>

ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፤ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ  ነው!!! (አቶ ቡልቻ ደመቅሳ - አዲስ ዘመን)

ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፤ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ  ነው!!!

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ሰዎች መካከል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይጠቀሳሉ፡፡ በአጼኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን ሰርተዋል።በተባበሩት መንግሥታት ተቀጥረው በተለያዩ የአፍሪካ አገራት አገልግለዋል፡፡በፖለቲካው መስክም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄን በመመስረትና ሊቀመንበር በመሆን የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡ፓርቲያቸውን ወክለው በፓርላማ አባልነት  ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡በኢኮኖሚው መስክም የአዋሽ ባንክ መስራች ናቸው፡፡የካበተ ልምድ ካላቸው ከ88 ዓመቱ አዛውንት ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን እንዴት ይገልጿታል?

አቶ ቡልቻ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገር አይነት አይደለችም፣ የፈረንጅ አገርም አይደለችም፣ ባህሏም ኑሮዋና ታሪኳም የአረብ አገር አይደለም፤  አትመስልም። ራሷን የቻለች ብቸኛ አገር ነች፡፡ በሌላ አገር የሆነ ሁሉ በአገሪቱ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ አገር ያልሆነውም አንዳንዴ ሊሆን ይችላል፡፡  ስለዚህ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ነች፡፡

አዲስ ዘመን፡- የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል  ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ የጃንሆይ የቅርብ ሰው ነበሩ  ይባላል፤ እውነት ነው? 

አቶ ቡልቻ፡- ልክ ነው፡፡ ከአለቃዬም አቶ ይልማ ደሬሳ ጋር ስንሰራ የነበረውም በጣም በስምምነት ነበር፡፡ ጃንሆይ ደግሞ ሁለታችንንም ያቀርቡን ነበር፡፡በተለይ እኔ ልጅ ስለነበርኩ ወዲያ ወዲህ ተሯሩጬ እንድሰራ እኔን ማዘዝ ይቀላቸዋል፡፡

በዛን ጊዜ የገንዘብ ምክትል ሚኒስትርነት ሥራ የተለየ ነው፡፡ እንደሌሎች ሚኒስትሮች ዓይነት ሥራ አይደለም፤ ትልቅ ሥራ        ነው፡፡ ጊዜ አልነበረኝም፡፡ እሰራ የነበረው ሁል ጊዜ ከሚኒስትሩ እና ከጃንሆይ ጋር  ነበር፡፡ የአጼ ኃይለ ስላሴ መንግሥት መንግሥት ይመስል ነበር፡፡ በደንብ መንግሥትም ነበር፡፡ በምክትል ሚኒስትርነትህ ሥራ ስትሰራ አለቃ አለኝ ብለህ ታስባለህ፡፡ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን ጃንሆይም ምክትል የገንዘብ ሚኒስትርንም አቅርበው ይከታተሉ ነበር፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሁሉ እንደእርሱ ነበር ማለት አይደለም፡፡ በወቅቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ትኩረት የሰጡት የገንዘብ ጉዳይ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ እና በዛን ጊዜ ደግሞ አገሪቱ በጣም ደሃ ስለነበረች ነው፡፡ አሁን ቢሊዮን ነው የሚጠራው፡፡ ያኔ ቢሊዮን ይቅርና መቶ ሚሊዮንም በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡

በየቀኑ አሶሳ፣ ነገሌ፣አሰብ፣ምጽዋ ስልክ እንደውል ነበር፡፡ ምን ያህል እንደገባ መቼ እንደሚደርስ እንጠይቅ ነበር፡፡ምክንያቱም ያኔ ትልቁ ውጥረታችን የጦር ሠራዊት ክፍያ ስለነበር ነው፡፡ እነርሱ ገንዘባቸው አንድ ቀንም ሊያልፍ አይችልም፡፡ አይታገሱም፣ ያስፈራሩናል፡፡ ጃንሆይም ለእነርሱ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ከማንም በፊት ለጦር ሠራዊቱ ቅድሚያ እንዲሰጥ ይፈለጋል፡፡

ስለዚህ በጣም በቅርብ ነበረ ከእርሳቸው ጋር የምሰራው፡፡ በጣም አደንቃቸዋለሁ፡የሚደነቁ መሪም ናቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመን ኢትዮጵያ ለዓርባ ዓመታት ዕድለኛ ነበረች፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጃንሆይን ከስልጣን መወረድ ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?

