>

ወደ ኤርትራ እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ...!!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ወደ ኤርትራ እንሂድ ባሉኝ ጊዜ …!!!
አፈንዲ ሙተቂ
ኤርትራ! ኤርትራ! ኤርትራ
የቢለን ጭፈራ መድመቂያ ሰፈር! የብሄረ ትግርኛ ሹሩባ መነስነሻ መንደር! የትግረ ሰይፍ መወልወያ ምድር! የአፋር ጊሌ መሥሪያ ደብር! የሳሆ ጦር መወርወሪያ ብኩር! የረሻይዳ ጂልባብ መስፊያ ክር!
ኤርትራ! በረከት መንግሥተአብን የሰጠችን ቀበሌ! አልአሚን ዐብዱለጢፍን የቀደሰች ምሳሌ! ፀሐይቱ ባራኪን ያፈራች ብርሌ! አብረሃም አፈወርቂን የወለደች ቱሩምቡሌ! አሕመድ ሼክን የባረከች ለሁሌ! ብሩክታይት ጥበበኛ የማይነካት ገለመሌ!
ኤርትራ! የሄለን መለስ ግጥም መቀመሪያ! የሄለን ጳውሎስ እስክስታ መወርወሪያ! የፋጢማ ዓሊ ወርቀዘቦ ጌጥ መውቀሪያ! የዘይነብ በሺር “ሸሊል” ፀጉር መሽከርከሪያ! የኤልሳ ኪዳነ የከበሮ ምት መዘወሪያ!
ኤርትራ! አቲ ሲኞሪና! አደይ ሳቢና! አደይ ፊዮሪና! አደይ ሮዚና! ቤላ የውበት እመቤቶችን ያበቀለች ሽኮሪና!
ኤርትራ! የኢብራሂም ሱልጣን ወኔ መቀስቀሻ! የወልደኣብ ወልደማሪያም ራእይ መተንፈሻ! የሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ ትግል መጠንሰሻ! የኢብራሂም ዓፋ ጀግንነት መቋደሻ! የኢሳያስ አፈወርቂ የድል ጉዞ መዳረሻ!
—-
ኤርትራ ጸኣዳ!
ኤርትራ አራዳ!
ኤርትራ አሚራ!
ኤርትራ ከቢራ!
ኤርትራ መሊካ
ኤርትራ መብሩካ!
ወላሂ እንደ ነፍሴ ነው የምወድሽ!
ከሀገሬ ነጥዬም አላይሽ!
——-
ለብዙ ወራት ድምፁ የጠፋብን ተስፋዬ ገብረአብ እነሆ ተገኝቷል። ከጥቂት ወራት በኋላ ከሚናፍቀን የኤርትራ ህዝብ ጋር እንገናኛለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን።
—–
በነገራችን በዚህ “የኤርትራ ህልም” በተሰኘ ድርሰት እንዳያነበባችሁት እያንዳንዱ የኤርትራ ከተማ እና አውራጃ የተመልካቹን ቀልብ የሚስብበት የየራሱ የተለየ ምልክት እንዳለው ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ለምሳሌ ተሰነይ የምትታወሰው ሳቂታው የቤኒአሚር ወጣት የበቀለባት በመሆኗ ነው። ናቅፋ ከልብ የማትጠፋው የህዝባዊ ግንባር ታጋዮች በዚያች ጠባብ ስፍራ በብዙ እጥፍ የሚበልጣቸውን ባለጋራቸውን በፅናት የታገሉበትን ታሪክ በስፋት በማንበባችን ነው። ከረን የምትወደደው የብዙ የኤርትራ ብሄረሰቦች የጋራ መገናኛ በመሆኗ ነው። ምፅዋ ደስ የምትለው ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሳይቋረጥ በዘለቀ ታሪኳ ነው። አስመራ የምትናፈቀው የጨዋታ አዋቂዎቹ እና የደጋጎቹ አስመሪኖዎች መፍለቂያ በመሆኗ ነው።
እንግዲህ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማዳረስ ባይቻለንም በተለያዩ ጊዜያት እናያቸዋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
Filed in: Amharic