>

“አገራችን የተረጋጋ የለውጥ ጎዳና ላይ ገብታለች ለማለት ያስቸግራል!!!” (ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ - በኢትዮጲስ)

አገራችን የተረጋጋ የለውጥ ጎዳና ላይ ገብታለች ለማለት ያስቸግራል!!!
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
 
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ አመራርነት ለረዥም ጊዜ የቆዩና  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁር ናቸው፡፡  በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበርና የመድረክም ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ የዚህ ሳምንት የኢትዮጲስ እንግዳ ናቸው፡፡
 
ኢትዮጲስ፡- ሁሉን ዓቀፍ የሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይቶች ተካሂዷል፡፡ እንዴት ተመለከቱት?
ፕ/ር በየነ፡-  በውይይቱ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሰባሰቡ የተቀመጠው አቅጣጫ መደገፍ ያለበት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሙከራ ሳይደረግ ቀርቶ አይደለም፤ በተደጋጋሚ ተሞክሯል፤ ምናልባት አሁን ተሰባሰቡ፣ ተዋሀዱ የሚለውን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ደጋግመው ስለሚገፋፉ የረባ ፓርቲ ይወጣው እንደሆነ በሂደት የምናየው ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ስንለፋበት የቆየነው ጉዳይ ነው፡፡ መሰባሰብ ከባድ ነገር ነው፡፡ ግንባር፣ ውህደት ማለቱ ቀላል ነው፡፡ ጅማሮው ጥሩ ነው፤ በእኔ ልምድ ግን ሄዶ፣ ሄዶ ፈብረክ ማለት አለ፡፡ ፓርቲዎች ሊዋሀዱ ሲፈልጉ፣ አንደኛውን ሌላኛውን በበላይነት ሊውጥ ነው የሚል የሚሉ ስጋቶች እንዳሉ አውቃለሁ ፡፡
ኢትዮጲስ፡- የምርጫው ሥርዓት ዋነኛ ችግር ምንድን ነው?
ፕ/ር በየነ፡-  ችግራችን የምርጫ ቦርድ ብቻ አይደለም፡፡ እስከ ታችኛው ድምጽ መስጫ ድረስ ያለው የምርጫ ስርዓት፣ በኢህአዴግ ካድሬዎች የተሞላ ነው፡፡ አሁን ያለነው ደግሞ ኢህአዴግ ባልከሰመበት ወቅት ነው፡፡ በእርግጥ፣ አመራሩ አንዳንድ ለውጥ እያደረገ ባለበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡በሚቀጥለውም ምርጫ ቢሆን፣ ኢህአዴግ በአሸናፊነት ወጥቶ መገኘቱ ለካድሬዎቹ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፤ ብዙ ስልጣን አላቸው፡፡ በዚህ እሳቤ ኢህአዴግ ምርጫውን አሸንፎ እንዲወጣ ይፈልጋሉ፣ ከዛም እንደሚጠቀሙ ስለሚያውቁ ያስቸግራሉ፡፡ ስለዚህ፣ ከላይ ያለው የመንግስት አካል በጎ አሳብ ብቻ በቂ አይደለም፤ ታች ድረስ መሰራት አለበት፡፡ 
የመንግስት ሥራ  ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ባልተያያዘ መልኩ እንዲከናወን  ነው የምንፈልገው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት  ለመደራደር ጥረት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ የድርድሩ ጥረት ምን ያህል ተሳክቶልን ነጻ፣ ተአማኒና ፍትሀዊ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል? የሚለውን ገና አላየንም፡፡ ይሄንን እውን ለማድረግ መልካም ምኞት እንዳለ እናያለን፡፡ መሬት ላይ  ወርዶ የሚቀጥለው ምርጫ ስኬት ይሆናል ወይ? የሚለውን ለመተንበይ ያስቸግራል፡፡ ሂደት ላይ ነው ያለነው፡፡ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ 
ኢትዮጲስ፡- የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በምን አቋም ላይ ይገኛሉ? ጠንካራ ናቸው ማለት ይቻላል? 
