>

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በፈረንሳይ ጋዜጣ (ታደለ ጥበቡ)

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በፈረንሳይ ጋዜጣ
ታደለ ጥበቡ
ታህሳስ 1867 ዓ.ም ” La Lune “የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጣ “THÉODOROS II, ROI D’Abyssinie ” በሚል ርዕስ የፊት ሽፋን ስለ ዳግማዊ ቴዎድሮስ እንዲህ ጽፏል!!!
ዳግማዊ ቴዎድሮስ በአቢሲኒያ ግዛት 14 አውራጃዎች 5 ሚሊዮን ህዝብ ያስተዳድራል።የ50 አመቱ ቴዎድሮስ ጦረኛ፣ሊቅ፣የማሰብ ልዕልናው ከፍ ያለ፣የሥነ-መለኮት እውቀት ያለው፣ደፋር፣አሸናፊ፣ተክለ ሠውነቱ ግርማ ሞገስ የታደለ እና የአባቶችን ወግ ሥርዓት የሚያከብር ነበር ሲል ይገልጸዋል።
አጼ ቴዎድሮስ ጎንደር ላይ ረግቶ ከመቀመጥ ይልቅ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምክንያት ሲያስቀምጥ በየቦታው እንደ እንጉዳይ እየፈሉ የሚያስቸግሩትን ሽፍታዎች ለመደምሰስ ነበር።በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ የጨረሰው በድንኳን ህይወት ነው።
ዳግማዊ ቴዎድሮዎስ  ቀለል ያለ አኗኗርን የለመደ፤ወደ አቢሲኒያ የሚጓዙ የውጭ ዜጎችን  በታላቅ ክብር የሚቀበል ማለትም በጦር አለቆችና ሹመኞች ታጅቦ፣በሚያስደንቅ ጌጠኛ አለባበስ፥የአንበሳ ምስል ያለበት ዘውድ ደፍቶ፣በቀሳውስት ድባብ ደምቆ፣ፈርጣማ ከንዶችን በአንበሶች ላይ ጭኖ ይቀበላል።አንበሶቹ  በእያንዳንዱ ንግግር ላይ ያገሱ ነበር”በማለት በቦታው የተገኘው  የፈረንሳይ ጋዜጠኛ ዘጋቢ ይገልጻል።
የፈረንሳዩ ጋዜጣ  የአጼ ቴዎድሮስን ንጉሳዊ ስነ-ስርዓት ከውጭ ንጉሳዊ ስነ-ስርዓት ጋር እያጣቀሰ የገጸለው ሲሆን “አጼ ቴዎድሮስ ጨካኝ አይደለም፥ይልቁንስ እንደ ክሮምዌ ፍጹም ክርስቲያን ነው።እንደ ልዑላዊነቱ በጋብቻ ጸንቶ መኖርን የሚወድ፣ወላጅ አልባ ህጻናቶችን በክብካቤ የሚያሳድግ፥የሚያስተምር፥የሚያሰለጥን፥ በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያጀግናቸው ነበር። እንደ ንጉሥ ሳይሆን እንደ ተራ ግለሰብ ከህጻናቶች ጋር  በድንኳኑ ውስጥ እና በሜዳው ያጫውታቸዋል።”ካለ በኋላ “እንዲህ ያለ ምስጉን ባህሪውን የሚያስቀይሩት በየቦታው የሚያምጹት ሽፍቶች ናቸው።በእነዚህም ላይ በደመነፍስ ሳይሆን በጥንቃቄ የማያወላዳ እርምጃ ይወስዳል”ብሎታል።
ዳግማዊ ቴዎድሮስ ስጓዝ ውሎ ቢያድር ድካም የማይሰማው ቆራጥ መሪ ነበር።አንዳዴም እሱን የሚያንኳሱሱትን እንግዶች ሆነ ባለሥልጣኖች ለመፈተን በፍጥነት ወደ ተራራው ጫፍ ይወጣና ተመልሶ በፍጥነት ተንደርድሮ ይወርዳል።በዚህን ጊዜ እንደሱ እንዲሞክሩት ሲጠይቃቸው ተራራውን ለመውጣት ተቸግረው ሳር ቅጠሉን ሲቧጥጡ ሲያዬ ፈገግ ይላል።በግጥሚያው ባሸነፈ ማግስት ተሸናፊዎች እራት ጋብዞ ኮሳ በዋንጫ እንዲታደላቸው ያዝዛል።ይቀጥልና