አቶ ቡልቻ፡- የሚገርምህ ነገር ጃንሆይ  ስልጣን ሲለቅቁ እኔ አሜሪካ ነበርኩኝ፡፡በኢትዮጵያ መንግሥት ተለወጠ ተባለ፡፡ ሰዎች ታሰሩ ተብሎ ይነገር ነበር፡፡ በኋላ በ10ኛ ቀኑ የመንግስቱ ኃይለማርያን ፎቶ በጋዜጣ አወጡት፡፡ በጣም ተገረምኩኝ፡፡ አውቀው ነበር፡፡ ከጀነራል ኃይሉ ባይከዳኝ ጋር መንግስቱ ኃይለማርያም እኔ ቢሮ ይመላለስ ነበር፡፡ እርሱ ሀረር ጦር ትምህርት ቤት የግምጃ ቤት ሹም ነበር፡፡ጀነራል ኃይሉ ባይከዳኝ ደግሞ የጦር ትምህርት ቤቱ ኃላፊ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጃንሆይን  የሚያደንቋ ቸው በምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡- ሞልቶኛል ! እነግርሃ ለሁ፡፡ እርሳቸው አይቆጡም፡፡ ለመቆጣት ትልቅ ነገር መሆን አለበት፡፡ ቀስ ብለው ነው የሚናገ ሩት፡፡ የሚሰጡት ሥራ ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል  ያውቃሉ፤ይረዳሉ፡፡ በእኔ በኩል እንደ አጼ ኃይለስላሴ ያለ መሪ የለም፡፡ እርሳቸውን ስንገድል እና ስናዋርድ ራሳችንን አነቅን ፤ ራሳችንን ነው ያዋረድነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በደርግ ዘመን በምን ሥራ ላይ ቆዩ?  

አቶ ቡልቻ፡- በደርግ ዘመን ሙሉ ለሙሉ  እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበርኩም፡፡ኢትዮጵያን እና ሌሎች 18 የአፍሪካ አገራትን ወክዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአምስት ዓመታት በዓለም ባንክ ኢትዮጵያን በመወከል የቦርድ አባል ሆኜ ሰራሁ፡፡ አፍሪካ አገሮች ብዙ ሆነው ነው አንድ ሰው ይመርጡ የነበረው፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና አንዳንድ ትላልቅ አገሮች አንድ አንድ ተወካይ የቦርድ አባል የላቸውም፡፡

