>

ከስህተቱ የማይማር ፈንጂ አምካኝ እና የኦሮሞ ፖለቲከኛ ብቻ ነው!!! (ግዛው ለገሰ)

ከስህተቱ የማይማር ፈንጂ አምካኝ እና የኦሮሞ ፖለቲከኛ ብቻ ነው!!!
ግዛው ለገሰ
– ለመሆኑ ኦነግ ማነው?
ባለፈው ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ ኦነግ የሚባል ድርጅት የለም፣ ድሮ ገና ተበታትንዋል፣ አሁን በኦነግ ስምና አርማ የሚንቀሳቀሱ አስመሳዮች ናቸው፣ በህወሓት እየተጋለቡ ኦሮሚያን እያመሱ ነው . .  . ብሎ ሲጽፍ ብዙዎችን አስቆጥትዋል፡፡ የእሱ የሰሞኑ ሁኔታ ግር ቢያሰኝም፣ የሆነ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ላይ የተጠመደ ቢመስልም፣ አባባሉ የተወሰነ አመክኒዮ የሳተ ቢሆንም፣ እንዲህ በይፋ መናገርና የልብን መግለጽ እንደጥሩ ጅምር ሊታይ ይገባል፤ ለውይይት መንገድ ይከፍታል፡፡
ሆኖም ኦሮሚያ ላይ አሁን ለሚገኘው ቀውስ እና ፍጥጫ ህወሓትን መወንጀል፣ ከዚያም አልሆ እራስን ነፃ ለማውጣት ሌላኛው ላይ ጣት መቀሰር፣ እንዲሁም የእኔ ካልኖርኩ ሰርዶ አይብቀል ድርጊቶቻቸው በተለይ በአሁን ሰዓት ፈንጂ አምካኝ መሆን ነው፡፡
አማኑኤል መሓሪ ከስህተቱ የማይማር «ፈንጂ አምካኝ ብቻ ነው» የምትል ግጥም አለችው፡፡ የኦሮሞ ኤሊቶች በህወሓት አነሳሽነትም ሆነ በግል ጥቅም እና መጠላለፍ ሲሳሳቱ ኖረዋል፡፡ ዛሬ ላይ አንድ መሆን አቅትዋቸውና የተነሱበትን «የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም» ዓላማ ዳግም በመዘንጋት ቀጥለው የሚፈፅሙት ስህተት ልክ የፈንጂ አምካኙ አይነት ነው፤ ለማረም የማይቻል፡፡ ፈንጂ አምካኙ በስህተት ያልሆነ ቀመድ ከበጠሰ፣ ቆይ ደግሞ ያንን ልሞክረው የሚልበት እስትንፋስ አይኖረውም፤ ፈንድቶ አልቆለታልና፡፡
ይህ ፎቶግራፍ በአርዳይታ ኮሌጅ ለስልጠና ከገቡ የኦነግ ጦር አባላት አንዱ በሆነ ወጣት ደረት ላይ የተነሳ ነው፡፡ ካኒቴራውን እና የአንገት ጌጡን ብዙዎቹ ወጣቶች ለብሰውት ነበር፡፡
የአንገት ጌጡን እኔም በስጦታ መልክ ተበርክቶልኝ ቁልፍ መያዢያዬ አድርጌዋለሁ፤ ልብ ብላችሁ ካያችሁት ጌጡ ላይ ABO ወይም WBO የሚል ጽሁፍ የለም፤  «ኦሮሚያ» ብቻ ነው የሚለው፡፡
እነዚህን ወጣቶች ማን እንደሆኑ ብትጠይቅዋቸው፣ የመጀመሪያ መልሳቸው «ወራና ቢሊሱማ ኦሮሞ (WBO)» ነው፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደማለት ነው፡፡ ካኒቴራው ላይ ደግሞ ጃዋር፣ ለማ እና አብይ ይገኛሉ፤ ኦነግነት ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም መታገል ካልሆነ ምን ሌላ ትርጉም ይኖረዋል?
ብርሃነመስቀል ኦነግ የለም ማለቱ ከድርጅትነት የዘለል ክቡር ምንነት አለው ለማለት ቢሆን ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም ኦነግ ዘመን ያስቆጠረ የኦሮሞ ትግል ‘ብራንድ’ ነው፤ ጽንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ የዳውድ ኢብሳን መልክ በቅጡ የማያቅ የኦሮሞ ወጣት በአሸባሪነት ታስሮና ተገርፎ ይሞት የነበረው ኦነግነት የዘላለም ስጋታቸው በነበሩ ኃይሎች ነው፡፡ ጃዋር መሐመድ ለእነ ዳውድ ኢብሳ አቀባበል መስቀል አደባባይ ሲገኝ በኦሮሞ ሕዝብ የኦነግ ‘ብራንድ’ ባለቤትነት አምኖ እንጂ የአመራሮቹ የትግል ስልት አድናቂ ሆኖ አልነበረም፡፡ እኛም በእለቱ ባንዲራውን የለበስነው በተመሳሳይ ነው፡፡
ኤልቲቪ ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለአንድነት (የኃይሉ ጎንፋ የኦነግ ክንፍ) ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አሚን ጁንዲ፣ «በአሁን ሰዓት ማናችንም ኦነግ አይደለንም፣ እንዲያውም ለማ እና አብይ ናቸው ኦነግ» ማለታቸው የኦነግን ጽነሰ-ሀሳብነት በትክክል ያመላክታል፡፡ ሆኖም ለማ እና አብይም ሆኑ ሌሎች ምኒልክ ቤተመንግስት መግባት ብቻውን የኦነግን የጽንሰ-ሀሳብ ግብ እንደመምታት አድርገው የሚያስቡ ገና የሚቀራቸው ይመስሉኛል፡፡ አብይ የተወሰኑ ግለሰቦችን ሳይሆን የወለጋን ሕዝብ በጥቅል እንደሕዝብ እንደጠላት ሲፈርጅ፣ ኢትዮጵያን አንድ ያደረገ ለማ መገርሳ ኦሮሞን አንድ ማድረግ ሲያቅተው ብቻ ሳይሆን የራሱ ካድሬዎች በአደባባይ ሌሎችን መግፋት ሲቀጥሉበት እያየን፣ የለውጡ የፊት ገፅ ስለሆኑ ብቻ የኦነግነት የክብር ካባ ልናጎናፅፋቸው አንችልም፡፡
ኦነግነት አክራሪነት፣ መገንጠል፣ ጨካኝነትና በጥባጭነት እንደሆነ የሚረዱ ብዙ ወዳጆች አሉኝ፤ ወያኔ አብቅቶለታል በተባለበት ጊዜ የሃያ ዓመት ፕሮፓጋንዳውን እስካሁን የሚያምኑ፡፡ ታዲያ ይህንን የተሳሳተ የኦነግነት ትርጉም ለማረም እየሰራ የሚገኘው የትኛው የኦሮሞ ፖለቲከኛ ነው? ለማም፣ አብይም፣ ኦነግ ናችሁ የተባሉትም ጭራሽ ሲያብሱት እንጂ ኦነግነትን ሲያስከብሩት አላየንም፡፡
እናም ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ «ከስህተቱ የማይማር ፈንጂ አምካኝ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው» ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡
ደግ ደጉን ያምጣልን!
Filed in: Amharic