>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6215

«ኮርማ አርደን ሰላምን እናበስራለን! ካሁን በኋላ ጦርነት የለም!!!»  አባገዳዎች

«ኮርማ አርደን ሰላምን እናበስራለን! ካሁን በኋላ ጦርነት የለም!!!» 

አባገዳዎች

በሳምራዊት ግርማና ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን

አምቦ፡- ባለፈው ማክሰኞ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የኦነግ ሰራዊት ለአባገዳዎች መሰጠቱን፣ መንግስትም የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን ተከትሎ ተግባሩን የሚከታተል ኮሚቴ መዋቀሩ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ኮሚቴው ወደ አምቦ ተጉዞ ሦስት አካላትን ማለትም የአንቦ ዩኒቨርሲቲን፣ አባ ገዳዎችንና የአካባቢው ማህበረሰብን እንዲሁም የጀስቲስ ፎር ኦል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትን በማካተት ስለ እርቀሰላም ጥቅምና ውጤት በመመካከር ሰላም የማውረድ ሥራ ሰርቷል።

በማክሰኞው ዕለት በነበረው ውይይት አንድ ምሁር «ኦሮሞ እንዲታረቅ ከብት ማረድ ያስፈልጋል። ስለዚህም እኔን እረዱኝና እርቅ አውርዱ» በማለት ለሰላም ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው በዚያው የሚገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች «እርሶም አይታረዱ ሰላምም ከመስፈን አይቀር፤ ኮርማ አርደን ሰላምን እናበስራለን ። ካሁን በኋላ ጦርነት የለም» በማለት የገቡትን እውን አድርገዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የኮሚቴው ጸሃፊ አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ የሰላምን ጠቀሜታ በማውሳት ኮሚቴው በሚገባ ተወያይቶ የደረሰበትን ስምምነት እንደገለፁት «በ20 ቀናት ውስጥ በጫካ ያለው የኦነግ ሰራዊት በሰላማዊ መንገድ ወደ ህዝብ እንዲቀላቀል ኮሚቴው ትዕዛዝ አስተላልፏል። በዚህም መጪው አስር ቀናት የዝግጅት ጊዜ ይሆናሉ። ከአስር ቀናት በኋላ ደግሞ በየደረጃው ኮሚቴ ተቋቁሞ ለሠራዊቱ አቀባበል ይደረግላቸዋል። ከዚያም ወደ ካምፕ ይገባሉ» ብለዋል።

አክቲቪስት ጃዋር ጦርነት  መቆሙን፣ ይህንን የማይቀበል አካል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ምንም እውቅና እንደማይኖረውና እንደሚወገዝ ፤ ሰላም እንዲመጣና ትዕዛዙ ተግባራዊ እንዲሆንም በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ኦነግ አስፈላጊውን ስልጠና ከወሰደም በኋላ ፍላጎት ያለው በፀጥታው ዘርፍ፤ የማይፈልግ ደግሞ በራሱ እንዲሰራ ማገዝ ላይ ከመንግስትም ሆነ ከማህበረሰቡ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ  አሳስበዋል።

የጉጂ አባገዳ ጅሎ ማኖ በበኩላቸው  «አንድ ወር ሙሉ በሰላም ዙሪያ አስተምረናል፤ ሰላምን ሰብከናል፤ ይሁንና ለውጡ በዚህ ፍጥነት ይመጣል ብለን አላሰብንም። ጥረታችን ውጤት አምጥቶ በማየታችን በጣሙን ተደስተናል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ህዝቡ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስት ምን ያህል ለአባገዳዎች እንደሚታዘዙና ለገዳ ሥርዓት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ የተገነዘብንበት ነው፡፡ ይህንን ሰላምና መከባበር መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ማህበረሰቡ ለሰላም መስፈን እንቁ ባህል አለውና ሊጠብቀው ይገባል» ብለዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀንኣ እንደተናገሩት፤ አሁን የተገኘውን ለውጥ ለማምጣት ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ብዙ መስዋዕትነትም ተከፍሎበታል፤ ከጦርነት ምንም አይገኝም። በፖለቲካ ሥርዓት አልበኝነት ህዝቡ ዋጋ መክፈል የለበትም። ስለሆነም ይህንን ለውጥ ለማስቀጠል ቅድሚያ ለሰላም መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በሰላማዊ መንገድ የተገኘውን ለውጥ ለመደገፍ ሁሉም መረባረብ አለበት።

የጀስቲስ ፎር ኦል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ «የኦሮሚያ ሰላም ማለት የኢትዮጵያ ሰላም ነው። ኦሮሞ የሰራው ባህል ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነትን ያሳያል። ለዚህም ምስክሩ እኔ ነኝ። በባህሉ በማደጌ ለአባቶች ክብር እሰጣለሁ። ስለዚህ ክብሩ የሆነውን  ሰላም ማስከበር ላይ መስራት ግድ ነው። ሰላም ከሌለ አገር መገንባት አንችልም። በባህላዊ መንገድ እርቀሰላምን ማውረድ የሚደገፍና ትውልድ የሚያስተምር በመሆኑ መጠቀም ያስፈልጋል» ብለዋል።

የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሞገስ ኤደኤ በበኩላቸው፤ አባገዳዎች ያደረጉትን ሥራ አድንቀው ፤ ለሰሩትም ሰላም የማስፈን ሥራ ምስጋና እንደሚገባቸው፤መንግስትም በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ፤  ሂደቱ ከተወሰነው ጊዜ ቢፈጥን በኦሮሚያ ክልል የተስተጓጎለውን ትምህርት መልሶ ለማስቀጠል እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

Filed in: Amharic