>

ይድረስ ለመኢጠማ አባላት በሙሉ - (ላልተወሰነ ጊዜ ቢራና ድራፍት ስለማቆም)

ይድረስ ለመኢጠማ አባላት በሙሉ 

(ላልተወሰነ ጊዜ ቢራና ድራፍት ስለማቆም)

ያው – ይሄም ከወያኔ ሤራዎች አንዱ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ እንጂ በዚህ ጭንቅ ጊዜ ስለሆድ መጻፍ ለትዝብት እንደሚዳርግ ዘንግቼው አይደለም፡፡ የሆኖ ሆኖ ሆድም ከዓለም ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱና ምናልባትም የመጀመሪያው እንደሚሆን በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ሆድና ወሲብ ባይኖሩ ኖሮ በዓለማችን የሚታየው የሥልጣን ፍትጊያም ባልነበረ ወይም ይህንን ያህል ባልተጋነነ፡፡ መብላትና መጠጣት፣ መልበስና ማማር ባይኖሩ ወያኔዎች ራሳቸው አቅላቸውን ስተው ያን ሁሉ ግፍና በደል፣ ዝርፊያና ስርቆት፣ ጄኖሳይድና ዘርን ማጽዳት … ባላከናወኑ፡፡ ስለዚህ ሆድ አጋዳይና አቆራራጭ ሰውንም ወደጭራቅነትና ዐረመኔነት የሚለውጥ ነውና አትታዘቡኝ፡፡

ሰሞኑን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ እጅግ ቀብጧል፡፡ በብርጭቆ ሁለት ብር ለማያወጣበት አንድ ድራፍት ከ20 ብር በላይ እንድንበዘበዝ እያደረገን ነው፡፡ ጭማሬው ደግሞ የብዙዎቻችንን ኪስ ያገናዘበ ሳይሆን ሀብታሞችንና ዘራፊ ሙሰኞችን ለበለጠ ዝርፊያና ሙስና እንዲተጉ እነሱን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው – በቀበሌዎች ሳይቀር አንድ ጃምቦ ድራፍት ከ12 ብር ወደ 15 ብር ከፍ ብሏል፡፡ ደግሞም ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማቀያየም ካልሆነ በስተቀር ለጭማሬው ምንም ዓይነት ተጨባጭ ምክንያት የለም፡፡ የዋጋ ጭማሪዎችን የጊዜ ማዕቀፍ (timing) ስናይ ደግሞ ድርጊቱ በርግጥም የወያኔ ሥራ ለመሆኑ እማኝ አያሻውም፡፡ ወያኔ የለውጡን ባቡር ባለ በሌለ መዶሻ እየቀጠቀጠው ነው፡፡ ባቡሩ ግን ፅኑ ነው!

በኤሌክትሪክና በመጠጥ እንዲሁም በሌሎች የምርትና የአገልግሎቶች ዋጋ ጭማሬዎች ሕዝቡን ማንጫጫትና የቀድሞውን የወያኔ ሥርዓት እንዲናፍቅ ማድረግ ይቻላል ብለው ያሰቡ የወያኔ ርዝራዦች አሁንም ኢኮኖሚውን እንደፈለጋቸው እያሽከረከሩት ነው፤ እነ ዶ/ር አቢይ የሚለፉበትን የለውጥ ሂደትም ለመቀልበስ ቀን ከሌት እየተራወጡ ነው፡፡ ለውጡ ከመጣ ወዲህ የገባንበት የዋጋ ንረት ከበፊተኛው ጋር ሲወዳደር የአሁኑ እጅግ የተሰቀለና አንዳች ዓላማ ያነገበ ለመሆኑ ዋቢ መጥቀስ ሳያስፈልግ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ማኅበራዊ ችግር ያስተዋለው የመንግሥት አካል ደግሞ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም የተያያዘው የዕውር ድምብር ሩጫ ነው፡፡ አስተውሎትና ሚዛናዊነት የሚጎድለው የሚመስለው የሀገር አመራር በአፋጣኝ ካልተስተካከለና ኢኮኖሚው በሁለት እግሩ ቆሞ ዜጎች የተረጋጋ ሕይወት መምራት ካልቻልን ስንረጋገም መኖራችን ነው፡፡ እሳት በማጥፋት የተጠመደው የለውጡ ኃይል የኛን የምሥኪን ዜጎችን ዕለታዊ ሕይወት ሊረዳና ማስተካከያ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ጊዜ አጣ፡፡

