>

የማሰቃያው ጉድጓድ በቡራዮ!!! (በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

የማሰቃያው ጉድጓድ በቡራዮ!!!
በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን
ጋዜጠኞቹ የደረሳቸው ወሬ እጅጉን ጆሮ ገብ ነው፡፡ ጥቆማውን እንደሰሙ ከቢሮ ወደቦታው ለመሄድ አላመነቱምለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሸክፈው ከቢሮ የወጡት በጥድፊያ ነበር፡፡ በሩጫ ወደ ቦታው አመሩ፡፡ ለምሳ እንኳ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡የሰሙትን ወሬ ሄደውበካሜራ በመቅረጽ፣ ቃለመጠይቅ በማድረግ ለሕዝብ ለማድረስ ቸኩለዋል፡፡
ይህንን ጥቆማ የላከው የቡራዩ ከተማ መስተዳድር ነው፡፡ የመንግሥት አካል መቼም ቢሆን የተጣራ መረጃ እንደሚልክላቸው እርግጠኞቸ ሆነዋል፡፡ ቡራዩን የሚመራው የመንግሥት አካል በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የሚሾም እንደሆነ ያውቃሉ፡፡እናም በቂ መረጃ እንዳላቸው አድርገው ወደ ቦታው ሄዱ፡፡ በአገሪቱ አለ የተባለውን ቴሌቭዥን አርማና መለያ ያለውን መኪናና የካሜራ ማይክ ይዘው ቡራዩ ደረሱ፡፡
በቦታው ሲደርሱ አንድ ክልላዊ የመንግሥት ቴሌቭዥን አለ፤ ሌላ የግል ግን በክልሉ ቋንቋ የሚሰራ ቴሌቭዥንም በቦታው ተገኝቷል፡፡ከአዲስ አበባ የሄዱት ጋዜጠኞች እየተጠበቁ ነበር፡፡ የተሰማው ወሬ ሁሉንም ጋዜጠኛ አጓጉቷል፡፡ ከክልል ሚዲያ የመጡት ‹ጋዜጠኞች› ግን ገና በወሬው ተበሳጭተዋል፡፡ ስንደፈር ኖረናል በሚል ስሜት እየፎከሩ ነው፡፡ መረጋጋት አልታየባቸውም፡፡ ጉዳይ ሊያጣራ የሄደ ጋዜጠኛ ሳይሆን ጉዳዩ መደረጉን አምኖ የተነሳ ተበዳይ ይመስሉ ነበር፡፡
የቡራዩ ከተማ መስተዳድር፣ሚዲያዎችን ጠርቶ ‹‹ኑ ጉዴን እዩልኝ፣ ለሕዝብም አድርሱልኝ›› ያለው ነገር ጋዜጠኞቹን ስሜታዊ አድርጓቸዋል፡፡ጉዳዩ፣ የቀድሞው አስተዳደር ሰዎችን ያሰቃይበት የነበረ የምስጢር ጉድጓድ በከተማው አለ የሚል ነበር፡፡
አሁን የሚፈለገው ሚዲያ ሶስቱም መጥቷል፡፡ የከተማው መስተዳድር የመደባቸው ሰዎች ጉድጓዱን ለማሳየት ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል፡፡ የቀረው ጉድጓዱን ማየት ነው፡፡ በጉድጓዱ ውስጥ ታስረን ተሰቃይተናል ያሉ ሰዎችም በከተማ መስተዳድሩ አማካኝነት ለቃለመጠይቅ ተዘጋጅተዋል፡፡
