>
5:13 pm - Friday April 20, 4446

  ኢሠፓና ጀነራሎቹ!!! (የቀድሞው የተረሳነው ጦር)

 

ETHIOPIA – DECEMBER 01: President of Ethiopia, Haile Mariam Mengistu in Addis-Abeba, Ethiopia in December , 1987. (Photo by Francois LOCHON/Gamma-Rapho via Getty Images)

ኢሠፓና ጀነራሎቹ!!!

የቀድሞው የተረሳነው ጦር 
ከጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሐምሌ 8/1979 እንደተመለሥኩ ለአራት ወራቶች ብቻ አዲሥ አበባ እንድቆይ ከተደረገ በሁዋላ ደሤ ላይ ሠሜን ምሥራቅ እዝ መምሪያ ሢቋቋም ቀጠናውን ሥለምታውቀው ሂድ ተባልኩ፡፡ተምሮ ላፈር ይሏችሁዋል ይሄ ነው፡፡የእዙ አዛዥ ሜጀር ጀነራል አለማየሁ ደሥታ ነበሩ፡፡ያሁኑ ሜጀር ጀነራል ያንጊዜ ሻምበል አለምሸት ደግፌ የዩኒቨርሥቲ ትምህርቱን እንዲያቋርጥ ተደርጎ በረዳት ዘመቻ መኮንንነት ከአለቃው ከኮለኔል ለገሠ ዳኜ ጋር ከአአ ወደጢጣ ጦር ሠፈር ከትመዋል፡፡
አለቃዬ ኮ/ላቀው ወ/ሠንበትም የእዙ ፖለቲካ መምሪያ ሐላፊ በመሆን እዙን መሥርቷል፡፡ጀነራል አለማየሁ ደሥታ ደልዳላና ብሥል ቀይ ሢሆኑ የተረጋጉ ፂማቸውን ከአፍንጫቸው ሥር ወደ ከንፈራቸው በጣም ዝቅ አርገው የሚላጩ፡በአፍንጫቸውና በላይኛው ከንፈራቸው መሐከል ቢያንሥ አንድ ሤ/ሜ ያህል የሚተዉና ከርዳዳ ፀጉራቸው ደግሞ ከፊት ለፊት ተፈጥሮ ይሁን ቀለም እርግጠኛ አይደለሁም ግማሽ ነጭ ሆኖ ግርማ ሞገሥ አላብሥአቸዋል፡፡
እሣቸው ባለፉበት ቦታ ወይም ከጨበጡህ የሚጠቀሙት ውድ ሽቶ ሙሉ ቀን ከምትሥበው አየር ጋር ተሥማምቶ መአዛው በቀላሉ የማይተው ሢሆን እርጋታቸው የሚገርም ነው፡፡ጀነራል አለማየሁ በራሣቸው አለም ውሥጥ ብቻ የሚኖሩ እንደሌሎች አቻ ጀነራሎች የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልም ሆነ ተለዋጭ አባል ያልነበሩ፡በመንግሥቱ ኃ/ማ ጭምር የአድሀሪ ቤተሠብ ተብለው ይፈረጁ የነበሩ። ለይሥሙላ ግን የኢሠፓ ተራ አባል ሆነው በእዝ አዛዥነት የተመደቡ አብዛኛውን ያገልግሎት ጊዜያቸውን በውጭ በመከላከያ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ያሣለፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ወሎ የተመደቡ አዛዣችን ነበሩ፡፡ኢሠፓ በመዋቅርና ያሥፈልጉኛል የሚላቸውን