያከማቹት በዚችው መዲና ነው። አዲስ አበባ የቀሩት የአገሪት ከተሞች ሁሉ እዳ አለባት። አዲስ አበባ ዛሬ ያለችበት ደረጃ ላይ የደረሰችው እና የአገሪቱ የሃብት ክምችት የተቆለለባት በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ኪሳራ ነው። ኢትዮጵያ ሌሎች ሰፋፊ እና አዲስ አበባን ሊገዳደሩ የሚችሉ ከተሞች የሏትም። አንዳንድ እንደ ባህርዳር፣ መቀሌ አና አዋሳን የመሳሰሉ ከተሞች አንገታቸውን ቀና ማድረግ ቢጀምሩም ከሸገር ተርታ ለመቆም ብዙ አመታት መጓዝ ይኖርባቸዋል።
አዲስ አበባ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንብርት፣ የፖለቲካ መዘወሪያ ከመሆኗም አልፎ የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት መዲና መሆኗ ደግሞ አቅሟን እጅግ አጎልብቶታል። እነዚህን እድሎች ለመጠቀም እና ሃብት ለማፍራት ዜጎች ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተመው ጎጇቸውን ከሸገር ቀልሰዋል። አዲስ አበባንም አዲስ አበባ ያሰኟት እነዚህ ያለ ምንም ስስት ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ሃብታቸውን እና ጊዜያቸውን የለገሷት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለተወለደበት ሥፍራ ይህን ያህል ቢደክም ኖሮ ብዙ አዲስ አበቦች ይኖሩን ነበር። ለትውልድ ቅዮው ንፉግ የሆነ ሁሉ ጀርባውን ለተወለደበት ሥፍራ እየሰጠና ዳግም አይመልሰኝ እያለ በሸገር ፍቅር ተለክፎኗ በንዋይዋም ተማሎ የልጅ ልጅ እያፈራ የከተመባት ጉደኛ ከተማ ነች።
ዛሬ አዲስ አበባን ማንም የራሱ ሊያደርጋት አይችልም። አዲስ አበባን የጸብ አውድማ ለማድረግ የሚደረገው ፉከራም ሆነ የፖለቲካ ግብግብ ለማንም አይበጅም። ማንም በዚህ አትራፊ ሊሆን አይችልም። አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነት ቋጠሮ እንዳይበተን ሆኖ የተገመደባት ሚስጥር የሆንቸ ከተማ ነች። የከተማዋን ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከሚገመተው በላይ የተሰናሰነውን የሕዝቧን ባህል፣ ባህሪይ እና ስነ ልቦና ያልተረዳ ሰው ብቻ ነው አዲስ አበባን የእኔ ብቻ ወይም የዚህ ዘር ብቻ ወይም የዚህ ክልል ብቻ ወይም የአዲስ አበቤዎች ብቻ ነች የሚለው። አዲስ አበባ ስትነካ ንዝረቱ ከሸገር ጋምቤላ፣ ኦጋዴን፣ ሃረር፣ ድሬዳዋ፣ አርባ ምንጭ፣ አገረ ማርያም፣ ባሌ፣ መተማ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አክሱም፣ መተከል ሁሉም ጋር ይደርሳል።
ስለዚህ አዲስ አበባን የማን ናት ብሎ መጠየቅም ሆነ ሙግት መግጠም ቂልነት ይመስለኛል። አዲስ አበባ የማንም የግል ሃብት አደለችም። የአዲስ አበቤዎችም አይደለችም። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች። አዲስ አበባን ለኢትዮጵያ እንተዋት።
ሸገር ምን መስላለች?
