>

አዲስ አበባ ከኦ.ዴ.ፓ ሞግዚትነት - ከታከለ ኡማ መስተዳድር መላቀቅ አለባት  !!!  (አብነት እንግዳ)

አዲስ አበባ ከኦ.ዴ.ፓ ሞግዚትነት – ከታከለ ኡማ መስተዳድር መላቀቅ አለባት  !!! 
አብነት እንግዳ
 …ታከለ፣ በኦሮምኛ “እንኳን በፊንፊኔ ዛሬ ተገናኘን። ለፊንፊኔ ተብሎ ብዙ ሰው ታስሯል። ተሰቃይቷል። ከሃገር ተሰዷል። በአባቶቻችን ሃገር ቀና ብለን መሄድ  እየቻልን፤ እየፈለግን ከዩኒቨርሲቲ ተባረናል። ዋጋ ለፊንፊኔ ከፍለናል” ሲል አዲስ አበባን የኦሮሞ መሬት እንደነበረች፣ ተነጥቀው እንደነበረና አሁን ግን  በእጃቸው እንደወደቀች አይነት የ”ድል” ንግግር ነበር ያደረገው።
አንደኛ – ታከለ ወደ ሃላፊነት የመጣው ፣ እርሱን ለማስመረጥ አሻጥር ተሰርቶ ነው። የከተማ ከንቲባ የሚመረጠው ከከተማዋ ምክር ቤት አባላት ውስጥ ነበር። ሆኖም ታከለን ለማስመረጥ ፓርላማው የአዲስ አበባን ምክር ቤት ሕግ እንዲቀይር ተደረጎ ሕገ ወጥ በሆነ አሰራር ነው የቸሾመው።
#ሁለተኛ ታከለ ምክትል ከንቲባ ከመሆኑ በፊት በአዲስ አበባ ላይ ጽንፈኛ አመለካከት ነበረው። ፊንፊኔ የሚላት አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ብሎ የሚያምን ሰው ነው። በቅርቡ ከንቲባ ከሆነ በኋላ አዲስ አበባ የሁሉም ናት ሲል ተደምጧል። ግን ለማስመሰል ያለው እንጂ የአመለካከት ለውጥ አድርጎ አይደለም። ኦነግን ለመቀበል በተደረገው ዝግጅት በኦሮምኛ የተናገረው ተተርጉሞ አንብበነዋል። እንደሚታወቀው አንዳንድ የኦሮሞ ቄሮዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ ነቅለው በጀብደኝነት የኦነግን ለመተካት ሲሞክሩ ግጭቶች ተፈጥሮ ነበር። ግጭቶችን ለማረጋጋት ፖሊስ ለተወሰነ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገቡ ወገኖች እንዲቆዩ በማድረግ ግጭቶች እንዳይባባሱ ለማድረግ ሞክሯል። በኋላም ሁሉም ገብተው በሸገር ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ሆኖም ታከለ ግጭቶች እስኪረጋጉ ለሰላም ሲባል የተወሰደውን ጊዚያዊ የመንገድ መዝጋት እርምጃ፣ በኦሮሞ ላይ በደል እንደተፈጸመ አድርጎ ነበር ያቀረበው። በዚያ የነበረው ኦሮሞ በደል ደረሰብኝ ብሎ እንዲሰማው ነው ያደረገው። ከማረጋጋት፣ ከማሰባሰብ፣ አንድ ከማድረግ ይልቅ የአዲስ አበባን ህዝብ ነው በኦሮምኛ የከሰሰው።
” ከዋዜማ ጀምራችሁ የዉሃ ጥማት ሳይበግራችሁ ርሃብ ሳያስቸግራችሁ፣ ብርዱ ስይበግራችሁ ስድብ ሳያስቸግራችሁ፣ አትገቡም ብትባሉ እንኳን ሳትበገሩ ..እንኳን ወደ ግዛታችን ወደ አባቶቻችን እምብርት ሃገር በሰላም መጣችሁ” ሲል ነው ታከለ ተበዳይ፣ ጻድቅ ቄሮ፤ በዳይ፣ ተሳዳቢ የአዲስ አበባ ወጣቶችን አድርጎ የሳለው።
አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ናት ሲል የነበረው ታከለ፣ በኦሮምኛ “እንኳን በፊንፊኔ ዛሬ ተገናኘን። ለፊንፊኔ ተብሎ ብዙ ሰው ታስሯል። ተሰቃይቷል። ከሃገር ተሰዷል። በአባቶቻችን ሃገር ቀና ብለን መሄድ  እየቻልን፤ እየፈለግን ከዩኒቨርሲቲ ተባረናል። ዋጋ ለፊንፊኔ ከፍለናል” ሲል አዲስ አበባን የኦሮሞ መሬት እንደነበረች፣ ተነጥቀው እንደነበረና አሁን ግን  በእጃቸው እንደወደቀች አይነት የ”ድል” ንግግር ነበር ያደረገው።
#ሶስተኛ –  ታከለ  የእቴጌ ጣይቱ ሃዉልት እንዲሰራ ከተወሰነ በኋላ የአዲስ አበባ እናት የሆንችዋን የእቴጌን ሃዉልት እንዳይሰራ አግዷል። የተጣለውን የመሠረት ድንጋይም አፍርሷል።
#አራተኛ – ታከለ በአዲስ አበባ ቋሚ አድራሻ ለሌላቸውና ስራ አጥ ናቸው በሚል የአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ ኦሮሞዎች በገፍ መታወቂያ እንዲታደል በማመቻቸት መታወቂያው አሁኑ ሰአት በየክፍለ ከተማው በመታደል ላይ ይገኛል።