ሞስኮ፣ ቻይና እና የመሳሰሉት ኮሚኒስት አገሮች ያኔ የዓለም ባንክ አባል አልነበ ሩም፡፡ አሁን ነው የሆኑት፡፡ ዓለም ባንክ እንደሚታወቀው ገንዘብ አበዳሪ ተቋም ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢትዮጵያ አባል ነች፡፡ ሆኖም ሰው ተልኮ አያውቅም ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እኔ ሄድኩኝ፡፡ የሚያበድሩንን ገንዘብ ከፍ ማድረግ፣ የተበደርነውን ገንዘብ ለታለመለት ሥራ መዋሉና ሥራው መካሄዱን መከታተል፣ በተባለው ጊዜ እንደሚያልቅ ለማረጋገጥ እንከታተላለን፡፡ በዛን ጊዜ በተለይ መንገድ በደንብ ተሰርቷል፡፡ ተቋሙ አውራ ጎዳና ነበር የሚባለው፡፡ብዙ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ የኢትዮጵያን መንገዶች ለማሰራት ብዙ ድጋፍ ያደረገው የዓለም ባንክ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የዓለም ባንክ ተወካይ ሆነው በማገልገልዎ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ አገራት ያበረከቱት አስተዋጽኦ  ነበር?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ ቦርድ ላይ ነው ያለሁት፡ ያኔ የእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ጉዳይ ይነሳል፡ለምሳሌ አንድ አገር ብድር ጠይቋል፤ ተስማምተናል ወይ ተብሎ ይቀርባል፡፡ይሄኔ ከዚህ በፊት የተበደሩትን ገንዘብ መልሰዋል ወይ? አመላለሳቸው እንዴት ነበር? በትክክል በስምምነቱ እንደተቀመጠው ፈጽመዋል ተብሎ ይቀርባል፡፡ይህ ተገምግሞ ለትምህርት ማስፋፋት፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ የጠየቀችው የብድር ጥያቄ እንዳይቀነስ እታገል ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን በኢትዮጵያ ለተገኘው ለውጥ ባለቤቱ ማን ነው ይላሉ ?

አቶ ቡልቻ፡- ለውጡን ያመጣው የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው፡፡ ሄደን ሄደን እዚህ ደረስን፡፡ እንደሚመስለኝ ለሁሉም አሁን የደረስንበት ምዕራፍ ጥሩና ተስፋ ሰጪ ይመስላል፡፡ ሌላም የሚመስል አለ፡፡ አንዳንድ ጠቅላይ ግዛት  ( አካባቢዎች) ውስጥ ሰዎች ይዋጋሉ፡፡ ሁኔታው የት እንደሚወስድ አናው ቅም፡፡ ያገኘነው መሪ እግዚአብሄር የሰጠን ሰው ነው፡፡ በጣም ጥሩ ሰው አግኝተናል፡፡

ኢህአዴግ ሳያውቅ ይህንን ሰው ሰጠን፡፡ እኔ ምርጫው ሲደረግ አልነበርኩም፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ዶክተር አብይን መረጡ፡፡ እኔ የተሻለ ሰው የሚገኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ እና ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በዶክተር አብይ መመረጥ ሁሉም ደስ ብሎት ያጨበጭባል ብለን ነበር፤ ግን ይጋ ደላል፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ በቦ ረና ተኩሶች ነበሩ፡፡ ሰዎች ይገደሉ ነበር፡ ይህ እኔን ያስፈራኛል፡፡ መነሻ ምክንያቱ ባይታወቅም ሰላም የነበረበት አገር ሁሉ ይታኮሳል፣ ይጣላል፡፡ ይህንን ማሸማገል ያስፈልጋል፡፡ አዋቂዎች መሪዎቻቸውን በማነ ጋገር እንዲስማሙ እና እንዲታረቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እኔ የራሴን ሰው አላኩም ሄጄም አላየ ሁም፡፡ ነገር ግን ኦነግ ከመንግሥት ጦር ጋር እንደሚጋጭ ሰምቻለሁ፡፡የኦነግ መሪን ዳውድ ኢብሳን አውቀዋለሁ፡፡ ከአስመራ እንደመጣ አግኝቼዋለሁ፡፡ ታረቃችሁ አይደል? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ አዎን በደንብ ታርቀን፣ የምንሰራውንና የምናደርገውን ሁሉ ተስማምተን ነው የመጣነው ብሎ መልሶ ልኛል፡፡ እኔም በምላሹ ተደስቼ ነበር፡  አንድ ላይ መሆናችን አስደስቶኝ ነበር፡፡ግን የእርሱ ሰዎች በወለጋ በኩል ከመንግሥት ፖሊሶች ጋር ለምን እንደሚጣሉ አይገባኝም፡፡

