>
5:13 pm - Friday April 19, 2926

አቶ ለማ መገርሳ ታፍኖ የቆየውን የመከራ ምስጢር ይፋ አወጡ!!! (ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ) 

አቶ ለማ መገርሳ ታፍኖ የቆየውን የመከራ ምስጢር ይፋ አወጡ!!!
ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ 
 “… ዶ/ር አብይ ኦሮሞ በመሆኑ ከቤተመንግስት በጉልበት እሳት አቀጣጥለን እናስወጣዋለን የሚሉ ከመጡ  እንሟሟታታለን እንጂ አይለቅም!!!”
አቶ ለማ መገርሳ
“ከሰማይ በታች የሚፈሩ ነበር – ለመናገር አይደለም ቀና ብለን የማናያቸው ነበሩ ባለጊዜዎቹ፡፡  በዚህ ሀገር ለጥቂቶች ህግ የበታች ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከ17 ቀናቱ በፊት 700 ቀናት ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ታሪክ ያወጣዋል፡፡ ላለፉት 7 አመታት ስንሳደድ ነበር፡፡ ከስልጣንም የተባረርን ነበርን፡፡ አዳኞች ተመድበውብን በወጣን በገባን ቁጥር ያስፈራሩን ነበር፡፡
 ኦሮሞ ለስሙ ባለስልጣን ሆነ ይባል እንጂ የምር ከወንበሩ ላይ አልነበረም፡፡ አሁን የማፍረስ ዘመቻ ቀጥሏል፡፡ ሰዎችን የመተካካት ሳይሆን ችግራችን ሆኖ የቆየው የተበላሸ ስርአትን ይዞ የመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ የኦሮሚያ መንግስት እና የፌደራል ሰራዊት ነው ግጭት ውስጥ የገባው፡፡ አሁን ጭራሽ ቀጥታ ውጊያ ገጥመውናል፡፡”
“ሰው የማሻሻያ እርምጃው የታለ ይለናል፡፡ እኛ የታገልነው አብይን ጠ/ሚኒስትር – ለማን ፕሬዚደንት ለማድረግ ነው ወይ እንዴ ይሉናል፡፡ ስልጣን ይዛችሁ ተቀመጣችሁ እንጂ ምን አደረጋችሁ እያሉ ይወቅሱናል፡፡ ኦሮሞ ማወቅ ያለበት ግን ከባድ ስራ መሆኑን ነው፡፡ ማሻሻያውን ለማምጣት ማንም የማይላተመውን ምሽግ ነው በቆራጥነት ማፈራረስ ያስፈልጋል፡፡ እሱ ፈራሶ መሬቱ ሲደለደል ነው ሊታረስም ሊዘራበትም የሚችለው፡፡ በተቃራኒው አሁን በየቀኑ እየተሰራ ያለው ይህንኑ ማፍረስ ነው፡፡
 የዚህ ሀገር ችግር ግለሰቦችን በመቀያየር የሚፈታ አይደለም፡፡ አንዱን ከወንበር አንስቶ ሌላውን የመተካት ሳይሆን የስርአት ችግር ነው፡፡ የነበረው ስርአት እገሌ የሚባል ግለሰብ እንደ እገሌ የግል ኩባንያ ለእሱ እንዲመቸው የዘረጋው ስርአት ነው – ስርአቱንም ዘርግቶ ሲገለገልበት ቆይቷል፡፡”
“የዛሬ አመት ጭምር የኦሮሚያ መንግስትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲካሰሱ ነበር፡፡ እኔ የክልሉ ፕሬዚደንት ነበርኩ፡፡ የውጭ ጠላት አይደለም ይኸው ሰራዊት ነው ህዝባችንን የጨረሰው ብለን ስንከስ ነበር፡፡ የድንበር ጉዳይ ጎልቶ አይውጣ እንጂ ላለፉት 20 አመታትም ሲያስቸግረን የቆየ ጭቅጭቅ ነበር፡፡ ከባለፈው አመት አንስቶ ጭራሽ በይፋ ጦርነት ተከፍቶብናል፡፡ ሌሎች ናቸው በአሻጥርና ደባ ሲዋጉን የነበሩት፡፡ በማስተዋል አለፍነው አንጂ ችግር ውስጥ እንወድቅ የነበረው አምና ነበር፡፡ አምና በሶማሌ በኩል ከሞያሌ አንስቶ እስከ ሀረርጌ በአንድ ቀን ነው ውጊያ የገጠመን፡፡”