ታከለ ኡማ መታወቂያ ማደል የፈለገበት ብቸኛ ምክንያት በአዲስ አበባ ቁጥሩ አናሳ የሆነውን የኦሮሞ ማህበረሰብ በመታወቂያ እደላ በማሳደግ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ከቀየረ በኋላ፤ ወደፊት ለሚካሄዱ ማናቸውም አይነት ምርጫዎች ድምፅ ለማግኘት ነው የሚለውን ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲነሳ ያደርጋል።
የአዲሱ መታወቂያ አሰጣጥ መመሪያ የከተማ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ እንዲያገኙ ክፍተት ይሰጣል። ይህን አሰራር ደግሞ የከተማዋን ነዋሪ ድምፅ ለማጭበርበር የተሸረበ ደባ ከመሆን ተናንሶ አይታይም።
#አምስተኛ – ታከለ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከ15 እስከ 20 አመታት ከኖሩበት ስፍራ በስመ ህገወጥ እያፈናቀለ ለጎዳና ተዳዳሪነት እያደረጋቸው ይገኛል።
አዲስ አበባ ዛሬ ነዋሪዎቿን ከቤታቸው እያፈናቀለ ጎዳና ላይ እያሰጣ በሚድያ ቀርቦ ” ጎዳና የወደቁትን እናንሳ – ትረስት ፈንድ”  እያለ በዜጎች ሰቆቃ  የሚያላግጥ የፖለቲካ ሹመኛ ነው።
 ከአዲስ አበባ ጫፍ ከካራ ቆሬ የጀመረው ስደት አሁን 4 ኪሎ ከቤተመንግሥቱ ስር ከተፍ ብሎልሃል። በታከለ ኡማ አስተዳደር ገፊነት ህጻናቱ ሜዳላይ ፈሰዋል። አረጋውያንና እናቶች ይሸሸጉበት፣ ጥግ ይሰደዱበት ሀገር አጥተዋል። የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሌለ ታይቶና ተሰምቶም በማያውቁት የፖለቲካ ስካር ላይ ናቸው። ፉከራና ቀረርቶ ላይ ናቸው። ከላይ እስከታች ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ሃብትና ንብረት ላይ እየተረባረቡ ነው። ምንም ሼም የሚባል ነገር አይሸምማቸውም። ክፍለከተሞች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ መንግሥታዊ ቢሮዎች በሙሉ የኦሮሞ ስም በያዙ የሥራ ኃላፊዎች ተተክተዋል እየተባለ ነው። ሃጎስ ወደ መቀሌ ገመቹ ወደ ቀበሌ በሰላም በጤና ተሸጋግረዋል።
ለልማት ተነሺ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በተመለከተ ደግሞ ሁሉም የልማት ተነሺ በአንድ አይነት ህግ መተዳደር ሲገባው፤ የኦሮሞ ገበሬዎች ብሎ በመለየት በተለየ እንዲጠቀሙ ልዮ ህግ በማውጣት ሚዛናዊ ያልሆነ ብሔርተኝነትን የሚያራምድ፤ ሌላውን የአዲስ አበባ ተፈናቃይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚያይ አሰራር በታከለ ኡማ እየተተገበረ ነው።
ታከለ የአዲስ አበባ ከንቲባ የመሆን መብት አለው። ምርጫ ሲደረግ እንደማንኛውም ዜጋ #ተወዳድሮ መሆን ይችላል። ሆኖም ግን አሁን በሹመት በተገኘ ስልጣን የአዲስ አበባን ህዝብ ፍላጎት ሊያስጠብቅ አይችልም። የአዲስ አበባን ህዝብ ሊመጥን አይችልም። አዲስ አበባ መተዳደር ያለባት የአዲስ አበባ ነዋሪ በመረጠው እንጂ  #በኦዴፓ ሹመኞች ሊሆን አይገባም።
አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ማስተዳደር፣ የራሷን እድል በራሷ የመወሰን መብቷ ተጠብቆላት፣ ከኦዴፓ ሞግዚትነት መላቀቅ አለባት። በመሆኑም በአዲስ አበባ ድምጻችንን እያሰማን ያለን ወገኖች ጥያቄ ትክክል ነው። ታከለ ኡማ በአስቸኳይ እያደረሰ ካለው ጥፋት ተነስቶ አዲስ አበቤ በመረጠው ከንቲባ መተካት አለበት።
አንዳንድ ዘረኞች ታከለ ኦሮሞ ስለሆነ ነው ይላሉ። ጎበዝ እኛ ኦሮሞውን ዶ/ር አብይ፣ ኦሮሞዉን አቶ ለማ የደገፍን ነን።”
Filed in: Amharic