ፕ/ር በየነ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥንካሬ የሚለካው በምረጡኝ ቅስቀሳ ተንቀሳቅሰው፣ ደጋፊ አሰባስበው፣ ወደ ምርጫ ሄደው በሚያስመዘግቡት ውጤት ነው፡፡ ከምርጫ በፊት፣ አንድ ፓርቲ በሰፊው ወደ ሕዝብ ገብቷል ወይ? ለማለት የሚቻለው ለምሳሌ፣ የት የት አካባቢ ጽ/ቤት ከፍቶ፣ በየቦታው ኮሚቴዎች አስመርጦ እየተንቀሳቀሰ ነው? የሚለው አንዱ መለኪያ ነው፡፡ ያ ደግሞ ከገንዘብ አቅም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በነበረው የፖለቲካ ምህዳር ዝግነት ማንኛውንም ፓርቲ እንደልቡ መንቀሳቀስ ስላልቻለ መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ጠንካራና ደካማ ፓርቲ ብሎ ለመፈረጅ ከባድ ነው፡፡ እኛ የምንለው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠሩን መጀመሪያ እንይና፣ ከዛ በኋላ ስለድክመትና ጥንካሬ ብናወራ ነው የሚሻለው፡፡ 
ኢትዮጲስ፡- ኢህአዴግ ከልብ ተለውጧል ብለው ያምናሉ ወይ?
ፕ/ር በየነ፡- ብዙ ለውጦችን ከላይ ከላይ እያየን ነው፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቀይረዋል፤ ከዚህ ጋር በተገናኙ ብዙ ውይይቶች ይካሄዳሉ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ተስፋ የሚያለመልሙ ንግግሮች ያደርጋሉ፤ እስረኞችን መፍታት፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፣ የተለያዩ ሕጎችን ለማስተካከል ኮሚቴዎች አቋቁሞ መንቀሳቀስ፣ እነዚህ እነዚህ ሁሉ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ናቸው፡፡ ግን፣ ሰው በሚመኘውና በሚፈልገው ደረጃ የደረስንበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለነው፡፡ 
ሌላው የባለስልጣኖችን ለውጥ የምናየው በማዕከሉ ላይ ነው፡፡ ወደ ታች ስንወርድ ግን የኢህአዴግ መዋቅር እንዳለ ነው ያለው፡፡ አንድ ወረዳ ውስጥ ችግር የፈጠረው ወደ ሌላ ወረዳ ይቀየራል፤ የስራው ዓይነት ቀየር ተደርጎ ይሾማል፡፡ ክልል ውስጥ ስንቱን ሕዝብ ሲያስለቅስ የኖረው ይነሳና እዚህ አዲስ አበባ መጥቶ ይሾማል፤ አንዳንዶቹን በቴሌቪዥን ብቅ ሲሉ እናያቸዋለን፡፡ ተገልጋዩ ሕዝብ ያለው ታች ነው፡፡ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ባላገሩ ነው፤ በገጠር ያለው የኢህአዴግ መዋቅር አልተነካም፡፡ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲኖር በገጠሩም ለውጥ መኖር አለበት፡፡ 
በአገሪቷ የምንፈልገው ዓይነት መረጋጋት ኖሮ፣ ሕዝባችን በሰላም ከቤቱ ወጥቶ እየገባ አይደለም፡፡ በአንዳንድ አካባቢ የመንግስት አስተዳደር መዋቅር ፈርሶ ሌሎች ናቸው እንደፈለጉ የሚያዙት፤ እንደፈለጉ መንገድ ላይ መኪና አስቁመው “ገንዘብ አምጣ” ይባላል፤ ድብልቅልቅ ዓይነት ነገር ነው ያለው፡፡ ከላይ ከላይ ተስፋዎች አሉ፤ እላይ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የተንኮል አካሄድ አላይባቸውም፤ “ያ ባለስልጣን እንዲህ አደረገ፣ የተንኮል ስራ ሰራ፣ የጭካኔ ተግባር ፈጸመ” የሚል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ነገር ውስብስብ ነው፡፡ ግጭቱም፣ መፈናቀሉም፣ ሞቱም ከታች አለ፡፡ አፍ ሞልተን አገራችን በምንፈልገው የተረጋጋ የለውጥ ጎዳና ላይ ሙሉ ለሙሉ ገብታለች ለማለት ያስቸግራል፡፡
ኢትዮጲስ፡- በሜቴክና ደህንነት ኃላፊዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ነው የሚል አስተያየት አለ፤ እንዴት አዩት?