ይህንን ጉብኝት እየመራ ያለው የመንግሥት ሹመኛ ‹‹በቅድሚያ ወደ ጉድጓዱ ጋር ከመሄዳችን በፊት፣ ሌላ ጉዳይ አሳያችኋለሁ፡፡እዚህ ከተማችን ላይ በጉድጓዱ ውስጥ እንዲሰቃዩ የሚደረጉ ሰዎችን ከሌላ ቦታ ጭኖ የሚያመጣ እና ካሰቃየም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ የሚወስድ ሄሊኮፕተር አንድ ቦታ አለ፡፡ መጀመሪያ ወደ ጉድጓዱ ከመሄዳችን በፊት ወደዚያ እንሂድ፤እርሱን መጎብኘት አለባችሁ›› አላቸው፡፡
ጋዜጠኞቹ ተስማሙ፡፡ የክልሎቹ ጋዜጠኞች ግን ብስጭታቸው ባሰ፤መረጋጋት አልቻሉም፡፡ ‹‹ስንደፈር ኖረናል በሚል ስሜታቸውን መቋቋም ተሳናቸው፡፡ከአዲስ አበባ የሄዱት ጋዜጠኞች ግን ግራ ቀኙን ከስሜት በጸዳ መልኩ ለመቃኘት እየሞከሩ ነው፡፡
ሹመኛው ወደተባለችው ሄሊኮፕተር ወሰዳቸው፡፡ በአንድ የተንጣለለ ግቢ ውስጥ ሸራ የለበሰ ሁለት ግዙፍ ነገር ይታያል፡፡ሲታይ ያስፈራል፡፡ጌሾ የመሰለ ሸራ አንዳች ነገር ሸፍኖ ተዘርግቷል፡፡ የከተማው ሹመኛ ይዟቸው የመጣ ፖሊሶች ሸራውን በቄንጥ ገለጡት፡፡ሲታይ አፈር ያሻገታቸው፣ ጸሀይ ያበለዛቸው፣ ዝናብ ያደበዘዛቸው ሁለት ሄሊኮፕተሮች ናቸው፡፡
ለቃለመጠይቅ ከተዘጋጁት ሰዎች አንዱ ‹‹ይህ አውሮፕላን ሲመጣ የነበረው ማታማታ ነው፡፡ ሌሊት በጉድጓዱ ውስጥ ሲደበደቡና ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች ጠዋት ጠዋት ተጭነው የሚወሰዱት በዚህ ሄሊኮፕተር ነው፤ በጉድጓዱ ውስጥ እጄን ከእግሬ ጋር አስረው ይገርፉኝ ነበር፤ ከዚያም በፈላ ዘይት ይጠብሱኝና ወደሄሊኮፕተሯ አምጥተው ይወስዱናል›› አለ፡፡ የክልሉ ጋዜጠኞች ይህንን ሰው ቃለመጠይቅ አደረጉት፡፡ይህንኑ ተናዘዘ፡፡
ከአዲስ አበባ የሄደው ጋዜጠኛ ግን ጉዳዩን ተጠራጠረ፡፡ ሁለቱም ሄሊኮፕተሮች ከካፒቴኑ ውጭ አንድ ሰው ብቻ ነው መያዝ የሚችል ቦታ ያላቸው፡፡ ቃለመጠይቅ ተደራጊው እንደተናገረው አይደለም፤ ሰዎችን ለመጫን የሚሆን ቦታ የላቸውም፡፡ ይልቅስ ከኋላ ትልልቅ ሲሊንደር ያላቸው ናቸው፡፡
ጋዜጠኛው ተዟዙሮ ሄሊኮፕተሮቹን አየ፡፡አንዱ የምሥራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ የሚረጭበት ጸረ-ተባይ ሄሊኮፕተር እንደሆነ የሚገልጽ ጽሁፍ አነበበ፡፡ እንደገና ያኛውን ሄሊኮፕተር አየው፡፡ ክንፍ የለውም የተሰበረ ነው፡፡ አርጅቷል፡፡ አገልግሎት ለመስጠት የማይችልና መለዋወጫዎቹ እንኳን የማይሰሩ መሆኑን አወቀ፡፡
‹‹በአምናው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዘመን በዚህ አውሮፕላን ነበር ታፍሰን የምንወሰደው›› ሲል የተናገረውን ቃለመጠይቅ ተደራጊ ከክልል የመጣው ጋዜጠኛ፣‹‹በዚች ሄሊኮፕተር እንዴት ልትጫኑ ትችላላችሁ፤ ለሰው መጫኛ የሚሆን ቦታ እኮ የላትም›› ብሎ አልጠየቀውም፡፡
የሄሊኮፕተሮቹን ጉዳይ አጣርተው ጉድጓድ ወደተባለው ቦታ ወሰዷቸው፡፡ አንድ የተንጣለለ ግቢ ውስጥም አስገቧቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡ ጉድጓዱ እዚህ ግቢ ነው ተብሏል፡፡በዚህ ጉድጓድ ውስጥም ተሰቃይተናል ያሉ ሰዎች ቃለመጠይቅ ለመስጠት ተከትለው ገቡ፡፡
የተባለው ጉድጓድ፣ ብዙ የቡራዩ ወጣቶችና ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች የተሰቃዩበት የቶርቸር ማዕከል እንደሆነ ለጋዜጠኞቹ ተነግሯቸዋል፡፡ ጉድጓዱ ወደ አለበት ቦታ ሄዱ፡፡ከከተማ የመጣው ሹመኛ ‹‹እዚህ ጋር ነው፤ በዓይኔ በብረቱ አይቼዋለሁ›› ብሏል፡፡
ጉድጓዱ ግን በተባለወ ቦታ የለም፡፡ ተሰቃይተንበታል ያሉት ልጆችም ጉድጓዱን ፈልጎ ማግኘት አቃታቸው፡፡ ጉድጓዱ ቢፈለግ ቢፈለግ ጠፋ፡፡ ወጡ ወረዱ፡፡ የለም፡፡
ሼዱ ውስጥ ያሉትን ቤቶች በሙሉ ፈለጉ፡፡ ጉድጓዱ የለም፡፡ ‹‹ቅድም እኮ እዚሁ ነበር›› አለ አንደኛው፡፡ተፈለገ፡፡ጠፋ፡፡የከተማው መስተዳድር ባለሥልጣን እፍረት አልተሰማውም፡፡ ጋዜጠኞቹ ‹‹ጉድጓዱ የታለ›› ብለው ሲጠይቁት፣‹‹እርሱንማ እናንተ ኢንቨስትጌት አድርጉ›› ብሏቸው አረፈው፡፡
ከአዲስ አበባ የሄደው ጋዜጠኛ፡፡ የገጠመውን ለኤዲተሩ ደውሎ አሳወቀ፡፡ የሄሊኮፕተሮቹን ጉዳይ እያጣራሁ እጠብቅሃለሁ ወደ ቢሮ ና አለው ኤደተሩ፡፡
ኤዲተሩ ጉዳዩን እዚያም እዚህም ደውሎ አጣራ፡፡ ሄሊኮፕተሮቹ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስር የሚገኘው የትራንስ ኔሽን ኃ/የተ/የግል ኩባንያ መሆናቸው ታወቀ፡፡ የአረም ኬሚካል ለመርጨት ሱዳን በኪራይ ተሰጥተው የተሰባበሩ፣ አንደኛው ከአመት በፊት የወደቀ ሄሊኮፕተር መሆኑን፣ ተሰባብሮ ከሚቀልጥ ለኢንጅነሪንግ ትምህርት ማስተማሪያነት ቢውል የተሻለ ነው በሚል ሃሳብ ቡራዩ ወደሚገኘው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከዓመታት በፊት የተወሰዱ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ ይህንን ጉዳይም ከዓመታት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦት እንደነበር የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው አስረዱ፡፡ “በጉድጓድ ተቀቅለን በሄሊኮፕተር እንጫናለን” ያሉት ሰዎችም በራሱ በከተማ አስተዳደሩ ሹመኞች የተፈጠረችን ሴራ እንዲጎነጉኑ የተውጣጡ መሆናቸው ታወቀ፡፡
Filed in: Amharic