>

መንግስት መካን ስለሆነ ሲሳይ አጌናን ሊያፈራ አይችልም! (ዳጉ ቲዩብ) 

መንግስት መካን ስለሆነ ሲሳይ አጌናን ሊያፈራ አይችልም!
ዳጉ ቲዩብ 
      ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሲሳይ አጌና ያላቸውን አድናቆት ” መንግሥት እንደሱ ያለ ጋዜጠኛ አላፈራም ” በማለት ነው የገለጹት ። ሲሳይ አጌና በእርግጥ በምንም ቃል ቢገለጽ ይገባዋል ። ይህ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ምን ሰርቶ እንደ ሲሳይ አጌና ያለን ትንታግ ጋዜጠኛ ሊፈጥር ይችላል ? የሚለውን ጥያቄ ማሰብ ያስፈልጋል ። እስካለፈው ዓመት ያሉ መንግሥታት የዲሞክራሲ  መካኖች ናቸው ። ዘር ሊያፈሩ አይችሉም ።
    ለአንድ ብዙሃን መገናኛ ነጻነት ውድ ዋጋ ያለው ጉዳይ ነው ። የሐገራችን ብዙሀን ከተቋቋሙ ጀምሮ በታሪካቸው ነጻነት ኖሯቸው አያውቅም ። አቅማቸው የት ድረስ እንደሆነ ታይቶ አያውቅም ። እንደ አዝማሪ ነው የኖሩት ። ሚናቸው የአወዳሽነት ነው ። አንድም ጊዜ ሕዝብን እንዲያገለግሉ እድል ተሰጥቷቸው አያውቅሞ ። ሲሳይ የግል ብርታቱ አንድ ነገር ሆኖ ነጻነቱ የሰጠውም አለ ። አንድ የኢቴቪ ወይም የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ሲሳይን ልሁን ብሎ ቢነሳና ቢሳካለት እንኳ በማግስቱ የሚጠብቀው እድገት ሳይሆን ስንብት ነው ።
    የቀድሞዎቹን እንተዋቸውና የመንግሥት ( የሕዝብ አንድም የለምና ) የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ዛሬም የሙያ ነጻነት የላቸውም ። የግሎቹ ነጻ ሲወጡ የመንግሥቶቹ ግን አሁንም በግዞት ላይ ይገኛሉ ። ነጻነት የላቸውም ። ትናንት ወዲያ የንጉሡ አፍ ጠራጊዎች ነበሩ ። ትናንት የደርግና የሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ አወዳሽ እንደነበሩት ሁሉ ዛሬ ደግሞ የዶ/ር አብይ ኢሕአዴግ ቀዳሾች ናቸው ። መንግሥታዊ ብዙሃኖቻችን ትናንት ፀረ ደርግ ነበሩ ፤ ዛሬ ፀረ ” ለውጥ አደናቃፊዎች ” ናቸው ። መንግሥትን መድፈር ያልቻለ ብዙሀን መገናኛ ነጻነቱ የቱ ጋ ነው ? የወደቀውን መርገጥማ የኖርንበት ነው ። የመንግሥት ጋዜጠኞች የእውቀት ድኩማን ሆነው አሊያም በሆድ አደርነት ከሳጥን መውጣት እንዳቃታቸው ማሰብ ሚዛናዊነት አይደለም ። በዚህ የጥቁርና ነጭ አሰራር ሲሳይ አጌናን መፍጠር እንዴት ይቻላቸዋል ? እንዴትም ።
Filed in: Amharic