ሶቭየት ኅብረት ድንችንና ቮድካን ርካሽ ታደርግ ነበር፡፡ ጃፓን ሩዝን ርካሽ ታደርግ ነበር፡፡ ለሕዝባቸው የሚያስቡ ብዙ ሀገሮች ዜጎቻቸው ለቀን ጅብ ነጋዴዎች ተጋልጠው መፈጠራቸውን እንዳይረግሙ በተለይ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ በተቻላቸው መጠን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የኛዎቹ ግን ከዚህ ተቃራኒ ናቸው፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የራሳቸው ኑሮ ከተመቻቸ ለዜጎች ደንታቢስ ናቸው፡፡ እርግጥ  ነው – ወያኔ ላለፉት 27 ምናምን ዓመታት ብሔራዊ ስሜትንና ሰብኣዊ የመተዛዘን ርህራሄን ለማጥፋት የሠራው ሥራ በዚህ አሁን በምናየው መጨካከን ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ሰዎችን ወደ ሮቦትነት ለውጦ በድን አድርጎናል፡፡ ከዚህ አኳያ ማንም ለማንም ሳይጨነቅ ዋጋን በየቀኑ ማሻቀብ እንደፋሽን ተይዟል፡፡ ተጠቅሞበት ለማይጨርሰው ረብጣ ብር አዳሜ ነፍሱን ስቶ በመተቱም፣ በጥንቆላውም፣ በአንደርቡም፣ በጭዳውም… እየታገዘ፤ በማጭበርበሩም፣ በማምታታቱም፣ በዘረኝነቱም… እየተደገፈ በሁሉም ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ሃይማኖታዊ መንገድ – በ “የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጭው” የሆዳሞች ፈሊጥ እየተነዳ ገንዘብ ማግበስበሱን ተያይዞታል፡፡ የሰሞኑ የዋጋ ጭማሪ ደግሞ የተለዬ ነው፡፡ ኤሌክትሪኩ ተሰቅሏል፡፡ እህሉም ሆነ ሸቀጡ ሰማይ ደርሷል፡፡ የቤት ኪራዩ ተሰቅሏል፡፡ ትራንስፖርቱ ተሰቅሏል፡፡ ግብሩና ቀረጡ ተሰቅሏል፡፡ የሆቴል ቤት ምግብና መጠጡ ለኔ ቢጤ ድሃው አይቀመስም – ሽቅብ ንሯል፡፡ ሳይሰቅሉት የቀረ ነገር የለም፡፡ እኛን በገመድ ማንጠልጠል ብቻ ነው የቀራቸው፡፡ ቢመቻቸው ይህንንም ያደርጉታል- ሲያደርጉት ነበርና፡፡ ሀገርና ዜጋ ጭንቅ ላይ ናቸው፡፡ ጥቂት ሀብታሞች ከተሞችን ቀን ከሌት በሙዚቃ ድልቂያ እሽቅንድር እያሉ ስለዋሉና ስላደሩ ብቻ ብዙኃኑም አልፎለታል ማለት የቂልነት ቁንጮ ነው፡፡ በመንግሥቱ ለማ አገላለጽ ሕይወት የሌለበት የተንጣለለ አስፋልትና የተገተረ ሕንፃ ቢበዛ በመቶ ሽዎች የሚገመቱ ጎዳና ተዳዳሪዎችን የያዘች ብልጭልጭ ከተማ ገመናዋን ልትሸፍንበት አንድም የረባ ጅራት አይኖራትም፡፡ ያለች የምትመሰል ግን የሌለች ሀገር ባለቤት መሆን ደግሞ አያኮራም፡፡ አውሮፓ የማይታይ ዘመናዊ መኪና አዲስ አበባና መቀሌ ላይ ቢርመሰመስ የገንዘብ ሀብታምነት የፈጠረውን ድንቁርናችንን እንጂ በአእምሮም ጭምር ባለፀጋ መሆናችንን አያመለክትም፡፡ ጠፍተናል !

