>

....የኢህአዴግ ፋንታሲ የሞተው - መለስ የሞተ ዕለት ነው!! (አሰፋ ሀይሉ)

የቀ.ኃ.ሥ ሞናርኪ የሞተው -ጥላሁን ግዛው የሞተ ዕለት ነው!!
የኢህአዴግ ፋንታሲ የሞተው – መለስ የሞተ ዕለት ነው!!
ሰፋ ሀይሉ
ነገር አላበዛም። ባጭሩ ያሰብኩትን እውነት እናገራለሁ። ለጓደኝነት ምሥጢር ስል አሁን ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ጓደኛዬ የ97ን ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በቅንጅትና በኢህአዴግ መሐል ሲደረግ በነበረው ድርድር ላይ ከቅንጅት ወገን ሆኖ ተሣትፏል። ብዙዎች እስካሁንም ድረስ ስሙን በውል ከማያውቁት የወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲ ከኢዲሊ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሊግ?) ከእነ አቶ መለስና አቶ በረከት ጋር ግንባር ለግንባር ተፋጥጧል። ከእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጎን ተሰልፎ ሃሳብን አንግቦ ተከራክሯል።
ያ ጓደኛዬ ያኔ በተገኙበት ይታሠሩ ተብሎ ፎቷቸው በቲቪ ሲተዋወቅ አብረን ምሣ እየበላን ነበር። በገዛ ሀገሩ ምን ዓይነት ስሜት እንደተሰማው በፊቱ ላይ ያየሁትን ነገር፣ በልቤ ውስጥ የተሰማኝን የዐቅመ-ቢስነት ስሜት መቼም እስክሞት ድረስ አልረሳውም። ታናሽ እህቱን ከትውልድ ሀገሩ ሊያስተምር አምጥቷል። ደራሲ ወንድም አለው። ጥሩ የባንክ ደመወዝ ይከፈለዋል። ግን ሀገሬን አለ። ሀገር ሱስ ነው። ምን ታረገዋለህ??!!
የመጣው ይምጣ ብዬ ያን ጓደኛዬን እኔ ቤት ኑር፣ እኔ እየሠራሁ አንተ ቤቴ ተደብቀህ እንኖራለን፣ ችግር የለም! ብዬው ነበረ። ላስብበት አለኝ። ፎቶው በቴሌቪዥን እየተሠራጨ ነው። የመ/ቤት አለቆቼ የለየላቸው ህወሃቶች (ኢህአዴጎች) (ግን መልካምም ሰዎች!) ናቸው። በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ጓደኛዬን በቤቴ ማስጠለል ግን ልከፍለው ከሚገባኝ የአደጋ (“ሪስክ”) ዋጋ በጣም ትንሹ ነው ብዬ አስቤ ነበረ። በወቅቱ። ያኔውኑ።
ያ ጓደኛዬ ግን ላስብበት ካለኝ በኋላ በገዛ ሀገርህ እስከመቼ ተሸሽገህ ትዘልቀዋለህ? በቃ ለፌዴራል ፖሊስ እጄን ልሰጥ ነው አለኝ። በስልክ። ተከራከርኩት። በሀሳቡ ፀና። ስልኬን ዘግቼ አለቀስኩ። የዚያኑ ዕለት ወፍራም ደመወዝ ለሚከፍለኝ (እና ምንም ላላጎደለብኝ!) ባንክ ቤት የሥራ መልቀቂያዬን አቀረብኩ። በ2 ወሩ ለቀቅኩኝ። እኔ ከሥራዬ ነው የለቀቅኩት። ሲንግል ለቀቀ ያሉኝም ወዳጆቼና የሩቆቼም ነበሩ። ጓደኛዬም እጁን ሰጠ። እና ታሠረ። ማዕከላዊ ስሜን እያስመዘገብኩ በሄድኩ ቁጥር “እዚህ የለም!” ነበረ መልሱ።
አንድ ቀን ላይ የሆነ ሌላ ጓደኛችን መጣና ያ ታሳሪው ጓደኛህ ተቀይሞሀል ወያኔን ፈርተህ ወህኒ (እስር-ቤት) ስላልጠየቅከው አለኝ። እኔ ደሞ ምን አልኩት? – ይቀየመኝ፤ መብቱ ነው፤ እኔና እግዜር ብቻ ነን እውነቱን የምናውቀው! ብዬ መለስኩለት። እውነቴን ነው። እውነትም ነው። የሚያሳዝነው ነገር ግን ያ የቅያሜ ነገር እውነት ሣይሆን ያለመቅረቱ ነው። አሁን ያ ጓደኛዬ በውጭ ሀገር ነው ያለው። እግዚአብሔር ይመስገን አግብቷል፣ ወልዷል፣ ከብዷል። አልፎ አልፎ በመሴጅ እንገናኛለን። ቆይቷል ከተገናኘን ለመጨረሻ ጊዜ።
አሁን ያን ጓደኛዬን ያነሣሁት ለምንድነው??? 
 