ፕ/ር በየነ፡- በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ በምትተዳደር ሀገር ውስጥ ማንኛቸውም ተጠርጣሪ ህግ ፊት መቅረብ አለበት፡፡ ይሄ የአንድ የሰለጠነና በሕግ የሚተዳደር አገር አካሄድ ነው፡፡  እነዚህ ሰዎች በቂ ጥርጣሬ ቢኖር ነው የሚያዙት፡፡ ‹‹ጭስ ባለበት እሳት አይጠፋም›› እንደሚባለው፣ ትንሽ ጥርጣሬ አለ፡፡  “መርምረን፣ አጣርተን ነጻ ከሆነ እንለቀዋለን” የሚል ጤነኛና ሕጋዊ አካሄድ ያለ ይመስለኛል፡፡ 
በዚህ ሂደት ሚዲያው በመረጃ ስም የሚያቀርባቸውን ነገሮች እናያለን፡፡ የዚህን አግባብነት የሕግ ሰዎች መፈተሽ አለባቸው፤ እኔ ስጋት አለኝ ፡፡ መረጃ ካላቸው ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡ “አሁን እየተቀየርኩ ነው” የሚለው ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞም የነበረውም፣ “መረጃ ነው” የተባለው ነገር ቀደም ብሎ ለሕዝቡ ይፋ ይደረግና፣ ከዛ በኋላ “ሰዎቹን ከሰናል” የሚሉት ነገር አለ፡፡ ይሄ ከየት የመጣ አሰራር እንደሆነ አይገባኝም፡፡ አንድ ሰው ሊጠረጠር ይችላል፣ ግን እስከሚፈረድበት ጊዜ ድረስ ነጻ ነው፡፡ ይሄ የፍትህ ስርዓት መርህ ነው፡፡ ልትጠረጠር ትችላለህ፣ ግን እስከሚፈረድብህ ድረስ ነጻ ነህ፤ ይሄ መከበር አለበት፡፡ ዳኞች በሚዲያ የተዘገበው ነገር ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል፡፡ የሰውን ልጅ ሕግ ብቻ ነው ሊዳኘው የሚገባው፡፡ 
በአንድ ብሄር ላይ ነው ያነጣጠረው የሚባለው፣ በብዛት ኃላፊነቱን የያዙት ሰዎች የሚናገሩት ቋንቋ ተመሳሳይ ስለነበርና የተያዙትም እነሱ ስለሆኑ ይመስለኛል ይሄ ትርጉም እንዲሰጠው ያደረገው፡፡ በስፋት ስልጣን ላይ የነሩት  እነሱ ከነበሩ ምን ይደረግ? በኃላፊነት ላይ ያልነበረው አይጠየቀም፡፡  “እኛ ላይ ብቻ ጥቃት ተፈጸመ” ከማለት ይልቅ፣ ሌሎችም አሉ ብለው ካመኑ፣ “እነ እከሌ አሉ” ብሎ መጠቆም ነው ያለባቸው፡፡  ስለዚህ ይሄንን በትክክለኛው ማዕቀፍ ውስጥ ማየቱ ነው የሚሻለው፡፡ ከስሜታዊነት ውጭ ማለት ነው፡፡
በእኔ አመለካከት፣ ከኢህአዴግ አመራሮች የኦሮሞም፣ የአማራም፣ የደቡብም “ከደሙ ነጻ ነኝ” የሚል አንድም የለም፡፡ ሁሉም ተነክረውበታል፡፡ አንዱን ከአንዱ ማበላለጥ የሚለው ነገር ጨርሶ አይዋጥልኝም፡፡ ስለዚህ፣ እንደ ጲላጦስ እጅን ታጥቦ “እነ እከሌ ነጻ ናችሁ፣ እነ እከሌ ወንጀለኛ ናችሁ” የሚለው ነገር አያስኬድም፡፡ ሕዝብ ያውቃቸዋል፡፡  
ከአራቱ የኢህአዴግ ፓርቲዎች ውስጥ ሶስቱ ነጻ ነን ለማለት አይችሉም፡፡ በየክልሉ ሲያሰቃዩ፣ ሲያፈናቅሉ፣ ከክልሌ ውጣ የሚል ትዛዝ ሲሰጡ የነበሩ አይደሉም እንዴ? መጠየቅ ያለባቸው የየክልሉ የኢህአዴግ መሪዎች አሉ፡፡ በተለይ የኢህአዴግ የክልል አመራር የነበሩት አብዛኛዎቹ ሊፈተሹ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ስማቸው በሕዝብ ይጠራል፤ ለምንድን ነው የሕዝብ ጥቆማ የማይሰማው? 