ኦነግ የተመሰረተው ወለጋ ነው፡፡ሲመ ሰረቱ እኔንም ጋብዘውኛል፡፡ ገንዘብም ጠይቀውኝ አንድ ሁለት ጊዜ ትንሽ ገንዘብ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ከዛም የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ተብሎ ተመሰረተ፡፡ይሄ ምን ለማድረግ ነው?ብዬ አቶ ገላሳ ዲልቦን ጠየቅኩት፡፡ ኦሮሞ እስከ መቼ ተጨቁኖ፣መሬቱን ተቀምቶ ለሌሎች እንደባሪያ ገብሮ  ይኖራል አለኝ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ነገር ግን  ከኢትዮጵያ ተለይቶ መኖር አይችልም አልኩኝ፡፡ እነርሱ ጋር ያልገ ባሁትም ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ሌላ አገር ይሆናል የሚለውን ተቃውሜ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ራስን በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ እታገላለሁ ይላል፡፡ ከአማራው ጋር ደግሞ በደም ተሳስሮ የሚኖር ነው። እርስዎ ይህንን  እንዴት ያዩታል፡፡

አቶ ቡልቻ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ብዙ ሰዎች ይሄን ጠይቀውኛል፡፡አዎን በተለይም አማራ ከኦሮሞ ጋር በስፋት ነው የተጋቡት፡፡ኦሮሞው ለብቻው ተገንጥሎ በየት በኩል የውጪ ንግድ ሊሰራ ? ባህሉን እንዴት ሊያስተዋውቅ  ነው ወይስ ዘግቶ ሊቀመጥ ? ከዚህም በላይ ደግሞ ምን ለማትረፍ ነው፡፡ በቂ መሬት አለ፡፡ ለሁሉም የሚበቃ፡፡

ኦሮሞ ከዚህ በኋላ ነጻ ነህ ቢባል ምን ለውጥ ያመጣል ? ድህነታችን ያው ነው፡፡ድንቁርነታችንም ያው ነው፡፡ በየት በኩል ከውጭ መንግሥታት ጋር ሊገናኝ ነው፡፡ድሮ በአሰብና ምጽዋ አማካኝነት በር ነበር፡በእርግጥ አሁንም ኢትዮጵያ የባህር በር የላትም፡፡ አቶ መለስ ምንም ሳንነጋገርና ሳንከራከር ነው ያስወሰነው፡፡ ‹‹ወደብ ምን ድን ነው መከራየት ይቻላል፡፡ገንዘብ ከፍለን እንከራያለን፡፡ምንም አይደለም ሲል ነበር››፡ ቆይቶ ደግሞ «ወደብ የለንም» ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያለዎት አቋም ምን ይመስላል?

አቶ ቡልቻ፡- ኢትዮጵያ እንዳለች፣ እንደ ነበረች፣ አንድ ሆና እንድትቆይ እፈልጋለሁ፡ሁሉንም የሚጠቅመው ይሄ ነው፡፡ ቀስ በቀስ እንደ ኤርትራ ውልቅ ማለት የተጀመረ እንደሁ ጥሩ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት ትግራዮች ከኢትዮጵያ ነጻ ለመሆን ሞክረዋል፡፡ ወያኔ ማለት እኮ አዲስ ቃል አይደለም፡፡ የድሮ ነው፡፡ ያኔም ነጻ ለመውጣት ታግለዋል፡፡ ጃንሆይ ራስ አበበን ልከው አስታርቀዋል እንጂ በየጊዜው ለመገንጠል ሞክረዋል፡፡ አሁንም ህገ መንግሥቱ ውስጥ ያለው አንቀጽ 39 በአቶ መለስ ምክንያት የገባ  ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኦሮሞ ከ16 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ይነገራል፡፡ የአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በእግሩ እንዲቆም ትልቁን ድርሻ የተወጡት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው ይባላል፡፡ በአንጻሩ አሁን ኦሮሞ ተጨቁኗል ሲባል እንዴት ያዩታል ?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ የጃንሆይ ሠራተኛ በነበርኩበት ከዛሬ50 ዓመታት በፊትም ኦሮሞ እንደሚበደል እናውቃለን፡፡ ምንም ስልጣን የለውም፡፡ የተበደለ እና የተጎዳ ህዝብ ነው፡፡ መሬቱን ዘማቾች ከግዳጅ ተመልሰው ይወስዱበታል፡፡ አጥንተው ይመለሱና አስፈቅደው ይወስዳሉ፡፡ ይህንን እኔም በጋዜጣ ብዙ ጊዜ ጽፌያለሁ፡፡ ጓደኞቼም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ እያሉ ይጽፉ ነበር፡፡  ተመስጌን ጎበና፣ ሰለሞን ደሬሳና ሌሎችም ብዙ ይጽፉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የኦሮሞ ታሪክ አልተጻፈም፡፡አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያ በጥናታቸው ያገኙት ከፈረንጆች ነው እንጂ ከአገር ውስጥ ምንም አላገኙም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኦሮሞነት እና ከኢትዮ ጵያዊነት ለእርስዎ የቱ ይቀድማል?  