ግለሠቦች የፓርቲው ሀላፊዎች በግምባር እየቀረበ የማርክሢሥት ሌኒንሥቱ የፓርቲ አመለካከት የሀይማኖት ተከታዮችን ማቀፍ ባይፈቅድም ጀነራል አለማየሁ ይጠየፉት የነበረውን ሥርአትና ፓርቲ በግድ እየተገፉ እንዲያገለግሉ ተፈርዶባቸው ከደቡብ ወሎና ከሠሜን ወሎ የፓርቲ ተጠሪዎች ጋር እየተላተሙ ለሥርአቱ አልመች አሉ፡፡የክፍለሐገሩ ኢሠፓ ፅ/ቤት በፀጥታ ጉዳዮች ሥብሠባ ሢጠራቸው ምን አገባችሁ፡ ይሄ የሠራዊቱ ጉዳይ ነው፡፡ጦር ከሢቢል ጋር ሆኜ አልመራም አይመለከታችሁም ሥለሚሏቸው ከሢቢል ሕ/ሠብ ሊገኙ የሚገባቸው ተጨማሪ የመረጃ ግብዓቶች ነጠፉ፡፡
እኔ ከምድብ የርእዮተ አለም ሐላፊነቴ በተጨማሪ የእዙ መ/ድ አንደኛ ፀሐፊ ሆኜ ተመርጬ እየሠራሁ ሥለነበር ወርሐዊ ሥብሠባ ላይም እያረፈዱ ሥለሚመመጡ ባንድ ወቅት ተሠብሣቢው በሙሉ ለምን በሠአቱ አይገኙም በሚል የእለቱ የሥብሠባ አጀንዳ በሚያውክ መልኩ ጉዳዩ አሁኑኑ እልባት ያግኝ በሚል አዳራሹ ተናጋ፡፡እኔም በመጀመሪያ ጀነራል ለመንግሥትም ለፖርቲም ሥራ ከፍተኛ ሐላፊነት ተሠጥቶት እኛን እየመሩ ያሉ ሠዉ ኖት፡፡በፓርቲው ድርጅታዊ መመሪያ ሕግ ደግሞ መሠረታዊ ድርጅቶች ቁልፍ የፓርቲው የአባላት የግንኙነት መድረኮች ናቸው፡፡የእርሦንም ሐላፊነት የሚያግዝ መዋቅር ሠአት ለማክበር ያጋጠሞት ችግር ምንድን ነው ግልፅ ያድርጉልን ብዬ በአክብሮት ለሥብሠባው መልሥ እንዲሠጡ ጠየኳቸው፡፡የመለሡት መልሥ ግን የኔና የናንተ ሠአት አጠቃቀም ላይ ችግር ካልኖረ በቀር በሠአቴ ነው የመጣሁት ብለው ደመደሙ፡፡በሣቸው አመራር ምቾት ያጡ መኮንኖችም ሹሞችም ወታደሮችም ያልተገባ የቃላት ምልልሥ እንዳይፈፅሙ ነገሩን መዝጋት ሥለነበረብኝ ጓዶች በመጀመሪያ ይሄን ጉዳይ በኮሚቴ አይተን በአጀንዳ አሥፈላጊም ከሆነ ለበላይ አካል አሥፈቅደን አሥቸኳይ ሥብሠባ ጠርተን እንወይበታለን፡፡
በተረፈ ጓድ ጀነራል በኛና በርሦ መካከል ይሄን ያህል የሠአት መለያየት ካለ በወታደራዊ የግዳጅ አፈፃፀም ላይም ችግሩ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ሠአቶትን በብዙሀኑ ልክ ያሥተካክሉ ወይም በእርሥዎ እዝ ሥር በኮንትሮባንድ ተይዘው የተቀመጡ ሠአቶች በወታደራዊ መደብር ውሥጥ ሥላለ አንዱን ቢጠቀሙ ችግር አይኖረውም ብዬ ተሣሥቀን የእለቱን አጀንዳ ተወያይተን ጨርሠን ወጣን፡፡የክ/ሐገሩ የኢሠፓ ኮሚቴ በሁዋላ ጀነራል ግርማ ንዋይ አየተመራ ሪፖርት ወደ ማእከላዊ ኮሚቴ የይነሡልን ጥያቄ በማብዛቱ ጀነራል አለማየሁ ደሥታ በአዲሡ ብ/ጀነራል አበበ ኃ/ሥላሤ ተተኩና ሌላው ድራማ ተተካ፡፡
