በውቀቱ ስዩም
ባገራችን የነገስታት መታሰቢያ ሀውልት ማቆም: በጀግና ተዋጊዎች ስም ጎዳናዎችንና ትምርትቤቶችን መሰየም የተለመደ ነው:: አገሩ በሙሉ በጦርና ጋሻ ምልክት የተሞላ ቢሆንም አሁንም በወታደሮች: በጌቶችና በእመቤቶች ስም ሀውልት የማቆም ግፊቶች ቀጥለዋል :: በፖለቲካው ግርግር መሀል: ለህዝብ መንፈሳዊ እና አእምሮአዊ እድገት መዋጮ ያደረጉ ሰዎች ተዘንግተዋል::
ለምሳሌ ዛሬ ድረስ ላዝማሪ ሀውልት ማቆም ተስኖናል:: ግን አዝማሪዎች ባይኖሩ ጀግኖች አይኖሩም:: ባልቻ ሳፎን የምናስታውሳቸው ወይዘሮ ፃድቄንና ሀሰን አማኑን የመሳሰሉ አዝማሪዎች ገድላቸውን እንዳንረሳቸው አድርገው ስለዘመሩልን አይደለምን? ከባልቻ ያልተናነሰ ጀብድ የፈፀሙ ጀግኖች አዝማሪ አይንና ቀልብ ስላልረፈባቸው ተዘንግተው ቀርተዋል:: ያጋነንሁ ከመሰላችሁ ይበልጥ ሞቅ ላርገው!! አዝማሪ የሌለው ህዝብ ትውስታ የለውም::
ቀደምቶቻችን ቤተ -እምነት እንጂ ቤተ-ሙከራ ገንብተው አላወረሱንም:: በዚህ ምክንያት አገሩ የሳይንስና ምርምር ምድረበዳ ሆኖ ቆይቷል: : በድሃ አቅማችን: ወደ ጨረቃ መንኮራኩር መላክ ብናስብ ቅብጠት ይሆናል:: ወደ ጨረቃ ዙሮ መሽናት ቂጥኝ ያስይዛል ብሎ የሚያምን ትውልድ እንዳይኖር ለማድረግ ራሱ ብዙ ይቀረናል:: ባለምአቀፍ ደረጃ ለሳይንስ መዋጮ ያደረጉ ሊቃውንታችን ብሄራዊ ጀግኖች አድርጎ ማስተዋወቅ አንዱ መፍትሔ ነው ብየ አስባለሁ::
“የጋቢሳ እጄታ ጎዳና ” : የ አክሊሉ ለማ መታሰቢያ : አየር ማረፍያ : “የ ተወልደ ገብረእግዚያብሄር ፓርክ ” ማየት እመኛለሁ:: አገርን ዳርድንበር ከጠላት የሚከላከልንን ብቻ ሳይሆን ከጠንቀኛ ባክቴርያና ቫይረስ የሚከላከለንን ማጀገን ይጠብበቅብናል::
ለዘር ማንዘርህ ብቻ መዋደቅ እርፍና በሆነበት አገር : ሰው ሳይመርጡ ሰው የሚያገለግሉ ሰዎች የጀግና መታሰቢያ ያስፈልጋቸዋል:: “የጀግነት ሁሉ አባት ፍቅር ነው” ይል ነበር ይድነቃቸው ተሰማ:: የሜቄዶኒያውን ቢኒያምና አበበች ጎበናን የመሳሰሉትን በጎ አድራጊዎች ሳስብ ትዝ የሚለኝ ይህ አባባል ነው::
ወዘተረፈ..
ባገራችን ከጥንት እስከዛሬ የጀግንነት ትርጓሜ ከጦርነት አልወጣም:: ምናልባት የጀግነትን ትርጉም ስንቀይር ያለንበት ሁኔታ ይቀየር ይሆን?