አቶ ቡልቻ፡- ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፤ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ  ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለሌላ ነገር ነው የሚያገለግለው፡፡ ማለቴ እኔ ውጭ አገር ስሄድ ምንድን ነህ ?  ተብዬ ስጠየቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ እመልሳለሁ፡፡ ኦሮሞ ነኝ ብል አይገባቸውም፤ለእኔ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት  ደግሞ  ለእኔ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

መጀመሪያ ወደዚህ አገር ስመጣ ኦሮሞ እንደማይታወቅ አውቄያለሁ፡፡ ከወለጋ ጊምቢ ነው የመጣሁት፡፡ ማንም አያውቅም፡፡ወለጋ  የት ነው  ይሉኛል፡፡ ጅማ በጅማ አባጅፋር አማካኝነት ታውቋል፡፡ወለጋን ብዙ ሰው አያውቅም ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም ኢትዮጵያዊ ነን ብለን ብዙ ታግለናል፡፡ እናም ኢትዮጵያዊ የሆንነው በትግል ነው፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንደዚህ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸው የታወቀላቸው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ አማራ፤ አማራ ነኝ ይላል ኢትዮጵያንም ይጠራል፡፡ ኢትዮጵያ የጥንት ስም ስለሆነ የሚጠራ ያኔ ይታወቃል፡፡ በመካከል ግን ብዥታ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- አጼ ምኒልክ ጡት አልቆረጡም፤ ሌላውንም ህዝብ አልጨቆኑም የሚሉ አሉ ይሄ ምን ያህል እውነትነት አለው?   