እኔ ከአስራ ሦስት አመት በፊት የማቃት አዲስ በብዙ መልኩ ተቀያይራለች። ወደጎን ተለጥጣ ከአንድ ጫፍ ሌላ ጫፍ ለመድረስ ወሎ ገብ ጉዞ ነው። እርቀቱ ብቻ ሳይሆን መንገዱን የሚያረዝመው ውጥንቅጣቸው የወጣው የከተማዋ መንገዶች፣ የተሽከርካሪው ብዛት፣ የእግረኛው እና መኪናዎች አብረው በአንድ መንገደ እኩል እየተጋፉ መትመም፣ እና ሌሎች በርካታ መንገድ አሰናካይ ነገሮች ተደማምረው በከተማዋ ውስጥ ከአንድ ሥርፍራ ወደ ሌላ ለመንቀሳቀስ የሚደረገውን ጉዞ የእንፉቅቅ አድርጎታል። በከተማዋ ቀላል ባቡር የመሳፈር እድል ስላልገጠመኝ ጉዞውን በማቅለል እረገድ ያላትን ሚና ለማየት አልቻልኩም።
አዲስ በሁሉም አቅጣጫ ተለጥጣለች። አዳዲስና ሰፋፊ የመኖሪያ መንደሮች ተመስርተዋል። የብዙዎቹን መኖሪያ መንደሮች ስም ደጋግሜ የሰማዋቸው ቢሆኑም ከአንድ ከሁለቱ በስተቀር ብዙዎችን ለማስታወስ እቸገራለሁ። መግሥት ባለፉት አሥርት አመታት ከሰራቸው መልካም ነገሮች አንዱ የመኖሪያ ቤቶችን ለማስፋፋት እና በወዳደቁ የአፈር እና የቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የሸገር ነዋሪዎችን ወደ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲገቡ ማድረጉ ነው። እነዚህ የኮንደሚኒየም ቤቶች ከጥራት አንስቶ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሳባቸው ቢችልም ከእነዛ ዘመናት ካስቆጠሩ እና በመፍረስ ላይ ከነበሩ የአፈር እና የቆርቆሮ ቤቶች በብዙ እጥፍ የተሻሉ እና የነዋሪውንም የኑሮ ዘይቤ የቀየሩ በመሆናቸው እሰየው የሚያስብል ነው።
በተቃራኒው የከተማዋን መስፋት እና የነዋሪዎቿን የተሻለ የመኖሪያ ቤት ማግኘት በጎ ነገር ቢሆንም በሌሎች ዜጎች ኪሳራና ጉዳት ላይ የተንሰራፋች ከተማ መሆኗ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፤ ያማልም። ዛሬ በመሃል የከተማዋ ግዛትም ሆን በአዳዲስ የተመሰረቱ መንደሮች ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ ደሃ የህብረተሰቡ ክፍሎች የት እንደደረሱ ማየት ተገቢ ነው። ብዙዎች የከተማዋ ሕንጻዎች የተሰሩባቸው ስፍራዎች ላይ ይኖሩ የነበሩ በብዙ ሺዎች የሚቆየሩ ድሃዎች ተገቢው የኑሮ ዋስትና ተሰቷቸዋል ወይ የሚለው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው። ለአንድ ባለሃብት ንብረት ለሚሆን ህንጻ በሺዎች ዜጎችን ያፈናቅል የነበረው አይን ያወጣ የመሬት ንጥቂያ ፖሊሲ ብዙዎችን ለጎዳና ላይ ህይወት ዳርጓል።
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የነበሩ ገበሬዎች ያለ በቂ የኑሮ ዋስትና መሬታቸው እየተነጠቀ ለዘመኑ ባለሃብቶች ታድሏል። ብዙዎቹ አዳዲስ የመኖሪያ ሥርራዎች የተገነቡት በነዚህ ደሃ ገበሬዎች ኪሳራ ነው። ይህ አይነቱ ጤና የጎደለው የመንግስት ልማት ፖሊሲ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አርሷደሮችን አፈናቅሏል፤ የኑሮ ዋስትናም አሳጥቷል። በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሷደሮች በዚህ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ የመንግስት የከተማ ማስፋፋት ፖሊስ ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሆነዋል።
ይህ በዙሺዎችን የኑሮ ዋስትና እያሳጣ እና ጥቂቶችን እያደላደለ የመጣው የተንጋደደ የልማት ፖሊሲ አዲስ አበባን የስጋት ከተማም እንድትሆን አድርጓታል። መሬቴ ተነጠቀ ብሎ ያኮረፈና ከንፈሩን እየነከሰ ቀን የሚጠብቅ የህብረተሰብ ክፍል አለ። መንግስት በሰጠው መሬት ላይ ሰፍሮ፣ ቤት ሰርቶ እና አልምቶም በስጋት እንቅል አጥቶ የሚያድር ሕዝብ አለ። እነዚህን ሁሉት አካላት አንዱን ከድህነት ሌላውን ከስጋት የሚገላግል ዘላቂና አስተማማኝነት ያለው፤ ማህበራዊ ፍትህን ያረጋገጠ የመንግስት አፋጣኝ እርምጃ የግድ ይላል።
