>

በአቶ ገለሣ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ!!! (ኢዜአ)

በአቶ ገለሣ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ!!!
ኢዜአ
በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከተለያዩ የዓለም አገራት እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኦሮሞ ፓርቲዎች 15 ደርሰዋል!!
 
አዲስ አበባ ታህሳስ 20/2011 በአቶ ገለሣ ዲልቦ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ብርቱካን አያኖና የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ተቀብለዋቸዋል።
ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ አገር ቤት የገቡት 22 የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት መንግሥት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ መሆኑን አቶ ገለሣ ገልጸዋል።
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ፓርቲያቸው በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከተውም ተናግረዋል።
“እንቅስቃሴውን በበጎ አይን ነው የተመለከትነው፤ ደግፈነዋልም፤ የደገፍነውም ያለ ምክንያት አይደለም፤ የተወሰዱት እርምጃዎች የሚያበረታቱና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እናደርጋለን ተብሎ የሚነገረው ተስፋ ሰጪ መሰሎ ሰለታየን ነው፤ ስለዚህ በዚህ መልኩ ነው ያየነው” ብለዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ፓርቲያቸው ለቆመለት የፖለቲካ ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብን ከጎኑ በማሰለፍ በሠላማዊ መልኩ ትግል ለማድረግና ተሳትፎውን ለማጠናከር መዘጋጀቱንም ነው የጠቆሙት።
የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዳንኤል ዲሳሳም መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ አስቀድሞ ፓርቲው መቀበሉን ገልጸው የተሻለ ተሳትፎ ለማድረግ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘግይተው መምጣታቸውም ለውጡን አስታከው ፍሬያማ ተሳትፎ ለማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ከሁሉም ወደ ኋላ ቀርተን ነው የመጣነው ምክንያቱም እያሰብንበት ነበር እንዴት መሥራት እንደሚቻል፤ አስበንበት ነው የመጣነው ግን በአጠቃላይ ሁኔታው የሚያሰራ ስለሆነ፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመቺ ነው ብለን ነው የመጣነው”  ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ በአቶ ገለሣ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ወደ አገር ቤት መግባቱ የኦሮሞን ጥያቄዎች በተደራጀ አኳኋን ለመምራት ያስችላል ብለዋል።
በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች አንድነት ፈጥረው የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮች ጋር አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ኦዴፓ በአቶ ገለሣ ዲልቦ ከሚመራው ኦነግ ጋር በጋራ የመሥራት ፍላጎት ስላለው እንዴትና በምን መልኩ የሚለውን በቀጣይ በውይይት ይወሰናል ብለዋል።
በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከተለያዩ የዓለም አገራት እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኦሮሞ ፓርቲዎች 15 ደርሰዋል።
Filed in: Amharic