አቶ ቡልቻ፡- አጼ ምኒልክ ያልተደረገ ነገርን አድርገዋል አልተባለም፡፡ ይህ ለእዛ ዘመን የተለመደ ነው፡፡ የወቅቱ የፍትህ ስርዓቱ ነው፡፡አንዳንድ አገር ጡት መቁረጥ፣ እጅ መቁረጥ፣ ምላስ መቁረጥ ህግ ነው፡፡ዳኝነት ነው፡፡ስለዚህ እርሳቸውም አድርገዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስም አድርገዋል፡፡ አጼ ዮሐንስም አድርገዋል፡፡ያላደረገ የለም፡፡ድሮ ሰው የሚፈራው እንዲህ ዓይነት ቅጣት ሲጣል ነበር፡፡ ፈረንጆቹም እንደዚህ እያደረጉ ነበር የሚይዙት፡፡ ጋናን፣ ናይጄሪያና ኬንያን እንዲሁ ነው፡፡ አጼ ምኒልክ በተቻላቸው አቅም ጦር ሠራዊታቸውን በመላክ የኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም አካባቢ ይዘዋል፡፡ ራስ ጎበናን ደግሞ ደብረ ብርሃን ጉግስ ይጫወቱ ነበር “ና እና እርዳኝ ያንተ ህዝብ ኦሮሞ እያስቸገረኝ ነው” ብለው መልዕክት ልከው አስመጥተዋቸው ራስ አድርገዋቸው ሰሩ፡፡ እንደተባለው ባይሆንም ብዙም ሳይሰሩ እርሳቸውም ታመው ሞቱ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡ እስኪመጣ ድረስ ያለውን  27 ዓመታት  እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ቡልቻ፡- በእነርሱ ዘመን ድንቁ ርና ነው የሚበዛው፡፡ ሰው አያውቅም እንጂ እነርሱ አሁንም ጉልበት አላቸው፡፡ የሰሩት በድንቁርና ነው፡፡ሰው ሲያስሩ፣ ሲገድሉ፣ ገንዘብ ሲሰርቁ ዓይን የላቸውም፡፡ጊዜው ያልፍና እንቀጣለን አይሉም፡፡ እኔ ፓርላማ ውስጥ አቶ መለስን ብዙ ጥያቄ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡እርሳቸው ስልጣን መጠቀምን እንጂ ሌላ ምንም የሚ ያስቡት ነገር የለም፡፡ አቶ መለስ አዋቂ ነው፣ ጎበዝ ነው፡፡ የሚሆነውን ነገር ያጣራል፡፡ ግን ለዘለቄታው የሚሆን ጥሩ ነገር በገጠርና በከተማ አልተሰራም፡፡

ብዙ ነገር ሲሰራ የነበረው በሞኝነት ነው፡ አጼዎች ይሻላሉ፡፡ እነርሱ ትንሽ ትንሽ ከዘመ ዶቻቸው ተምረው ነው የሚመ ጡት፡፡ ለምሳሌ ኃይለ ስላሴን በጣም ነው የማደንቃ ቸው፡፡ ሲያዝዙ፣ ነገር ሲበላሽ ሲመረምሩ ጎበዝ ናቸው፡፡ ለእኔ ብዙ ጊዜ እኛ ማን ነን? ይሉኛል፡፡ ኦሮሞ ነኝ እኔም ማለታቸው ነው፡፡ግን ከአፋቸው አውጥ ተው ኦሮሞ ነኝ አይሉም። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ…መባልን አይወዱም፤ ኢት ዮጵያዊ ነኝ እንዲባል ነው የሚፈልጉት፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በመሆንዎ ያለፉትን ጊዜያት እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ቡልቻ፡- ስለኢኮኖሚ መነጋገር ደስ ይለኛል፡፡ ኢህአዴግ በኢኮኖሚ ጉዳይ ሰው እንደሚለው መጥፎ አልሰራም።ለምሳሌ እኔ ገጠር ብዙ አካባቢዎች ዞሬያለሁ፡፡ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መንገድም ሰርተዋል፡፡ ጤና በጣም አስፋፍተዋል፡፡ አርሶ አደሩ ለምርቱ ማዳበሪያ እንዲጠቀምና ምርት እንዲጨምር አድርገዋል፡፡ይህ እንደመጡ የሰሩት ነው፡፡ እኔ ሁሉንም ነገር ዋጋ አላሳጣቸውም፡፡ ድሮ ያልተሰሩ ነገሮችን ሰርተዋል፡፡

አቶ መለስ ብቻውን ብልህ ነበር፡፡ሲወለድም ተፈጥሯዊ እውቀት ያለው ጎበዝ ነው፡፡ አሜሪካኖችና እንግሊዞች ነበሩ የሚያስተምሩት፡፡ በኋላ እየተበላሸ  ሄደ፡፡ የግል ጥቅም ፍለጋ ጀመሩ፡፡ መሬቱ ንም በህግ አጣርተው ሳይሆን እንዲሁ እየተነጋገሩ እዚህም እዚያም ፎቅ ይሰራሉ፡፡ አሁን ብዙ ፎቅ  የእነርሱ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደነበር እየተናገሩ ነው፤በአንድ ወቅት ግን ኢትዮጵያ 11 በመቶ አድጋለች ተብሎ በፓርላማ ሲቀርብ በዚህ ደረጃ አላደግንም በማለት የተከራከሩት ትክክል ነው?

