>
5:13 pm - Monday April 19, 0371

እኚህ አቶ ታዮ ደንድአ "የኦሮሞ ፎቢያ" አለባቸው እንዴ? (ያሬድ ሀይለ ማርያም)

እኚህ አቶ ታዮ ደንድአ “የኦሮሞ ፎቢያ” አለባቸው እንዴ?
ያሬድ ሀይለ ማርያም
ኦነግ ገና እግሩ ሸገርን ከመርገጡ ለሕግ እና ለሥርዓት አልገዛም ሲል እና በአደባባይ ወጥቶ ትጥቄን አልፈታም፤ ማን አስፈቺ ማንስ ፈቺ ሊሆን ነው ሲል ነገሩ አላምር ስላለን ብዙ ሰዎች ድምጻችንን አሰምተናል። እኔም ‘ኦነግን እንደ ስለት ልጅ ማንቀራበጡ ይብቃ!’ በሚል የድርጅቱ ባህሪ በጊዜ በሕግ ካልተገራ አገሪቱን ወደ ከፋ ብጥብጥ ይሰዳታል በሚል አቤቱታ በማቅረቤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የክልሉ ተወላጆች ትጥቅ አልፈታም ያለውን ኦነግን ትተው እኔን እና እንደኔ ቅሬታቸውን ያሰሙ ሰዎችን አፍ ለማስያዝ የኦሮሞ ፎቢያ ስላለባችው ነው ብለውን ነበር።
ዛሬ አቶ ታዮ ደንድአ ከታች በምታዩት ቪዲዮ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኦነግ ለአገሪቱ ሕግ አልገዘ ማለቱን እና ከመንግስት ጋር ያድረገውን ስምምነትም በመጣስ በክልሉ ውስጥ ዝርፊያ፣ ግድያ እና የመንግስትን መዋቅር እስከማፍረስ የደረሰ መሆኑን እየነገሩን ነው። እንግዲህ እሳቸውንም የኦሮሞ ፎቢያ ስላለብህ ነው በሏቸዋ። ኦነግን የሚከሱት ለኦሮሞ ጥላቻ ስላለዎት ነው ብላችው አቶ ታዮንም ውቀሷቸው። እኛ ስንናገር የዘር ትርጉም የሚሰጠው እውነታውን ለመደበቅ ወይም በመረጃ የተደገፉ ቅሬታዎችን ለማፈን ከሆነ ግን ያስተዛዝበን ይሆናል እንጂ ቅሬታችንን ከማቆም አያስቆመንም።
ስለ ህውሃት ሲወራ ትግራይን ጠላችሁ፤ ስለ ኦነግ ሲወራ ኦሮሞን ጠላችሁ፣ ስለ አብን ሲወራ አማራን ጠላችሁ እያሉ ጥፋትን ለመሸፈን ወይም ሃሳብን ለመገደብ የሚደረጉ ፍረጃዎች ለአገር አይበጁም። የሚሻለው ነገሮችን በወቅቱ እና በቅን ልቦና መነጋገር ነው።
Filed in: Amharic