ጀነራል አለማየሁ ደሥታ ከሠሜን ምሥራቅ እዝ መምሪያ መነሣታቸው እርግጥ ሆኖ አኔጋ የፓርቲ አባልነት ግዴታቸውን ሊወጡ መጡ፡፡ተነሥቼ ተቀበልኳቸው፡፡የፓርቲ አባልነት ደብተራቸውን ተደላድለው ከተቀመጡ በሁዋላ አውጥተው ሠጡኝ፡፡ሁኔታቸው ልቤን ነክቶታል፡፡የደረሡበትን የማእረግ ከፍታና እውቀትና ልምዳቸውን ጊዜው ከሚጠይቀው ያካሄድ ብልጠት ጋር አዋህደው በፓርቲው ያሠራር መርህ ጋር ራሣቸውን አዋህደው ያለግትርነት መሄድ ቢችሉ ያለችግር እዙን እየመሩ ይቆዩ ነበር፡፡ጌታዬ ምድቦትን አወቁ አልኳቸው፡፡
ለጊዜው መከላከያ ሪፖርት እንዳደርግ የዝውውር ደብዳቤዬ ያሥረዳል፡፡በኔ ቦታ በሢቢል የኢሠፖ መዋቅር ውሥጥ ሢሠራ የነበረና በቅርብ ብ/ጀነራል የተሾመ ጎረምሣ ተሹሞላችሁዋል፡ደግሞ እሥቲ ሞክሩት፡፡መቸም ክፍለሐገሩ ኢሠፓ ከገበሬው፡ከመምህሩ ከሴቶች ከወጣቱ ወዘተ ጋር ሥብሠባ እያሥቀመጠ ወታደራዊ እቅዶችን አብረን እንድናቅድ ይፈልጋል፡፡ይሄንን እናንተ መቃወም አለባችሁ፡፡በተረፈ  በኔ ደረጃ ቅሬታ የፈጠርኩት ነገር ካለ ይቅርታ እየጠየኩ ማታ አዲሡን አዛዥ ለመቀበልና አኔን ለመሸኘት በተዘጋጀ የራት ምሽት ላይ እንገናኛለን ተባብለን የፓርቲ አባልነት ክፍያቸውን አጠናቀው በቀጣይ ለሚሄዱበት የመከላከያ መሠረታዊ ድርጅት ዶክሜንታቸውን እንደምልክላቸው ገልጨላቸው፡የማታው ዝግጅት ላይ ደሤ አምባሠል ሆቴል እንደምንገናኝ አሥበን ተለያየን፡፡
ማታ ላይ ግብዣው ላይ ክፍለ ሐገሩ ኢሠፖባዘጋጀው አሸኛኘት ሥለ ጀነራል አለማየሁ በቆይታቸው ጦሩንና ሕብረተሠቡን አቀናጅተው የመሩ ወደፊትም ለመከላከያችን አሥፈላጊ የነበሩ ፡በበላይ አካል ለተጨማሪ ሐላፊነት በመታጨታቸው ሢለዩን እናዝናለን በሚል ውሥጡ የእንኳን ገላገለን የጉዞ ፍታት ተደርጎ ገና ምንነታቸው ያልታወቀዉን ብ/ጀ አበበ ኃ/ሥላሤን ያገነነ ንግግር ተደርጎ መሠነባበቱና የመቀበል ሥርአቱ ተጠናቀቀ፡፡
የአዲሡ ብርጋዲየር ጀነራል አበበ ኃ/ሥላሤ የፓርቲ አባል የመመዝገቢያ ደብተርና ሌሎቹም ዶክሜንቶች ከአብዮታዊ ጦር ዋና ፖለቲካ አሥተዳደር ቀድሞ ተልኮልኝ ሥለነበር ቢሮአቸው የገቡትን የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባል የሆኑትን አዲሥ ጀነራል እኔው እራሤ ሄጄ ተዋውቄ እኛጋ በመሠረታዊ ድርጅቱ ውሥጥ ታቅፈው የፓርቲ ግዴታቸውን እንደሚወጡ ገልጬ መልሣቸውን ሥጠብቅ፡፡በመጀመሪያ ደረጃህን እወቅ፡፡እኔ የማእከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባልና አንድ ትልቅ ጀነራል ነኝ ፡፡በመጀመሪያ አቅማችሁን እወቁ ብለው ከፍ ዝቅ አድርገው የውጣልኝ አይነት ሀይለ ቃል ሢመልሡልኝ ልወጣ ሥል ፡ይገባሀል ቢያንሥ መሠብሠብም መነጋገረም ካለብኝ ከክፍለ ሐገሩ ኢሠፓ ኮሚቴ እንጂ ከእናንተ ጋር አውጫጭኝ አልቀመጥም ብለውኝ አረፉ፡፡ይሄ የፈረደበት ፓርቲ ያወቁ የበቁ በማእከላዊ ኮሚቴና በተለዋጭ አባልነት የሠበሠባቸው ማርክሢሥቶች ደንብና ፕሮግራሙና በሚገባ ሣይረዱ ወይም ለይሥሙላ ብቻ የተሠባሠቡ ከኛ በላይ ላሣር የሚሉ ግለሠቦችን ሠብሥቦ ድልን መጓጓቱ አሣዛኝ ነበር፡፡
ከቢሮአቸው በመጣሁበት አኳሁዋን ሠላምታ ሠጥቼ በሆዴ ራሥዎ ቢሮዬ ድረሥ መጥተው አሥፈላጊውን ይፈፅማሉ ብዬ ወጣሁ፡፡እንደ ሁኔታቸው አጃቢዎቻቸውን ጠርተው ደቦል ቅጡልኝ ብለው ጉድ ሣይሠሩኝ ወደ ቢሮዬ አመራሁ፡፡በሦሥተኛው ቀን ኤዲሢአቸውን /ፀሐፊያቸውን ልከው ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉ ሢለኝ እንደማንኛውም የፓርቲ አባል መጥተው ሪፖርት ያድርጉ ሥራ ላይ ነኝ በላቸው፡፡ለካሥ እኔ ሠውየው የፖርቲውን አሠራር አውቀው ይሁን ሣያውቁ ደረጃህን የማታውቅ ብለው ከፍ ዝቅ አርገው ከቢሮአቸው ተባርሬያለሁና በሚገባቸው ቋንቋ አሥረዱዋቸው ብዬ ሪፖርት ባደረኩት መሠረት ለካ ተወቅሠዋል፡፡በዚያ መሠረት ነበር የጠሩኝ፡፡ፀሐፊያቸው መልሤን እንዳደረሠላቸው ወደ ቢሮዬ መጡ፡፡ጌታዬ ይቅርታ ያድርጉልኝ መምጣት ነበረብኝ የፓርቲውን ታላቅነትና የሐገሪቱ ርእሠ ብሔር ጭምር በፓርቲው መሠረታዊ ድርጅት እንደማንኛውም የፓርቲ አባል እኩል ጀረጃ ያላቸው ናቸው፡፡
ለዚያ ብዬ ሣይሆን ሥራዬን ጨርሼ ልመጣ ነበር ብዬ በዘዴ ከማንም በፓርቲው አባላት መካከል መናናቅ ተገቢ ያለመሆኑን በፓርቲው መርህ ፍንጣሪ ጨረፍ አረኳቸው፡፡
ጊዜ አልወሠዱም በናንተ ሥር እንደምደራጅ ተነግሮኛል፡፡የአባልነት ክፍያዬን መክፈል እችላለሁ ብለው የመታወቂያ ደብተራቸውን ሠጡኝ፡፡ከተመለከትኩ በሁዋላ ክፍያቸውን ተቀብየ ተለያየን፡፡ጀነራሉ ትእግሥት የለሽ ብዙ ጊዜ ፂማቸውና ፀጉራቸውን እንደወታደር የማይሥተካከሉ በጣም ችኩልና ወደ እኛም ተመድበው ሢመጡ በሁሉም ዘርፍ በራሣቸው እምነት ብቻ የሚጓዙ፡ሥህተታቸውን ወዲያው ከማረም ይልቅ ሥህተቱ በሚፈጥረው መዘዝና ጉዳት የሚማሩ፡ራሥን ብቻ አዋቂ አድርጎ የመደምደም ባህሪ የነበሩ መኮንን ናቸው፡፡
ኢሠፓ ጉዱ ብዙ ነበር፡፡

 

Filed in: Amharic