“ከፍተኛ መሳሪያ የታጠቀና ከፍተኛ ስልጠና ያለው ከኋላም ጠንካራ ድጋፍ የሚደረግለት ከ50ሺህ በላይ ወታደሮች ናቸው የዘመቱብን፡፡ አርብቶ አደሩ አይደለም ያንን ያቆመው፡፡ ችግር ውስጥ ብንገባ ያልቅልን የነበረው ያን ዕለት ነበር፡፡
 እዚህ አቅማችንን አይተው ሲያቅታቸው ችግሩን ወደ ደቡብ ወሰዱት፡፡ ሞያሌ ዛሬ ሰላም ይሆናል  – ነገ ደፍርሶ እሳት ይነሳል፡፡ ለምን?  አነኚህ አፍራሽ ኃይሎች በዚያ አካባቢ ለብዙ አመታት ዘርግተውት ሲጠቀሙበት የቆዩት ስውር ኔትወርክ አለ፡፡ እዚያ የዘሩት ዘር ስሩ አልተነቀለም፡፡ በጉጂ እና በጌዴኦ ህዝብም መካከል ድራማ ሰርተውብን ያን ሁሉ ህዝብ አፈናቅለዋል፡፡
 ከወለጋ የመጣችሁ ሰዎች ታውቃላችሁ – የኦነግ ታጣቂዎች ከቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡ 5 ሰዎችን በክልላችን በገደሉበት ዕለት ነው እነሱ ደግሞ በአጸፋው የእኛን ተወላጆች በጅምላ ያፈናቀሉት፡፡ የድንበር ጉዳይ አይደለም ነገሩ፡፡”
“ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር በድንበር ጉዳይ ተዋግተን አናውቅም፡፡ በዚያ በኩል ድንበር እየወረሩ ያሉት ሌሎች ናቸው፡፡ ፖሊስ እንዳንልክ መንገድ ሁሉ ዝግ ነበር፡፡ ወደ ወለጋ የሰዎችን ጅምላ ጉዳት ለመከላከል በመኪና ፖሊስ ለማጓጓዝ በመንገዱ መዘጋት አልቻልንም፡፡ ስለዚህም ለህዝቡ በወቅቱ መድረስ አልቻልንም፡፡ ክልሉ ደግሞ አውሮፕላን የለውም፡፡ እኛ ድንበር ላይ ፖሊስ ከማስፈር ይልቅ ዶ/ር አብይ ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲያበጅ በማድረግ በመጨረሻ የመከላከያ ሰራዊት በአንቶኖቭ አውሮፕላን ተጉዞ ነው ህዝቡን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለውን ከጥቃት ለማትረፍ የተሞከረው፡፡”
“እስኪ ምንድነው መንገድ የሚያዘጋ ችግር የተፈጠረው፡፡ ከምዕራብ የመጣችሁ ሰዎች አታውቁም  በወለጋ ደምቢዶሎ 30 የመንግስት ሰራተኞች ናቸው የተገደሉት፡፡ ግድያውን ተከትሎ ምንም አላደረግንም፡፡ ከ1ሺህ በላይ ነው ሚሊሻዎች ጦር እንዲፈቱ የተደረገው፡፡ ከዚህ በላይ እንዴት ነው የምንታገሰው፡፡ እስኪ የቱ ጋ ነው ትዕግስት ያጣነው፡፡ ወደመፍትሄም አይወስደንም – ይሄ አያግባባንም፡፡”
“ወደዚህ ቤተመንግስት እናንተን ጨምሮ ዛሬ ሁላችንም ነው በጋራ የገባነው፡፡ የኦሮሞ ቤተመንግስት ልናደርገው አይደለም፡፡ የእውነትና የሀቅ ቤተመንግስት ሊያደርገው ነው ኦሮሞ የገባው እንጂ ኦሮሞ ብቻ የሚጨፍርበት ቤተመንግስት ካደረግነው እኛም እንደትናንቶቹ ሰዎች እንሆናለን፡፡ እኛ እሱን አንፈልግም፡፡ በህግ እና በምርጫ ዶ/ር አብይ ከዚህ ቤተመንግስት መውጣት ባለበት ቀን ከዚህ መልቀቅ አለበት፡፡ በጉልበት መቆየት አለበት ብለን አናምንም፡፡ ግን ኦሮሞ በመሆኑ በጉልበት እሳት አቀጣጥለን እናስወጣዋለን የሚሉ ከመጡ ግን እንሟሟታታለን እንጂ አይለቅም፡፡”
Filed in: Amharic