>

አምሀ እሸቴ - የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለዉለታ!!! (ታሪኩ አበበ)

አምሀ እሸቴ – የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለዉለታ!!!
ታሪኩ አበበ
በልጅነቱ በሥራ ምክንያት ከአዲስ አበባ አስመራ ሲመላለስ በአስመራ አሜሪካኖቹ ከፍተውት የነበረው የቃኘው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ የሙዚቃ ፍቅሩን በእጥፍ እንደጨመሩለት ይናገራል፡፡
በአዲስ አበባም ቢሆን የክቡር ዘበኛ ንብረት የነበረው የጠቅል ሬዲዮ ጣቢያ አልፎ አልፎ የሚለቃቸውን ሙዚቃዎች መስማት የመንፈስ ሀሴትን ያጎናፅፉት ነበር፡፡
አምሃ እሸቴ ከአሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከእንግሊዝ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እና ከጣሊያን በ1950ዎቹ መጨረሻና በ60ዎቹ መጀመርያ የነበሩ ተወዳጅ የሙዚቃ ሸክላዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስመጣት እና በመሸጥ ነበር የሙዚቃ ዓለምን የተቀላቀለው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ፍቅር ማህበርና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትያትር ቤቶች በጊዜው ሙዚቃን የማሳተም መብት ከግርማዊነታቸው በፅህፈት ሚኒስቴር በኩል ቢሰጣቸውም ተግባራዊ ሳያደርጉት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡
ይህን የተመለከተው ወጣቱ አምሃ ለምን እኔ አላሳትምም ሲል በድፍረት ተነሳ፡፡
በወቅቱ ከትያትር ቤቶቹ የተሰጠው ምላሽ “መብቱ የኛ ነውና እንዳትሞክረው” የሚል ዝግ መልስ ነበር፡፡
አምሃ ጉዳዩ አስጨነቀው፡፡ የንጉሰ ነገስቱን ህግ መጣስ ደሞ የሚያመጣውን መዘዝ ያውቃል፡፡
በሌላ ጎኑ እሱ የተለያዩ የውጭ ሀገራትን ሙዚቃ እያመጣ እየሸጠ የሀገሩ ሙዚቀኞች በሸክላ አለመቀረፅ፣ ለሌላውም ዓለም አለመተዋወቅ ከንክኖታል፡፡
ያለው አማራጭ በድፍረት አሳትሞ የሚመጣውን በፀጋ መቀበል ብቻ ሆነ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚተባበር ድምፃዊ ያስፈልጋል፡፡
አምሃ የሚያውቃቸውን ዘፋኞች አማከረ፡፡ ሁሉም ፈሩ፡፡” አዬ ጦስ ታመጣብናለህ “ እያሉ ወደኋላ አፈገፈጉ፡፡
በዚህ መሀል አንድ ወጣት ድምፃዊ ብቅ አለ፡፡ ድምፃዊው ከአምሃ ጋር የማይደፈረውን ለመድፈር ተስማማ፡፡
“ ከታሰርንም እየዘፈንን አብረን እንገባለን” ሲል የአምሃን ልብ በወኔ ሞላው፡፡ እናም ሆነ፡፡ እንደተፈራው እዚህ ግባ የሚባል ቅጣት ግን አልነበረም፡፡
ይህ ድምፃዊ ተወዳጁ አለማየሁ እሸቴ ሲሆን በአጋጣሚውም በአምሀ እሸቴ ሪከርድስ አማካኝነት የመጀመርያ የሸክላ ሙዚቃ አሳታሚ ለመሆን በቃ፡፡
ይህም ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በጀርመን ሀገር ካሳተሙት መዲናና ዘለሰኛ፣ ከነፈረደ ጎላ የሸክላ ስራ፣ እንዲሁም በጣሊያን ወረራ ወቅት ከታተሙ ጥቂት ሸክላዎች በኋላ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ህትመት ለመሆን በቃ፡፡
Filed in: Amharic