ይባስ ብለው ማታ ማታ መቆዘሚያችንን፣ ብሶት መተንፈሻችንንን፣ እርስ በርስ መወያያችንን ድራፍትና ቢራ ሰሞኑን ሰቀሉት – ያባቴ አምላክ ይስቀላቸውና፡፡ “ድሃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ የወይን ጠጅ ስጡት” የተባለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ረሱት፡፡

ስለዚህ ውድ የመኢጠማ አባላት በሙሉ (መላው የኢትዮጵያ ጠጭዎች ማኅበር ማለቴ ነው) ላልተወሰነ ጊዜ መጠጥ እንድናቆም  እኔ ወንድማችሁና የድርጅታችሁ ነባር አባል በታላቅ ትኅትና እጠይቃለሁ፡፡ ይህን ብናደርግ አንሞትም፡፡ በጣም ተደፍረናል፣ ተንቀናልም፡፡ እንዴ?

ለ15 ቀናት እንኳን ብናቆም ታያላችሁ ያወርዱታል፡፡ በኛ ሀገር በዚህ መልክ መብትን ማስጠበቅ ዕርም ሆኖ እንጂ ይህ መንገድ በቀላሉ መብትን ያስከብራል፡፡ ነገር ግን “ልታይ ልታይ” የሚለውና “ገንዘቤን የት ልጣለው?” የሚለው ወገን አንድ ነገር ዋጋው ሲጨምር በእልህ ወይም በሀብት ብዛት ከሰው በመለየቱ በመደሰት ያን ዋጋው የጨመረን ዕቃ/አግልግሎት የሚጠቀም ሰው ይበዛል፡፡ በዚያ ላይ ዕውቀታችን ወርዷል፡፡ አንድነታችን ላልቷል፡፡ መግባባታችን ጠፍቷል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እየተንጠላጠለ የሚደረገው ሽቅብ ጉዞ ገኗል፡፡ ሀገራችን አሁን ሰው ሰው አትሸትም፡፡ ግዑዝ እየሆነች ነው፡፡ የአንድና የሁለት ሰዎች ጥረት ደግሞ ብዙም አያራምደንም፡፡ መቶ ሚሊዮን በረዶ ውስጥ በጣ የሚቆሩ ጥቂት ሻማዎች ምንድን ናቸው? በቦሌም በባሌም የሚገባው ፖለቲከኛ ሲታይ አብዛኛው ቢከፍቱ ተልባ እየሆነ የት እንዳለንና ወዴትም እየሄድን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግረናል፡፡ ሰው እንዴት ወደኋላ ይሮጣል? ባለንበት መሄድም አቃተን፡፡ ሳቢውን እየገረፍን እስከመቼ የደናቁርት ዋሻ ሆነን እንደምንኖርም  አንድዬ ይወቅ፡፡

ለማንኛውም መንግሥት ይህን ሥውር የወያኔ ተግባር ሃይ ቢለው መልካም ነው፡፡ ቀን ቀን የሚገነባውን ሁሉ ማታ ማታ የሚያፈርሱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ የመሸጉ ወያኔ ነጋዴዎችና የመንግሥት ቴክኖክራቶች ሞልተዋልና አደብ እንዲገዙ ይደረግ፡፡ ከታች እያረረ ከላይ ያማረ ቢመስል በጊዜ ሂደት ሁሉም ማረሩ አይቀርም፡፡ ይህን መሰሉን አሻጥር እየመረመረ መፍትሔ እንዲሰጥ ሥልጣን የሚሰጠው ወይም ለበላይ አካል የመፍትሔ ሃሳብ የሚያቀርብ ሀገራዊ ኮሚቴ ቢቋቋምም አይከፋም፡፡ አብሮን ያለን አስመሳይ በጊዜው ካላወቅን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ መቀሌ የመሸገው ኃይል “አንዲት ጥይትና አንድ ዛፍ እስኪቀረው” ድረስ እጁ እጅግ ረጂም ነውና አሁንም በእጅ አዙር በተለይ ኢኮኖሚውንና ቢሮክራሲውን ተቆጣጥሮታል፡፡ በሙስና የበከተውና በዘረኝነት የከረፋው ቢሮክራሲ የሚተጋው ለሀገርና ለሕዝብ ሳይሆን ቀድሞ ለተካነበት ወያኔያዊ የመድሎ አሠራር ነውና ይህ ነገር ካልታሰበበት አይበልብን እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፍ ጢማችን መደፋታችን አይቀርም፡፡ የመኢጠማ አባላት ግን መነሻ ሃሳቤን አትርሱብኝ፤ አደራ፡፡

ከልደታ እስከባታ ለመኖር ከሚፍጨረጨሩ የኗሪ አኗኗሪ ዜጎች አንዱ – ከአዲስ አበባ

Filed in: Amharic