>

የአማራን የትግራይ ርዕሰ መስተዳድሮች ስለ ሰላም መከሩ!!!

የአማራን የትግራይ ርዕሰ መስተዳድሮች ስለ ሰላም መከሩ!!!
 
አብርሃም በዕውቀት
‹‹አዲስ አበባ ስለሰላም ተናግሬ ከዚያ ሌላ ብናገር ይጠይቀኛል፤ ሄጄ የምሠራውም ከዚህ እንደምናገረው ነው!!!›› 
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
‹‹ይህች መሬት ሄደች ለኛ አጀንዳ አይደለም፤ ሊያጋጨንም አይገባም፡፡ ሕዝቡም ግጭት አይፈልግም፤ የአማራ ሕዝብ ከግጭትም አትርፎናል እላለሁ!!!››
 ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
ባሕር ዳር፡ ጥር 07/2011 ዓ.ም(አብመድ) የአማራና ትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር እየተወያዩ ነው፡፡ በመድረኩም ሁለቱ ርዕሰ መስተዳድሮች ንግግር አድርገዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ‹‹ስለሰላም ተጨንቃችሁና አስባችሁ ባሕር ዳርና በሌሎችም ክልሎች ተዘዋውራችሁ አስተምራችሁናል፤ መክራችሁናል፡፡ ይህ ደግሞ ከሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎችና እናቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ የሰላም አጀንዳ ይዛችሁ በዚህ ወቅት በመንቀሳቀሳችሁና እንድንገናኝ ጥረት ስላደረጋችሁ በአማራ ክልል ሕዝብ ስም አመሠግናለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ሰላም እንድንትሆን የምንመኛው ስለሆነ አካል ብለን ሳይሆን ለሁሉም መሠረት ስለሆነ ነው፡፡ ትንሽ ጊዜ እንኳ ግጭቶች ሲኖሩ ምን ያህል ጉዳት እንደሚደርስ እያየነው ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ከወንድሞቹና ከጎረቤት ክልሎች፣ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሰላም መሆን ይፈልጋል፤ ለዚህ የሰላም አጀንዳችሁም አመሠግናለሁ፡፡ የምመራው ሕዝብም ሰላም ይፈልጋል፤ ለመሥራት፣ ለመኖር፣ ለመሻሻል… የሚፈልግ ነው፡፡ ይህንንም ስታወያዩት ነግሯችኋል፡፡ እኔም ዝግጁ ነኝ፡፡ ሰላምን የሚጠላው ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተጠናወተው ነው›› ነው ያሉት አቶ ገዱ፡፡
‹‹የአማራና ትግራይ ሕዝቦች ለሺህ ዘመናት የጋራ ሃይማኖት፣ ባሕልና እሴት ያላቸው አንዱ በአንዱ የሚሰጋ ሳይሆን የሚኮራ ሕዝቦች ናቸው፤ ይህ ግን ከጊዜ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ሕዝቡ ሰላማዊ ፍላጎቱ በሰላም እንዲፈታ እንጅ እንዲጋጭ በፍጹም አይፈልግም፡፡ ያሉ ጥያቄዎች በውይይት በሰላም የሚፈቱበትን ሁኔታ ነው የሚፈልገው›› ሲሉም ተናረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ የሚሰጋና ከፍተኛ ጉጉት ያለው መሆኑንም ነው የተናሩት፡፡ ‹‹እኛም የዚህ ሕዝብ መሪዎች ነን፡፡ እኔ የምመራው ሕዝብ ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጭ ብሔድ ይጠይቀኛል፡፡ ከክልሎች ጋር በሰላም መኖር ይፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ ስለሰላም ተናግሬ ከዚያ ሌላ ብናገር ይጠይቀኛል፤ ሄጄ የምሠራውም ከዚህ እንደምናገረው ነው፡፡ አትጠራጠሩ የአማራ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ግጭት ጀማሪ አይሆንም፡፡ ከወንድሞቻችን የትግራይ አመራሮችና የትግራይ ሕዝብ ጋር በውይይት መፍታት እንችላለን፡፡ ቃሌ ፊርማዬ ነው ለሰላም እሠራለሁ›› ብለዋል አቶ ገዱ አንዳርቸው፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤም የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን አመስግነዋል፡፡ ‹‹በሕዝብ ብትመረጡም ባትመረጡም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ስለሆናችሁ አክብሬያችሁ ተገኝቻለሁ፡፡ እኛ የፖለቲካ መሪዎች መሥራት የሚገባንን ስላልሠራንና ስለተጨነቃችሁ አመሠግናለሁ፡፡ በታሪክ ያላየናቸውን ድርጊቶች እያዬን ስለመጣን አሳስቧችሁ ስለመጣችሁ አመሠግናለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹ግንኙነታችን ከወንድምነትም በላይ ነው፤ የፖለቲካ ጓዶች ነን፡፡ የሀገራችን እሴቶች ብቻ ሳይሆን የድርጅታችንም እሴት መሸርሸር ስላለ ነው እናንተንም ወደዚህ ጉዳይ የጋበዝናችሁ፡፡ ከዚህ ችግር ቶሎ መውጣት አለብን፤ መጨነቅ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አሉ›› ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፡፡
‹‹ተግባራችን ታሪካችንን የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡ ወደኋላ ተመልሰን ታሪካችን ስናይ ከሀገራቸው የተሰደዱና በሃይማኖት የማይመስሉንን ሰዎች በመሆናቸው ተቀብለናል›› ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፡፡
‹‹ፍትሕ ላጡ የሚረዳና ልዩነትን የማይቀበልና እንደ ሰው አብሮ መኖርን የሚያውቅ ታሪክ ያለን ነን፤ አሁን እየታዬ ያለው ድርጊት መጤ ነው፡፡ ባሕላችንና ታሪካችን አሁን ከሚታዬው የተለዬ ነው፡፡ የምንገኘው ከውርደትም ውርደት ውስጥ ነው፡፡ የድሮ የወላጆቻችንን መከባበር በመያዝ ብቻ ብዙ ርቀት መጓዝ እንችላለን፡፡ ለሌላው ዓለም የሚተርፍ ታሪክ ነው ያለን፤ እንዲህ ያለ ታሪክ እያለን ግን እንዲህ ወዳለው ሁኔታ እንዴት ገባን?›› ሲሉም ጥያቄ አዘል ሐሳባቸውን ዶክተር ደብረጽዮን ገልጸዋል፡፡
የድንበርም ሆነ የሰላም ጉዳይ በድርድር መሆን ያለበት ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹መገዳደል ኋላ ቀርነት ነው፤ የአራዊት ሥራና ኃጢአትም ነው፡፡ ግን የአመራሩ አካል ስለሆንን የችግሩም አካል ነን፡፡ የተበላሸ ፖለቲካ ስላለ ወደኋላ ትተን ተደጋግፈን መሥራት እንዳለብን አምናለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹የተበላሸው የእገሌ የእገሌ ነው ስለማይባል ፖለቲካችን ውለን አድረን ማስተካከል አለብን፤ የሰላም ጉዳይ ግን ለነገ አይባልም፡፡ የፖለቲካ ልዩነት አስቀድመን ሰላማችንን ማጣት የለብንም፡፡ በአማራ ላይ የምናነሳው የተለዬ ጥያቄ የለንም፤ ጥቂት ሰዎች ግን የሚያበጣብጡን አሉ፡፡ ይህች መሬት ሄደች ለኛ አጀንዳ አይደለም፤ ሊያጋጨንም አይገባም፡፡ ሕዝቡም ግጭት አይፈልግም፤ የአማራ ሕዝብ ከግጭትም አትርፎናል እላለሁ፡፡ ተፈናቅለው የመጡ የትግራይ ሰዎች አሉ፤ ግን የአማራ ሕዝብ ግጭቱን ቀንሶታል›› ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፡፡
‹‹የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዘመድ ብቻም አይደለም፤ ከዚያ በላይ ነው ግንኙነቱ፡፡ ችግር ያለው ፖለቲከኞች ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ ወደግጭት አታስገቡን ነው እያለ ያለው፡፡ በእኛ በኩልም እንደ አመራር ለመጋጨት አንፈልግም፡፡ ከትግራይ የሚተኮስ ነገር አይኖርም፤ ግፊቶች ግን አሉ፡፡ ሁሉም ኃላፊነት ከወሰደ ግጭቶች አይኖሩም፤ ታሪካችንም አይፈቅድም፡፡ ፖለቲካችን በፖለቲካው መድረክ እናየዋለን፤ ድርጅትም መንግሥትም ሕዝብም እየተናበብን እየሠራን ነው፤ የምትመክሩንን እየሰማን እያስተካከልን እንሄዳን›› ብለዋል፡፡
Filed in: Amharic