>

ይድረስ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ   (ስዩም ተሾመ)

ይድረስ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ 
ስዩም ተሾመ
ይህ መልዕክቴ እንዲደርስዎ በቀና መንፈስ እንዲያዩትም በትህትና እጠይቃለሁ። አራት ኪሎ እሪ በከንቱ መጠጊያ የሌላቸው እናቶች ህፃናቶቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ ወድቀዋል። ህፃናቱን እና የእናቶችን እንባ በዚህ ሁኔታ ማየት ልብ ያደማል እረፍት ይነሳል። በእርስዎ አስተዳደር ስር ያሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እነዚህን ምስኪን መጠጊያ የሌላቸው ድሆች ህገወጥ ናችሁ በማለት መጠለያቸውን ድምጥማጡን አጥፍተው በዚህ ሁኔታ ለስቃይና እንግልት ዳርገዋቸዋል።
እርስዎ በዶክተር አብይ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው ከመሾምዎ በፊት ኪራይ ቤቶች አስተዳደር በሰጠዎት ቤት ይኖሩ እንደነበረ አውቃለሁ። ስልጣን በተሰጥዎ ማግስት ግን ያ ባለ ሶስት መኝታ አፓርታማ ለክብርዎ አይመጥንም በማለት ከመንግስት ካዝና ከነዚሁ ዛሬ እያነቡ ጎዳና ከወደቁ እናቶች በታክስ ከተሰበሰበ ገንዘብ በወር 140 ሺህ ብር ገደማ ኪራይ ወደሚከፈልበት ክብርዎን ይመጥናል ወደተባለ ቤት መዘዋወርዎም ይታወቃል።
ይህም በራሱ በቂ ሆኖ አልተገኘምና ሳር ቤት የሚገኘው የጀነራል አደም መኖሪያ የነበረው ግዙፍ ቪላ ቤት በከፍተኛ ወጪ እድስት ተደርጎ እየተዘጋጀልዎ እንደሆነም በሚገባ አውቃለሁ። የተከበሩ ከንቲባ ኢትዬጵያ አቅም ኗሯት ከዚህም በላይ ብታደርግልዎ ባልከፋኝ ነበር። ነገር ግን እርስዎ በዚህ ደረጃ ሲከበሩ ህፃናት በገዛ አገራቸው በእርስዎ አስተዳደር ህገወጥ ተብለው ሜዳ ላይ ሲወድቁ ማየት ግን እውነት እልዎታለሁ የግፍ ሁሉ ግፍ ነውና ስለፈጠርዎ እነዚህን ህፃናት ይታደጓቸው።
 
ም/ከ ታከለ_ኡማ በሁለት ወር ውስጥ ለ27_አመት የሚበቃ የቤት_ኪራይ ከፍለዋል 
የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ የመኖሪያ ቤት ወራዊ ኪራይ 140ሺህ ብር ነው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በተገኘ የሰነድ ማስረጃ መሰረት ለም/ከንቲባው የሚከፈለው ወራዊ የቤት ኪራይ 860 ብር ብቻ እንደሆነ ተገልጿል። ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው ላለፉት ሶስት ወራት የተከፈለውን የቤት ኪራይ ነው። ይህ ግን “ም/ከንቲባው በወር 140ሺህ ብር ኪራይ በሚከፈልበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ኖረዋል” የሚለውን መረጃ ስህተት አያደርገውም። ምክንያቱም ብጹዕ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ከስደት ሲመለሱ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀውላቸው ነበር። ይህን ተከትሎ ለሁለት ወራት ያህል በወር 140ሺህ ብር የሚከፈልበት ቤት ውስጥ ኖረዋል። ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሶስት ወራት ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በወር 860 ብር የሚከፈልበት ቤት ውስጥ ኖረዋል። በዚህ መሰረት ኢ/ር ታከለ ኡማ ለሁለት ወር ያህል 140ሺህ ብር፣ ለሦስት ወራት ደግሞ 860 ብር ወራዊ ኪራይ የሚከፈልበት ቤት ውስጥ ኖረዋል። ላለፉት ሦስት ወራት የተከፈለው 860 ብር የቤት ኪራይ ከዚያ በፊት ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ የተከፈለውን 140ሺህ አይቀይረውም። ከዚያ ይልቅ ለሁለት ወራት የተከፈለው 280ሺህ ብር አሁን በ860 ብር የሚኖሩበትን ቤት የ27 አመት የቤት ኪራይ ይከፍላል። (280000 ፥ 860 ፥ 12 = 27) በዚህ መሰረት፤
አንደኛ፡- ም/ከንቲባው ለሁለት ወር ለኖሩበት ቤት የ27 አመት የቤት ኪራይ ከፍለዋል።
ሁለተኛ፡- እኔ ባወጣሁት መረጃ መሰረት የም/ከንቲባው መኖሪያ ቤት የሚከፈለው ወራዊ የቤት ኪራይ ታውቋል።
ሦስተኛ፡- መረጃ ማውጣትና መጠየቅ በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ ለማግኘት ያስችላል።
አራተኛ፡- የሃሳብና የመረጃ ነፃነት በመንግስት ሥራና አሰራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያመጣል ማለት ይሄ ነው።
አምስተኛ፦ ከዚህ አንፃር ለዋልኩት #ውለታ ምስጋና ሲገባኝ ጠዋት-ማታ ስድብና ዛቻ ይወርድብኛል!!!
“ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል!!!”
 
በነገራችሁ ላይ ኢ/ር #ታከለ_ኡማ በወር 860 ብር የቤት ኪራይ እየከፈለ በሚኖርባት እና በከንቲባነት በሚያስተዳድራት አዲስ አበባ ውስጥ ቀድሞ 225 ብር #የቤት_ኪራይ ይከፍሉ የነበሩ #የከተማ_ነጋዴዎች 43,972 ብር እንዲከፍሉ፣ 136,818 ብር ይከፍሉ የነበሩት ደግሞ 1,823,287 ብር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ 2,840 ብር ኪራይ ይከፍል የነበረን ነጋዴ 37,680 ብር ክፈል በሚባልበት ከተማ “#በ860 ብር የሚከራይ ቤት ውስጥ የምኖረው!” ማለት ሌላ ስላቅ ይሆናል፡፡ “ዓሳ ጎርጏሪ ዘንዶ ያወጣል” አሉ!!!
*****
ከላይ የተጠቀሰው የኪራይ መጠን #የንግድ_ቤቶች ቢሆንም የከተማዋን ነዋሪዎች የሚያስተዳድረው ከንቲባው እንደመሆኑ መጠን በነጋዴዎቹ ላይ የተጣለው የተጋነነ የኪራይ ተመን ልክ እንደ ራሱ #የመኖሪያ_ቤት ኪራይ ሊያሳስበው ይገባል፡፡
Filed in: Amharic