አዲስ አበባ የትርምስ ከተማም ሆናለች። የሰዉ እና የተሽከርካሪው ብዛት፣ የአዳዲስ ግንባታዎች እጅግ መበራከት፣ ከቁጥጥር ውጭ የወጣው የትራፊክ ፍሰት፣ የመንገዶች መጣበብ እና ሥርዓት አልበኝነት ከተማዋን ቅጥ አሳጥቷታል። ሌላው የከተማዋ እድገት ጤና የጎደለው መሆኑን ማሳያው ብዙዎቹ የልማት እና የግንባታ ሥራዎች በቂ ጥናት ያልተካሄደባቸው፣ የከተማዋን ዘላቂ ውበት እና ጠናማነት ያላገናዘቡ የዘፈቀደ ሥራዎች መሆናቸው ነው። ነዋሪዎቿ ወጣ ብለው ንጹ አየር ሊቀበሉበት እና ጥላ ሊያገኙ የሚችሉበት ሥፍራ ብዙም አይታይም። የከተማዋ ግራና ቀኝ መንገድ ሁሉ በብሎኬትና ድንጋይ ቁልል ህንጻዎችና አዳዲስ ግንባታዎች ተጨናንቀዋል። ልኮች ከቤታቸው ወጣ ብለው ሊጫወቱ የሚችሉባቸው ስፍራዎች የሉም። ዛፎች አይታዩም። አልፎ አልፎ የሚታዩ ዛፎችም ከየግንባታው ላይ በሚመጣ አቧራና የስሚንቶ ብናኝ ተውጠው ልምላሜን አያሳዩም። ባጭሩ አዲስ አበባ አመድ የወረሳት ከተማ ሆናለች። እርግጥ የእወሰኑ አካባቢዎች ለአይን የሚስቡ ህንጻዎች እና ግራ ቀኙ የጸዳ አካባቢ አለ። ነገር ግን  የከተማዋን ሙሉ ገጽታ አያሳይም።
አማራጭ ከተሞች ለምን የሉንም?
ኢትዮጵያን የምታክል ሰፊ እና ከመቶ ሺ ሕዝብ በላይ የሚኖርባት አገር አማራጭ ከተሞች የሏትም። እነ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ አዋሳ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ናዝሬት እና ሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች አማራጭ ከተሞች የመሆን አቅም ገና አልፈጠሩም። የአገሪቱ ሃብት፣ እውቀት፣ የተማራ የሰው ኃይል፣ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ተቋማት፣ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የውጭ ድርጅቶች እና ቆንስላዎች ተሰባሰው የከተሙት አዲስ ላይ ነው። ከላይ እንደገለጽኩትም ትንሽ ቅሪት ያፈራ የየትኛውም ክልል ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊም የኑሮም ሆነ የኢኮኖሚ መሰረቱን የሚጥለው አዲስ አበባ ነው። ብዙዎች ከየክልሉ ሃብት ሊያፈሩ የመጡባት ሸገር ውስጥ ሁለት ጸጉር አብቅለው፣ የልጅ ልጅ ወልደው እና ሃብታቸውንም እዛው አከማችተው ዘመድ ጥየቃ ካልሆነ በቀር ወደ መጡበት የትውልድ ስፍራቸው አቅጣጫ ፊታቸውን እንኳን አዙረው አይተኙም።
ይህ አይነቱ የመንግስት እና የሕዝብ የከተማ አሰፋፈር አማራጭ እና ተፎካካሪ ከተሞች እንዳይፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ሳቢያ ሁሉም ያለችውን ቋጥሮ ዛሬም የኑሮ ዋስትናውን ሊያረጋግጥ የሚተመው ወደ አዲስ አበባ ነው። ከተማዋም ተለጥጣ ልትፈነዳ አንድ ሃሙስ የቀራት መስላልች። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሰው ፍልሰት ወደ አንድ አቅጣጫ፤ ወደ አዲስ እንደሆነ በከተማዋ ጎዳናዎች የሚታየው የሕዝብ ብዛት እና ጉራማይሌ ቋንቋ በቂ ማሳያ ነው።
መንግስት ፖሊሲ ቀርጾ ሌሎች ቢያንስ ሶስት እና አራት ከተሞችን የማስፋፋት እና የማዘመን ሥራ ካልሰራ ወደፊት አዲስ አበባን ማስተዳደር እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። የአማራጭ ከተሞች መበራከት የሰዉን ፍልሰትም ሆነ የኢኮኖሚ ድልድሉን አገራዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደርገዋል።
ከብዙ በጥቂት አዲስ አበባን እንዲህ አግኝቻታለሁ። እናንተስ?
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic