>
5:13 pm - Saturday April 20, 8346

ከጀርመን አምባሳደርነት የእስር ቤት ካቦነትን የመረጡት እብሪተኛው ሰው!!! (አብርሀ በላይ)

ከጀርመን አምባሳደርነት የእስር ቤት ካቦነትን የመረጡት እብሪተኛው ሰው!!!
አብርሀ በላይ
በረከት ስምዖን ገና ከጥንስሱ የመለስ ቀኝ እጅ ነበር ማለት ይቻላል። የመለስ የሚስጥር ተካፋይ መሆኑን አንዲት አጋጣሚ እንጥቀስ። መለስ በህወሃት ውስጥ በተነሳው ቀውስ አገሪቱ ውጥረት ላይ ነች። ስልጣኑ እንዳይነጠቅ፣ ስልጣን ነጣቂ ያለ ይመስል፣ መለስ፣ በረከት እና ቃፊሮቻቸው እንቅልፍ አተው እያሴሩ ናቸው። በዚሁም መንፈስ፣ መለስ የቀድሞ የደህንነት ሹሙ ክንፈ ገ/መድህን እንዲገደል ወስኗል። ሻለቃ ፀሀዬ ወ/ስላሴ በተሰጠው ትእዛዝ ክንፈን ገደለ። የክንፈ ቦታ ለመውሰድ ቃል የተገባለት ጌታቸው አሰፋ ግድያው በተሳካ ውጤት መጠናቀቁ ለጌታው ለመግለጽ ከመኮንኖች ክለብ ወደ ቤተ-መንግስት ጥቂት የደህንነት ሰዎችን አስከትሎ በረረ። በአንድ ክፍል መለስ እና በረከት ከ11 የማይበልጡ  ሰዎችን ይዘው ዝግ ስብሰባ ይመሩ ነበር። ጌታቸው አሰፋ ገባና በመለስና በበረከት መሀል ጎንበስ ብሎ “ጉዳዩ” እንደተፈጸመ ነገረው። መለስም “ጥሩ፣ በል አሁን ቀጣዩን ስራ ደግሞ ሂደበት” የሚል መልእክት የሚነበብበት ፊት ሰጠው። ጌታቸው ወደ ቀጣዩ ስራ – ወደ ክንፈ ጽ/ቤት እና መኖሪያ ቤት በመሄድ – ያለ የሌለ ዶክመንት እና ኮምፒተሮች አስጭኖ መለስ ጽ/ቤት ወስዶ አስረከበ። (ከቀደሞ የደህንነት ሰራተኛ የተሰጠ ምስክርነት)…
እዚህ ላይ ግድያው ቢጎላም፣ ከግድያው የበለጠ ግን መለስ እና በረከት ቤተ-መንግስት ውስጥ በሚስጥር ይመሩት የነበረውን ዝግ ስብሰባ ጉዳይ ነው። በረከት ሌላውን ግራ ለማጋባት ወረቀት ላይ ተራ የኮሚኒኬሽን ሚኒስተር ይባል እንጂ ወሳኝ በሚባሉ ከፍተኛ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የመለስ ቀኝ እጅ ሆኖ እንደኖረ ይመሰክራል። በረከት ስልጣኑ ገደብ አልነበረውም። በመሰለው ሁሉ ገብቶ  ትእዛዝ ያስተላልፋል። ሰዉ ካላበደ፣ የፍርድ ቤትም ትእዛዝ ቢሆን ተሰርዞ፣ በረከት ባለው መንገድ ይፈጸማል። ባለስልጣናትም ሳይቀሩ፣ በሱ ትእዛዝ ይታሰራሉ፣ ፍርድ/ቤት ያሰራቸውም በበረከት ትእዛዝ ይፈታሉ።
አማራውና ኦሮሞው በማያባራ ግጭት እንዲዘፈቁ ተፈልጎ የታተመው “የቡርቃ ዝምታ” መጽሐፍ ተስፋዬ ገ/አብ ይጻፈው እንጂ፣ ዋና መሃንዲሶቹ መለሰ እና በረከት እንደሆኑ የደህንነት ምንጮች ይናገራሉ።
ዲፕሎማቶች በረከትን እንደ ጦር ይፈሩታል
የአ.አ. ዲፖሎማቲክ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ ትንፍሽ እንዳይሉ ደጋግሞ በማሸበር፣ የጠረጠራቸውን ዲፕሎማቶችና የውጭ ጋዜጠኞችን በማባረር ከመለስ ቀጥሎ እንደተፈራ ኖሯል። የተለያዩ የውጭ ሚድያ ተቋማት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን አወዳድረው ለመቅጠር ቢጠይቁም፣ በበረከት ማስጠንቀቅያ ግን እሱ ራሱ የመለመላቸው ካድሬዎች በሮይተርስ፣ በዶቼ ቨለ፣ ኤ ፒ እና ቪ ኦ ኤ አማርኛ፣ ትግርኛ እና ኦሮሞኛ ተመድበው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት ሳይሆን የነ በረከት የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሰሩና በረቀቀ ዜዴ የህዝቡን ተጋድሎ ሲያሽመደምዱ ኑረዋል።
ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል!
ቅንጅት የ97ቱን ምርጫ ማሸነፍ ተከትሎ በተካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያ በአቀናባሪነት፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መለስን ወግኖ የኢትዮጵያ ወታደራዊ የበላይነት እንዳይኖር ሴራ በማቀነባበር እና በማክሸፍ እና በሌሎች ኢትዮጵያን በሚያዳክሙ ወንጀሎች ሁሉ እጁ ያለበት በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል የማይባሉ አሰቃቂ ወንጀሎችን ከደህንነት ጓዶቹ ጋር ሆኖ ሲፈጽም የነበረ ፍጡር ነው።
ፈገግ የሚያሰኝ ነገርም አለው
ጠ/ሚ አብይ በረከትን ጠርተው በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ልሾምህ ነው ሲሉት – እሱና መለስ በአምባሳደርነት ይልኳቸው የነበሩት ሰዎች ትናንሽ ካድሬዎቻቸው ስለነበሩ እሱም ወግ ደርሶት “እኔን አይመጥንም” በሚል እሳቤ፣ “ውጭ ህጄ መኖሩ አይመቸኝም” ብሎ ሲናገር የሰማነው ሁሉ ፈገግ አስኝቶናል። በረከት የተማመነው ሌላ ሳይሆን መራሹ ህወሃት “ዳግማይ ትንሳኤውን” ያሳየኛል! ከመቀሌ ዘመቻ-ወ-አራት-ኪሎ አይቀርም፣ እኔም በክብሬ እዚሁ አዲስ አበባ ሁኜ የደደቢት ጓዶቼ ሲገቡ፣ እቅፍ አበባ ይዤ እቀበላቸዋለሁ” ከሚል ህልም ነበር።
የበረከት ቆንጆ ህልም ግን ሳይውል ሳያድር ወደ መጥፎ ቅዥት ተቀይሮ ከግብረ-አብሩ ከታደሰ ጥንቅሹ ጋር ዘብጥያ ወረዱ። ያውም በባህር ዳር!
ከዚሁ ሳልወጣ:- አቶ በረከት በፎቶው እንደምታዩት ለስንት ንጹሀን እስረኞች የከለከለውን በቤተሰብ የመጎብኘት መብት ተጎናጽፏል – ለውጥማ አለ!
 
ፍትህ ፈላጊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፣ እንኳን ደስ ያለን!
Filed in: Amharic