“ገብያው ጥሩ አይደለም መሰል ድሃዋ እናቴ ዛሬ አልቀናትም።እርዷት!!..ጌቶች ጡጡ፤ያልታደሉት ዋንጫ ሙሉ ዝቃጭ ጨልጠው ይጠጣሉ”ይላቸዋል።ነገርዬው አጼ ቴዎድሮስ አልቧልተኛ የሚላቸውን ተሸናፊዎች እርሱን ለማሸማቀቅ “የኮሶ ሻጭ ልጅ”እንደሚሉት ስለሚያውቅ ነው።
ዳግማዊ ቴዎድሮስ ያልተለመዱ ነገሮችን በማድረግ ይታወቃል ይላል የፈረንሳዩ ጋዜጣ።መልከ መልካሟን እትጌ ተዋበችን መልአከ ሞት ከነጠቀው በኋላ አዝኖ ከርሟል።በኋላም የመሳፍንት ዘር ያላትን ራሷን በንጉሳዊ ቤተሰብ አይን እያዬች ለቴዎድሮስ ክብር የማትሰጠውን የአጼ ዮሐንስ 4ኛ ልጅ ልዕልት ጥሩወርቅን አግብቷል።ጥሩ ወርቅ ለአጼ ቴዎድሮስ ክብር ባለመስጠቷ ንጉሡ በንዴት 4 ዕቁባቶችን እንደያዘ ጋዜጠው ይገልጻል። በኋላ ግን  በሚገባ ታዛዥ ከሆነችው በስተቀር 3ቱን ዕቁባቶች ተዋቸው።
በዚህ ምክንያት ቀሳውስቱ የቤተክርስቲያን ህግና ሥርዓት የሚጥስ ነው በማለት ተቃውመውታል።እንዲያውም አንዳንድ ቄሶች በድፍረት ዘወትር በትንሳኤ ዋዜማ የሚፈጸመውን የይቅርታ ሥርዓት እስከማቆም ደርሰው እንደነበር ያትታል።አጼ ቴዎድሮስ ተቃውሞው ሲበረታባቸው ከወደዷት ዕቁባት ጋር ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ቢሞክሩም ከ10 ቀን አልዘለሉም።
ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከመጀመሪያው ትዳራቸው 2 ልጆችን ወልደዋል።አንደኛው ልጁ በባህሪው ቁጡ፣ቴዎድሮስንም ጭምር የሚያናድድ በመሆኑ ታስሮ እንደነበርና ባልታወቀ ምክንያት እንደሞተ ጋዜጠው ያወሳል።ይቀጥልና ለአልጋ ወራሽነት ታጭቶ የነበረው ሁለተኛ  ልጁ መሸሻ የ28 ወጣት እንደነበርና መልከ መልካም፣አስተዋይ፣አባቱ ሳይቀር የሚቀኑበት ተወዳጅ ልጃቸው ነበር”በማለት ይገልጸዋል።
አጼ ቴዎድሮስ ተስማሚ የአየር ንብርት እና  ምርታማ ሀገር የሆነችውን አቢሲኒያን እንደሚገዛ፣ስለቤተሰቦቹ ከዘረዘረ  በኋላ  የካሜሮን እና ራሳም እንዲሁም ተከታዮቻቸው ለረዥም ጊዜ በእስር ቤት መቆየት ምክንያት በማድረግ ስለዘመተው የእንግሊዝ ጦር ጽፏል።
በጊዜያው እንግሊዞች በአውሮፓ የአጼ ቴዎድሮስን ምስል በካርቶ መልክ እያዘጋጁ የሚነዙት ፕሮፖጋንዳ የፈረንሳይ ጋዜጣ መሰረተ-ቢስ ሲል ያጣጥለዋል።
“አጼ ቴዎድሮስ ለንግስት ቪክቶሪያ ለላኩት የእርዳታ ጥያቄ መልስ አለማግኘት በጣሙን እንዳሳዘናቸው ገልጾ ስለ አጼ ቴዎድሮስ በአውሮፓ ጭራቅ ተደርገው እንደሚሳሉት ሳይሆኑ አጼ ቴዎድሮስ አዛኝ፥ሩህሩህ፥በከፍታ የሚመለከቱ፥ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን የሚቃወሙ፥ክርስቲያን የሆኑ ጀግና ነበሩ” ይላቸዋል።
ጋዜጣው ጽሁፉን ሲያጠቃልል፦
“በአጭር ቃል ዳግማዊ ቴዎድሮስ አፍንጫቸው ላይ ላባና ቀለበት እንደሚያደርጉ ጨካኞች አይደሉም፤ ነገርግን  እኛ ከምናውቀው ማህበረሰብ በትንሹ ዝቅ ያለ ሥልጣኔ ላይ ያሉ ነጻ ህዝቦችን የሚያስተዳድር ንጉሥ ነው፤በቃ። አጼ ቴዎድሮስ በእዝነ-ህሊናቸው በቅርቡ ያጡትንና የሚወዱትን ጓዳቸውን እንግሊዛዊውን ቤልን እያስታወሱ ከልብ በመነጨ ሃዘን ፊታቸው በእንባ የሚታጠብ ንጉሥ ነው”…..በማለት በአካል ተገኝቶ የዘገበው ጋዜጠኛ ጽሁፉን ይደመደማል።
Filed in: Amharic