>

“የከፋ በደል የፈፀሙ ናቸው ብዬ ስለማምን በመታሰራቸው እፎይታ ነው የተሰማኝ!!!”  አና ጎሜዝ

“የከፋ በደል የፈፀሙ ናቸው ብዬ ስለማምን በመታሰራቸው እፎይታ ነው የተሰማኝ!!!”
 አና ጎሜዝ
ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን
በትዊትር ገፃቸው “በመጨረሻ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመተንፈስ እድል ሊያገኝ ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን አስፍረው፣ አቶ በረከትን ከጀርመኑ ፕሮፓጋንዳ ሚ/ር ጆሴፍ ጎብልስ ጋር አመሳስለዋቸው ነበር፡፡
.
እርግጥ ነው አና ጎሜዝ በአቶ በረከት ላይ በተደጋጋሚ ጠንካራ ተችት በመሰንዘር ይታወቃሉ፡፡ አቶ በረከት በጥቅምት ወር አጋማሽ 2010 የስልጣን መልቀቂያቸ ማቅረባቸው በተሰማ ጊዜ አና ጎሜዝ ደስታቸውን ገልፀው “ጨካኝና እምነት የማይጣልባቸው ግለሰብ ናቸው” ሲሉ ከረር ያለ ትችት ሰንዝረውባቸው ነበር፡፡ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ/ም እንዲሁ በአቶ በረከት ከብአዴን አባልነት መታገድ ደስታቸውን ገልፀው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው የሚል አስተያየት ሰንዝረው ነበር፡፡
.
በወቅቱ አቶ በረከት፣ የቢቢሲ አማርኛ ዘጋቢ “አና ጎሜዝ በትዊተር ገጻቸው ላይ ስለሰጡት አስተያየት ምን ምላሸ አለዎት?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡
“… ወይዘሮ አና ጎሜዝ ፖርቹጋላዊት ናቸው። ፖርቹጋል የአውሮፓ አፍሪካ ነው የምትባለው። በደንብ ካልለሙት አገሮች አንዷ ናት። ሴትየው በቁም ነገር የሚያስቡ ከሆነ ስለ ፖርቹጋል ቢያስቡ፤ ጊዜያቸውን የአገራቸውን ችግር በመፍታት ቢያውሉት። ኢትዮጵያ ሉአላዊት አገር ናት። ሿሚ ሻሪ የአገሬው ሕዝብ ነው። ‘እርስዎን አያገባዎትም። አርፈው ይቀመጡ። ፖርቹጋልን ቢያግዙ ይሻልዎታል’ በልልኝ። ይሄ በሉአላዊት አገር ጣልቃ መግባት የድሮ የፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ አለቀቃቸውም።” የሚል ምላሽ ሰጠተው ነበር፡፡
.
የሆነ ሆኖ ትናንትና ጥር 15 ቀን 2010 ዓ/ም አቶ በረከት ስምኦን መታሰራቸው እንደተሰማ ደግሞ ጎሜዝ በትዊትር ገፃቸው ከሂትለሩ አፈ ቀላጤ ጆሴፍ ጎብልስ ጋር አመሳሰሏቸው፡፡ ከዚህ አስተያየት በኋላ የቪኦኤ ጋዜጠኛ አሉላ ከበደ አጭር ቃለ ምልልስ አደረገላቸው፡፡ አና ጎሜዝ ለስራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ደቡባዊ ግዛት ፍሎሪዳ እየተጓዙ ነበር፡፡ ለአጭር ጊዜ በሚያሚ አውሮፕላን ጣቢያ ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ነው በስልክ ያነጋገራቸው፡፡
.
“…. እፎይታ ተሰምቶኛል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በፈፀሙት እጅግ የከፋ የመብት ጥሰት እና የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ረገድ ሚና ነበራቸው፡፡….”
.
ቀጠሉ አና ጎሜዝ፡-
“ በእርግጥ የተከሱበትን ጭብጥ ሙሉ በሙሉ አላውቅም፤ በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸን ግን ሰምቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በፈፀሙት በደል፣ በበኩላቸው ተጠያቂ ይሆናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”
.
አና ጎሜዝ በ1997 የአውሮፖ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ በነበሩበት ወቅት ከአቶ በረከት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማስታወስ አስተያየታቸውን ይቀጥላሉ፡-
“….ያኔ በነበረኝ ግንኙት እንደተረዳሁት፣ እርሳቸው በፈፀሙት ወንጀል ሰለባ የሆኑ፣ በግፍ የተገደሉና በደል የደረሰባቸው በርካታ ዘመዶቻቸው ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡”
በተለይ ይላሉ አና ጎሜዝ፡-
“ሰኔ 8/2005 ዓ/ም (ሰኔ 1/1997 ማለታቸው ነው) በመሃል አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የተፈፀመውን ፍጅት አስታውሳለሁ፡፡ ምናልባት አቶ በረከት አሁን የተያዙት በሙስና ተጠርጥረው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላደረሱት በደል ይጠየቃሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
.
በኢትዮጵያ አሁን የሚታየውን ለውጥ “እጅግ አስደናቂ” ሲሉ ነው የገለፁት አና ጎሜዝ፡፡  በውጪ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡና የሚያምኑበትን በግልፅ እንዲናገሩ መደረጉ “አንዳች ተስፋ” እንዳሳደረባቸውም ገልፀዋል፡፡
.
“በኢትዮጵያ እውነተኛ ምርጫ ይካሄዳል፤ ተቃዋሚዎችም በነፃነት የምርጫ ዘመቻቸውን ማካሄድ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ” ይላሉ፡፡
ይቀጥላሉ ጎሜዝ፣
“ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ፣ ዓለም ሁሉ የሚቀበለው፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1997 ዓ.ም ለትክክለኛ ምርጫ ዝግጅ መሆኑን ያሳየበትን የመሰለ …ምርጫ ይካሄዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ነው ሃሳባቸውን በአፅንኦት የገለፁት፡፡
.
እናም፣-
“በአቶ በረከት ላይ የተወሰደውን የመሰለ እርምጃ፤ ተጠያቂዎችን በሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት አካል በመሆኑ አስደስቶኛል” ሲሉም እርምጃውን አወድሰዋል፡- አና ጎሜዝ፡፡
.
ዘገባው፡- (የጥር 16 ምሽት የየቪኦኤ ነው፡፡)
Filed in: Amharic