አዎ። ያን ጓደኛዬን ያነሣሁት በምክንያት ነው:-
አንድ ቀን ከነ አቶ መለስ ጋር ተከራክረው (“ተደራድረው!”) እየተመለሱ ነበር። አምባሣደር ቴያትር ጎን ያለ ካፌ ውስጥ ጓደኛዬን አገኘሁት። መንፈሱ ዝሏል። ሁለመናው በግኗል። እና በጨዋታችን መሐል ምን አለኝ?! ፦ “የሚገርምህ ነገር… ከመለስ በላይ እኮ ነገር እየበጠበጠ ያስቸገረን ማን መሠለህ? … ይሄ በረከት የሚሉት ‘ጭር-ሲል-አልወድም’ ሰውዬ!!!” ነበር ያለኝ። አሁን ያ ‘ጭር-ሲል-አልወድም’ የት እንዳለ – ጓደኛዬ የት እንዳለ ስመለከት – ሌላ አይደለም – እግዚአብሔር ብዙም ሩቅ እንዳልሆነ ነው የምገነዘበው። አምላክማ ታገሠ እንጂ አልራቀም። ጨክኖ አልጨከነምም።
ያ የድሮ የልብ ጓደኛዬ ከመታሠሩ በፊት ነው። ከአቶ መለስ ጋር ለተከታታይ ቀናት ሙግት ላይ ነበር የሰነበተው። ሁለመናው ዝሎበት ነው የማገኘው። እና አንዱ የቁዘማ ቀን ላይ ግን እንዲህ አለኝ። ያለኝን የምናገረው በእግዚአብሔር ሥር ሆኜ ነው። ከዋሸሁ አይደለም። ከተሣሣትኩ ራሱ እንዲቀስፈኝ። እግዚአብሔርን ከላዬ ጭኜ። እውነትን። የእውነትን ሁሉ ምንጭ ከበላዬ አድርጌ።
እና ያ ከእነ አቶ መለስ ጋር ሲሟገት ውሎ ዝሎ የሚመለስ ጓደኛዬ ከምድር ጦር ግቢ ፊት ለፊት – ከአምባሣደር ቴአትር አስፋልት ባሻገር – ምንድን ነበር ያለኝ? – ያለኝማ እንዲህ ነው። ቃል በቃል። በደከመ (እና ተስፋ የቆረጠ በሚመስል አነጋገር!) ፦
“ታውቃለህ? ከዚህ ሰውዬ [ከአቶ መለስ] ጋር እየተደራደርን፣ እየተከራከርን፣ እየተወያየን፣… ምን የሚል ሃሳብ በዓዕምሮዬ እንደሚመጣብኝ ታውቃለህ?… በቃ.. ይሄ ሰውዬ በህይወት እያለ.. መቼም ቢሆን የኢህአዴግ ሥርዓት አይወድቅም! እንዴት እንደሚገለባበጥ ብታየው!? እንዴት ዓይነት አሣማኝ ነገር መዞ ራስህ ባነሣኸው ነገር ተንተርሶ እንደሚገባብህ ብታይ.. በቃ.. ታውቃለህ?! ! መቼም ቢሆን.. ይሄ ሰውዬ በህይወት እያለ ወያኔ-ኢህአዴግ እንደማይወድቅ… በቃ ዛሬ አምኜ ተቀብዬአለሁ። በቃ። እሱ እያለው ወያኔ ዕድሜ ልካችንን እንደሚገዛን አትጠራጠር። ይሄ ሰውዬ እስካለ ሁሉን ነገር “ጀስቲፋይ” እያረጉ ይቀጥላሉ። እሱ በህይወት እያለ ለውጥ ይመጣል ብለህ አታስብ። በበኩሌ ተስፋ ቆርጬያለሁ!!!!!!
እንዲህ ነበር ያለኝ። የልብ ጓደኛዬ:-
ፈርዶብኝ ልበ ሰፊ አርጎ ፈጥሮኛል። የኢህአዴግ አኦርታ የሆኑ ጓደኞችም ነበሩኝ። የአንዱን ለአንዱ አስተላልፌ አላውቅም። ኮንዳክተር አይደለሁም። ኢንሱሌተር ነኝ። እነዚህ ባላንጣ ጓደኞቼ ባንድ ጠረጴዛ ቢቀመጡ ምናልባት አንገት ላንገት ይተናነቃሉ። እኔ ይኸው ሕዝበ አዳምንና ሕዝበ ሠይጣንን ልታስታርቅ እንደተነሳች እንደ ክርሥቶስ ሣምራ.. ሁሉን ላስማማ እየዋተትኩ.. ይኸው የኢትዮጵያዬ አምላክ ይመስገን.. ይኸው እንዳለሁ አለሁ!!!
አሁን ይሄን የዶ/ር አብይን ነገረሥራ ሳስተውለው.. የእኔ ቢጤ ይመስለኛል። ሸክሙ ይሰማኛል። ፈጣሪ ይርዳው እላለሁ።
እምዬ ኢትዮጵያን ለነገ ያሻግራት። እኛን ሁላችንንም ሳይለየን የነገ ሰው ይበለን። ይቅር ለእግዜርን በልቦናችን ያሳድር። ለአሁን ህፃናት፤ ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶቻችን ፍቅርና ኅብረት የምንጨነቅ፣ የምንጠበብ ዜጎች ያድርገን። ሁላችንንም። አንዳችንንም ሳይለይ። ፈጣሪ። አምላክ። የኢትዮጵያዬ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ ይባርክ!
እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
አበቃሁ።
Filed in: Amharic