ኢትዮጲስ፡- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የትግራይ ክልል አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፌ አልሰጥም ማለቱን ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል፤ ምን መደረግ አለበት?
ፕ/ር በየነ፡- እኔ እንግዲህ የሕገ-መንግስቱን ይዘት እስከማውቀው ድረስ፣ የክልሉ መንግስት ሕገ-መንግስቱን የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ የፌደራል መንግስት፣ “ክሱ የፌደራል ጉዳይ ስለሆነ፣ ይሄንን እንዲህ አድርጉ” የማለት ስልጣን አለው፡፡ ከዛ አልፎ ግን፣ “በከለከላችሁ ጦር ይዤ ገብቼ እከሌን አስገድጄ እይዛለሁ” የሚል አሰራር ግን የለም፡፡ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ሲደርስ፣ በፌደራል መንግስቱና በክልሉ መንግስት መካከል ድርድር ይካሄዳል ብዬ ነው የማስበው፡፡  በክልሉና በፌደራል መካከል የሰከነ ውይይት መደረግ አለበት፡፡
ኢትዮጲስ፡- በኦዲፓና በኦነግ መካከል አለመግባባቶች አሉ፤ እንዴት ያዩታል?
ፕ/ር በየነ፡- እኔ የሰላማዊ ፖለቲከኛ አራማጅ ነኝ፡፡ አላማዬን በጉልበት የማስከበር አጀንዳ ይዤ አላውቅም፤ ወደፊትም የማልይዝ ሰው ነኝ፡፡ የጠራኸው ድርጅት ወደ አገር ቤት ገብቶ በይፋ እንቅስቃሴውን እንዲያደርግ የጋበዘው መንግስት ነው፡፡ ረጅም መንገድም ተሂዶ እንደተጋበዘም አይተናል፡፡ ይሄ ነገር እንዴት ተቀይሮ  ወደ ግጭት እንደወሰዳቸው አይገባኝም፡፡ 
ኦዴፓ የሚባል አንድ የኢህአዴግ ድርጅት እኮ የራሱ ሰራዊት የለውም፣  ጉዳዩ ከፌደራል መንግስት ጋር ነው የሚሆነው፡፡ ጉዳዩ የኦነግና የኦዴፓ ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡ የክልሉም ጉዳይ ሳይሆን የፌደራል ጉዳይ ነው፡፡  ምህዳሩ ክፍት ነው፣ “ገብታችሁ በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቀሱ” የተባለው፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ፣ ምንድን ነው እንዲመለስላቸው የሚፈልጉት? የሚለውን ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ምንድን ነው? የሚለውን አውቆ፣ በዛው በፖለቲካው አግባብ መልስ የሚሰጥበት፤ የሰጥቶ መቀበል ድርድር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፤ ለሰላምና መረጋጋቱ ሲባል ማለት ነው፡፡  ወደ ጉልበት ከተሄደ ሕዝቡ ይጎዳል፡፡ ለምን እንደሚጋጩና እንደሚታኮሱ ያልገባው ሕዝብ ይጎዳል፡፡ “ዓላማ አለኝ” የሚለው ሁሉ የሕዝብን ጥቅምና ሰላም አስቀድሞ መገኘት አለበት፡፡
 
ኢትዮጲስ፡- አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ እንዴት አዩት? 