አቶ ቡልቻ፡- ይህ ክርክር የነበረው ኢህአዴግ አገሪቱን ለ15 ዓመታት ካስተዳደረ በኋላ ነው፡ ዕድገት በዓይን ይታያል፡፡ሰዎች ልጆቻቸውን ጥሩ ደግሰው ይድራሉ፣ተሽከርካሪ ይገዛሉ፣ ይገባበዛሉ፣ሰው ደስ ብሎት ይኖራል፡፡ወለጋ ድሮ ልጆች ሲዳሩ ግብዣ የሚደረገው ዳስ ተጥሎ ፣ መሬት ላይ የሙዝ ቅጠል ይነጠፍና እዛ ላይ ነበር ሰው የሚመገ   በው፡፡ ሁሉም በፈረስ እየጋለበ ነበር የሚታየው፡፡ ብዙ ቆይቼ ከተመለስኩ በኋላ ፈረስ ያለውም የለም፡፡ እኔ የማውቃቸው አባቶቻቸው ፈረስ የነበራቸው እንኳን ልጆቻቸው ፈረስ የላቸውም፡፡ ታመው መሞት እንጂ መዳን የለም፡፡ ኢኮኖሚ እኮ ማለት ይሄ ነው፡፡ እኔ ያኔ እናደድ የነበረው ይሄን እያየን ለምን አደግን ትላለህ? ብዬ ነበር፡፡

ታይዋን፣ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን አድገ ዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ እንኳን ናይጄሪያ እና አንጎላ አድገዋል፡፡ ያደጉበት ምክንያቱ ዘይት በማግኘታቸው ነው፡፡የእኛ ህዝብ ምንም የለውም ደሃ ነው።ለምንድነው 11 በመቶ አድጓል የምትለው? በ11 በመቶ ያደጉት ቻይና ቀጥሎ ታይዋን ናቸው። ቻይና ከዛ በፊት በ13 በመቶ አድጋለች፡፡ ይህ የዕድገት ቁጥር በሁሉም ኢኮኖሚስቶች ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ የአገሪቱ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ልማት ፍሬ ምንም የለም፡፡ ምንም ሳይኖር ነው አቶ መለስ ጉዳዩን ስለሚያውቀው አድገናል ያለው፡፡ እኔ እውነቴን ነው፡፡ እርሱ እውነቱን አልነበረም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ በወቅቱ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት  ምን አሉ ?

አቶ ቡልቻ፡- በዛን ጊዜ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዕድገት ያለው አምስት በመቶ ነበር፡፡ እርሱም ጥሩ ነው፡፡ በሃያ ዓመት ጥሩ ኢኮኖሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡         

አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ  ምን ይመኛሉ?

አቶ ቡልቻ፡- የህዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል እመኛለሁ፡፡ ዋናው የህዝቡ በሽታ የኑሮ አለመሻሻል ነው፡፡እርሻ እንዲስፋፋ ያስፈልጋል፡፡እግዚአብሄር የሰጠን መሬት አለ፡፡እርሱን በደንብ ማረስ ያስፈልጋል፡፡ በየጊዜው የእርሻ መሬቱን ማሳደግ ይገባል፡፡ ማዳበሪያ በመጠቀም በስፋት ማረስ ያስፈልጋል፡፡ተጨማሪ አዳዲስ መሬት ማልማት ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ አርሶ አደሩ ብዙ እንስሳቶች ይኖሩታል፣ተሽከርካሪ ይገዛል፣ ልጆቹን ባግባቡ ያሳድጋል፣ ኑሮው ይሻሻላል፣ ዘመናዊ ቤትም ይገነባል፡፡ይሄ በኢትዮጵያ እንዲሆን እመኛለሁ።

እኔ ተማሪ ሆኜ ጫማ የሚያደርግ ተማሪ አልነበረም፡፡ በእርግጥ አሁን ይህ ተቀይሯል፡ ይሄም  ትልቅ እድገት ነው፡፡ በመንግሥቱ፣ በኃይለስላሴ ጊዜ ጫማ ማድረግ አልተለመደም ነበር፡፡ አሁን ዶክተር አብይ ወደ ሥራ ቢመለስና ሥራውን ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ፤ከዚህ በኋላ ማደግ እንጀምራለን፡፡ ግን ለእርሱ ሰላም መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የእርሱን ንግግር ተከታትያለሁ በጣም አዋቂ ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከእርሱ ጋር ሲወዳደሩ የነበሩ ትን ሰዎች በሙሉ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ሲጨቃጨቁ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚ መራ እንመርጣለን ብለው የተሰባሰቡት ሰዎች ያኔ በጣም ጥሩዎች ነበሩ፡፡ እርሱን የመረጡት አውቀውና ተረድተውት ነው፡፡ሰው ዬው ጭንቅላት አለው፣ ከሰው ጋር የመኖር ችሎታ አለው፣ ሰውን ማስደሰትና ማባባል ያውቃል፡፡ሰውን የሚገዛው ጉልበት ብቻ አይደለም ፍቅር ነው፡፡ እርሱ ይሄንን አጥንቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን አስተዳደር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹን ይነግሩኛል?

አቶ ቡልቻ፡-ኡይ …መቼ ተጠናና፡፡ ደካማና ጠንካራ ጎንነው ብሎ ለማለት አይቻልም፡፡ ሰውዬው ጥሩ ነው ከማለት በስተቀር፡፡ ግን ሰውዬው እንዲሁ ሰው ይወደዋል፡፡ እርሱ ሲናገርም ሃሳቡ ግልጽ፣ጥሩም ነው፡፡ ገና ነው አሁን ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ገና የድሮ ሥርዓት ወድቆ የአሁኑ አልተተካም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀሪ ዘመንዎ ምን ለማድረግ ያስባሉ?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ የቀረኝ ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ አሁን 88 ዓመቴ ነው፡፡ አንጎሌ ይሰራል፣ ሰውነቴም በእርጅና ምክንያት አልደከመም፡፡ ፓርላማ ውስጥ ገብቼ መነጋገር እችላለሁ፡፡ በመሆኑም አንድ ጊዜ ፓርላማ መመረጥ እፈልጋለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤት አባልነትዎ የነበረዎትን ትውስት እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ቡልቻ፡- ምክር ቤት ውስጥ ኦሮምኛ መናገር ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አስ ቸጋሪ አደረጉብኝ፡፡ እንኳን ሹሞቹና ትንንሾቹ ጀሌዎች ቃለ ጉባኤ የሚጽፉት ኦሮምኛ አያውቁም፡፡ ቃለ ጉባኤ ደግሞ ምክር ቤት ውስጥ ዋና ጉዳይ ነው፡፡የተባለው ነገር መጻፍ አለበት፡፡ በዚህ ምክን ያትም እንድተው ይወተውቱኝ ነበር፡፡ ‹‹ስንዘጋጅና ቋንቋውን ስናውቅ በኦሮምኛ እንሰራለን እንጂ አሁን አይቻልም›› ብለው አፈ ጉባኤ የነበሩት አቶ ተሾመ ቶጋ ጠየቁኝ፡፡ እሺ ብዬ በራሴ ፈቃድ ተውኩት፡፡ አሁን መንግሥት መክሮበት ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ እንዲሆን እየታሰበ ነው፡ያ ከሆነ ቃለ ጉባዔ የሚይዝ ቋንቋውን የሚያውቅ ሰው ይቀጠራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!

አቶ ቡልቻ፡- እኔም አመሰግናለሁ!

Filed in: Amharic