>

መክዳትስ እንደ ዛዲግ አብርሃ. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

መክዳትስ እንደ ዛዲግ አብርሃ. . . 
አቻምየለህ ታምሩ
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም  የመጀመሪያዎችን  የኤርምያስ ለገሰ ቃለ መጠይቆችና  «የመለስ ትሩፋቶች፡ ባለቤት አልባ ከተማ» እና «የመለስ ልቃቂት» በሚሉ አርዕስቶች ኤርምያስ ለገሰ የጻፋቸውን ድርሳናት ካነበቡ በኋላ  «መክዳትስ  እንደ ኤርምያስ ለገሰ ነው» ብለው ነበር።
ኤርምያስ ለገሰ ወያኔን ከከዳ በኋላ ከወያኔ ጋር በነበረበት ወቅት የሚያውቀውን ሁሉ ሚስጥር  በገሀድ በማውጣት መጋረጃ ቀድዶ የአገዛዙን ገመና  ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየ፣ ወያኔን ያሳመመና  ለጸረ ወያኔው ትግሉም  አስተዋጽኦ ካደረጉ  ኮብላይ የወያኔ ሚንስትሮች መካከል  ቀዳሚው ነው። ከወያኔ ተለየን ያሉን እነ ገብሩ አስራት፣ ስዬ አብርሃ፣  አረጋዊ በርሀ፣ ወዘተ መጽሐፍትን ጽፈዋል። ሆኖም  ግን አንዳቸውም  እኛ የማናውቀን የወያኔ ሚስጥር በጻፏቸው ዳጎሱ ያሉ  መጽሐፍቶች  ውስጥ አልነገሩንም። መጽሐፍ ጽፎ   ወያኔን የሚያሳምም ሀቅና  የማናውቀውን የወያኔ  እውነት ገልጦ ያሳየን ኤርምያስ ለገሰ ብቻ ነው።
ስለ ኤርምያስ ለገሰ ማውሳቴ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም «መክዳትስ እንደ ኤርምያስ ለገሰ ነው» ያሉትን አባባል ዛሬ ከወያኔ  ለኮበለለው ለዛዲግ አብርሃ ለመጠቀም ፈልጌ ነው።  ፋሽስት ወያኔን እስኪያልበው  ድረስ ያገለገለው ዛዲግ አብርሃ ዛሬ ለድርጅቱ ባቀረበው የመልቀቂያ ወረቀት  ማገባደጃ ላይ ፋሽስት ወያኔ በወረራ ስለያዘው የአማራ ምድር  በመሰከረበት የመልቀቂያ ጽሁፉ  ፋሽስት ወያኔን አጥንቱ ድረስ የሚያሳምም  መናኛ ጉዳይ   አንስቷል።
እነ ገብሩ አስራት፣ ስዬ አብርሀ፣ ወዘተ ከወያኔ ተለይተዋል።  እነሱ ከወያኔ መለየታቸው ግን ወያኔን አላሳመመውም።   ወያኔ በዛዲግ መኮብለል የሚታመመው ዛዲግ ወያኔን በመካዱ ሳይሆን  ዛዲግ ወያኔን ለከዳበት  ባቀረበው ምክንያት ነው። ዛዲግ ለወያኔ ባስገባው መልቀቂያ መመደምደሚያ  ላይ እንዲህ ብሏል. . .
«የራያ ሕዝብ በተድላና በፍቅር ከወሎ አማራና ከመላው የአማራ ሕዝብ ጋር ለዘላለሙ ይኖራል»
ይህ እውነተኛነት ከከዱ አይቀር እንደዛዲግ የሚያስብል ነው። የዛዲግ መሰሎች ከከዳችሁ  አይቀር «መክዳትን እንደ እገለ ነው»  እንድንልላችሁ አድርጋችሁ ወያኔን አጥንቱ ድረስ የሚሰብር እውነት ይዛችሁ በመውጣት የሰላም እንቅልፍ  እንድትተኙ ሁናችሁ ኮብልሉ። እንደ ገብሩ አስራትና ስዬ አብርሃ  ከድርጅቱ ተለይተናል ብላችሁ አልሸሹም ዘወር አሉ  በመሆን የየወያኔን  ደዌና ጭነት  ተሸክማችሁ ያንን በአዲስ መልክ ለማስተጋባት ወደ ሕዝብ ብትቀላቀሉ  ያው የጠፋው በግን ናችሁ፤ አንዳች  የምትረቡት  ነገር የለም።
Filed in: Amharic