ፕ/ር በየነ፡- ፍኖተ ካርታ የተባለውን በዝርዝር ለማየት ዕድል የተሰጠኝ ሰው አይደለሁም፡፡ የኋላ ታሪኬን መለስ ብዬ ሳይ፣ የደርግ ስርዓት ወድቆ ከኢህአዴግ ጋር በሽግግሩ መንግስት አብረን ስንሰራ፣ እኔ በትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴርነት “የትምህርቱን ስርዓት መልሶ ለማቋቋም” በሚል ለሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የተደመሰሱትን ትምህርት ቤቶች መልሶ ማቋቋም፣ የትምህርት ስርዓቱንም ማሻሻል የሚል ኃላፊነት ነበር የተሰጠኝ፡፡ ከሞላ ጎደል፣ መልሶ ማቋቋሙንና ግንባታውን በሁሉም ክልል ለማስተካከል ተችሏል ፡፡ ትምህርት ቤት በሌላቸው የዘላኑ አካባቢም አዳሪ ትምህርት ቤት የማቋቋም ስራ ተሰርቷል፡፡
በሌላም በኩል፣ “የትምህርቱን ስርዓት እንደገና ማቀናጀት፤ የትምህርት ሥርዓቱን እንደገና መፈተሽ” የሚለውን ኃላፊነት ተሰጥቶኝ፣ ባለሙያዎቹን በማስተባበር ለመስራት የሞከርኩ ሰው ነኝ፡፡ ነገር ግን፣ ወደ መሀሉ ገደማ ኢህአዴግ ጣልቃ ገባና፣ ‹‹የትምህርት ሥርዓቱን መገምገም በራሱ በትምህርት ሚኒስቴር ሊሰራ አይችልም፣ እኛ ነን የምንገመግመው›› ብለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ከእኛ ነጥቆ ወሰደው፤ ለስድስት ወር ያህል የሰራነውን ስራ ነጠቁን፡፡ እኔ ያኔም በሽግግር መንግስቱ ውስጥ የነበርኩት በተቃዋሚነትም ነበር፡፡ በወቅቱ ጥምር መንግስት ነው የነበረው፡፡ “በበየነ እጅ አንተወውም” በሚል ስጋት ነው መሰለኝ የወሰዱት፡፡ ዶክተር ታደሰ ከበደ የሚባሉ ነበሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የማህበራዊ ዘርፍ  ሚኒስቴር ነበሩ፤ ትእዛዙ የመጣው ከሳቸው ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ፍኖተ ካርታ ብለው አስጠናን ማለት ጀመሩ፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ የኔ የትዝብት ነጥብ፣ ይሄንን እያሉ ባሉበት ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ንግግር ያደረጉ ቀን፣ ከሶስት ሺ በላይ ተወካይ መምህራኖች በተገኙበት ስብሰባ ላይ እኔም የመጠራት እድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ መምህራኑ በድርጅታዊ መዋቅር የመጡ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ሁሉም “ድርጅቴ በላከኝ መሰረት” እያለ ተጽፎ የተሰጠውን ነበር ሲያነብ የነበረው፡፡ ሁሉም ብሶት ነው ያቀረበው፤ በዚህ በዚህ መልኩ ይሻሻል የሚል አሳብ አልነበረም፡፡
ሻይ እረፍት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔን ወደ ጎን አስጠርተው አነጋገሩኝ፡፡ ትምህርት ሚኒስትሩም፣ ምክትሎቹም ነበሩ፣ በእነሱ ፊት ‹‹ይሄንን እናንተ የጀመራችሁትን ፍኖተ ካርታ እነ ዶክተር በየነ ማየት አለባቸው፤ ያኔ ትምህርት ሚኒስቴር ለነበሩት ሁሉ ስጧቸውና የነሱን ግብአት መጨመር አለባችሁ›› አሉ፡፡ ነገር ግን አላሳተፉኝም፡፡ አንድ ቀን ሚኒስተር ዲኤታው ደውሎ አናገረኝ፣ የምንወያይበት ቦታና ቀን መቼ ነው ብዬ እየጠበኩ እያለሁ፤ መጨረሻ ላይ የትምህርት ፍኖተ ካርታውን ተነጋግረው ተጠናቀቀ የሚል በቴሌቪዥን ሰማሁ፡፡ ለምን ማግለል እንደሚፈልጉ አላውቅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እነ በየነ አይተው መተቸት አለባቸው” ካሉ በኋላም፣ አላሳትፍ ማለታቸው በጣም ገርሞኛል፡፡  እንደትዝብት ነጥብ አድርጌ ትቼዋለሁ፡፡ ስለዚህ፣ በጥልቀት ለማየትና አስተያየትም ለመስጠት እድሉ አልተሰጠኝም፡፡ እድሉ ቢኖረኝ ጥራት ላይ ነው ላነሳ የምፈልገው፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ እንደ ኢትዮጲያ ላለ ደሀ ሀገር ከአርባ በላይ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ የከፍተኛ ትምህርት መሰረታዊ ነገሩ ጥራት ነው፡፡ ዝም ብሎ ቁጥር አይደለም፡፡ በቴክኒክና ሙያ አካባቢ ልታበዛው ትችላለህ፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ግን ጥራት ነው፡፡ ምርምር የሚደረግበት ተቋም ላይ ዜጎችን የማብቃት ስራ ነው የሚሰራው፡፡ አሁን እንደማየው፣ ከፍተኛ ትምህርትን እንደ ስራ ፈጠራ ነው እያዩት ያሉት፡፡ በያንዳንዱ ዞን፣ አንዳንዱ ጋር በወረዳም ይከፈታል፡፡ የግድ በእያንዳንዱ መንደር በስሙ የሚጠራ ዩኒቨርስቲ ሊኖረው አይገባም፡፡ መስፈርቱን ሳያሟላ መከፈት የለበትም፡፡ ዩኒቨርስቲዎች የብሄርና የማንነት ስሜት አንዲይዙ ያደረገው ይሄ ይመስለኛል፡፡ በየዩኒቨርስቲው የሚታየው ግጭት ምንጭ  ይህ ስሜት ነው፡፡ ‹‹የኔ ዩኒቨርስቲ ነው፤ መጣህብኝ›› የሚል ነገር አለ፤  በዛ ዩኒቨርስቲ የአካባቢው ተወላጆች ናቸው ከላይ እስከታች ያሉት፡፡ ይሄንን አርቆ ማየት ያስፈልግ ነበር፡፡
ኢትዮጲስ፡- የትምህርት ስርዓቱ መዛነፍ የጀመረው ያኔ ነው?
ፕ/ር በየነ፡-አዎ፣ በኢህአዴግ ጊዜ የታየው የትምህርት መዛነፍ የጀመረው ከዚያ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ እንዳንሰራ ተከለከልን፡፡ እነሱም በፖለቲካው መስመር የማይቃረኗቸውን፣ በስመ ምሁርነት እዛም እዚም ያለውን አሰባስበው፣ የይድረስ ይድረስ ሥራ ተሰራ፡፡ 
እዚህ ውስጥ ለኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት እንደወንጀል የምቆጥረው፣ ብዙ የኢህአዴግ መሪዎች እንግሊዝን ያውቋታል፡፡ ህወሓትም በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ያለው ለንደን ነው፤ በኋላ በሽግግሩ ወቅት ላይ ለስራ ጉዳይ ሄጄ አስጎብኝተውኛል፡፡ ከዛ ሆነው ነው የውጭ ግንኙነቱን የመሩትና ለተዋጊዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ያሰባሰቡት፡፡ እንግሊዝ አገር ውስጥ ያዩትን የእንግሊዝን ሥርዓተ-ትምህርት ለመኮረጅ ፈለጉ፡፡ የእንግሊዝና ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ይለያያል፡፡ እንግሊዞች ኦ ሌቭል ኤ ሌቭል የሚሉት አለ፡፡ ኦ ሌቭል አስረኛ ክፍል ማጠናቀቅ ነው፤ ኤ ሌቭል ደግሞ አስራ ሁለተኛ ክፍል ማጠናቀቅ ነው፡፡ ሀይስኩል አስረኛ ክፍል ያበቃል የሚለውን እኮ ከእንግሊዞች የኮረጁት ነገር ነው፡፡ አስራ አንድና አስራ ሁለት ፕሪፓራቶሪ ነው፣ ተማሪው ዩኒቨርስቲ ሲገባ አንደኛን ዓመት አጠናቆ ነው የሚሉት ነገር አለ፡፡ እንግሊዞች አስራ ሁለተኛ ክፍል ማጠናቀቅ የሚሉት እዚህ ፍሬሽ ማን  (የመጀመሪያ ዓመት) የምንለው ነው፡፡   እንግሊዞች በትምህርት ግብዓትም ሆነ መዋቅር ረዥም ርቀት የሄዱ እንደመሆናቸው ለእነሱ ልክ ነው፡፡ ለእኛ ግን ጨርሶ የማይሆን ነው፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥ ከመቶ በላይ ተማሪ ታጭቆ በሚማርበት ሀገር የሚስማማው ፖሊሲ አይደለም፡፡ ትልቅ ችግር የፈጠሩት የትምህርት ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች  የትምህርቱን ፖሊሲ ፖለቲሳይዝ ማድረጋቸው ነው፡፡
Filed in: Amharic