>

"ጋዜጠኛ ነኝ" ብሎ በተጠያቂው አቋም መዘባበት ሙያዊ ሥነ ምግባር አይደለም!!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ጋዜጠኛ ነኝ” ብሎ በተጠያቂው አቋም መዘባበት ሙያዊ ሥነ ምግባር አይደለም!!!
በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
ቤቴልሔም ታፈሰ ከይልቃል ጌትነት ጋር በኤልቲቪ ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ትላንት አየሁት። በእውነቱ በጣም ነው ያዘንኩት። አቀራረቧ ማሳጣት (bullying) እንጂ በጥያቄ መገዳደር ሊባል አይችልም። ይልቃል እንደማንኛውም ፖለቲከኛ ብዙ ሊጠየቅ ይችላል። እሷ ግን ራሷ እርግጠኛ ሆና ያመነችውን ነገር እንዲቀበልላት እና መሳሳቱን እንዲያምንላት ስድብ የሚመስሉ ቃላትን ሳይቀር ተጠቅማለች። ጋዜጠኞች ተጠያቂዎችን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ማውጣጣት ይችላሉ። በአቋማቸው ግን መዘባበት (to be judgemental) ሙያዊ ሥነ ምግባር አይደለም። ይልቃልን ደጋግማ  “ግብዝ ነህ” ስትለው ነበር። በዚያ ላይ የጠየቀችውን ጥያቄ ለመመለስ ጀምሮ ገና አንድ ዓረፍተ ነገር ሳይጨርስ ታቋርጠዋለች። ሌላው ቀርቶ ሊጠየቅ የሚገባውን ብዙ ጥያቄዎች አንድ ጉዳይ ላይ እኝኝ በማለት አባክናዋለች። ቤተልሔም ከዚህ በፊትም ሠራዊት ፍቅሬን እንዲሁ “የሆንከውን ነገር ለምን ሆንክ” እያለች ስታደርቀው አይቻለሁ። እዚያኛው ቃለ ምልልስ ላይ ጥያቄዋ ረብ የለሽ ከመሆኑ የተነሳ ካሜራ ፊት ሳቋ አምልጧታል። የማዝነው አጠያየቋ የጎደፈ፣ እርግጠኝነቷም በተሳሳተ መሠረት ላይ የቆመ እንደሆነ የሚነግራት ተጠያቂ ስላልገጠማት ነው። ወይም ደግሞ ጥፋቱ የኔ ይሆናል፤ እሷ የምታስባቸው ተደራሲዎች (audiences) ሐቀኛ የፖለቲካ ውይይት የምንፈልገውን ሳይሆን “ቤተልሔም አስገባችለት” እንዲባል የምትፈልጋቸውን የብሽሽቅ ፖለቲከኞችን ይሆናል
ሊንክን አያይዣለሁ:-
Filed in: Amharic