>

የሙታኖች ጩኸት!  (ኤርሚያስ ለገሰ)

የሙታኖች ጩኸት! 
ኤርሚያስ ለገሰ
መቀሌ ላይ የውሸት አለቆች የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን እና ጌታቸው ረዳ ዲስኩር ለማሰማት አሰፍስፈዋል። እነዚህ የቀድሞ ስርአት ናፋቂዎች ምን ሊናገሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ መገመት እጅግ በጣም ቀላል ነው። የአቶ በረከት ንግግር የመጨረሻ ኑዛዜ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዲስኩሮቹ በከፊል፣
#ህውሓቶች ፈላጭ ቆራጭ የነበሩባት ” አዲሲቷ ኢትዮጵያ” በፓለቲካው፣ በኢኮኖሚውና ማህበራዊ መስክ የምታስጐመዥ፣ ባለከባድ ሚዛን፣ የአፍሪካ ነብር ነበረች። ለዚህ አንፀባራቂ ድል ብፃይ መለስ ዜናዊ ዘላለማዊ ክብር ይገባዋል።
(* በተለይ በረከት በኢኮኖሚ ዘርፍ የተመዘገበውን እድገት ለመዘገብ የቁጥር ቶፋውን ይዘረግፋል። የኢትዮጵያውያን የእድሜ ጣራ 65 የደረሰው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሆኑን ይፋ ያደርጋል። የልማታዊ መንግስትን ባህሪያት ይተነትናል።)
#የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የባለሁለት አሃዝ እድገት የተገታው፣ አገሪቷም ቀውስ ውስጥ መግባት የጀመረችው አቶ ሐይለማርያም ስልጣኑን ከያዘ ጀምሮ ነው። የህውሓት/ ኢህአዴግ ህገ መንግስት በቅጡ አንብቦ መረዳት የተሳነው ሐይለማርያም ደሳለኝ ድርጅቱን እና አገሪቷን እንደ ግመል ሽንት የጐተተ ደንታቢስ፣ ዝርክርክ፣ መወሰን የማይችል አሳፋሪ ሰው እንደነበረ እንሰማለን።
( * የበረከት የመጨረሻ ፍላጐት መፍትሔ ማምጣት ሳይሆን ከሚዲያው ላለመጥፋት እና አነጋጋሪ ሆኖ ለመቆየት እንደመሆኑ መጠን እጅግ ጠብ አጫሪ እና ተንኳሽ ቃላትን እንደሚጠቀም ይጠበቃል)
#አገሪቷን በዋናነት እንድትታመስ እና ወደ መበታተን ጫፍ እየወሰዳት ያለው አዴፓ ( የቀድሞ ብአዴን) ነው። አዴፓ የተሰጠውን ክልል መምራት ስላቃተው በማንነት እና የድንበር አወሳሰን ሽፋን የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል።
( * በተለይ በረከት የአዴፓን መሪዎች ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ -አማራ፣ ፀረ -ትግራይ፣ ፀረ -አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ፀረ -ልማታዊ መንግስት፣ ፀረ- ህውሓት፣ ፀረ -ደብረጺዮን፣ ፀረ- በረከት ለማለት በርካታ ኢንፎርሜሽኖች ከኪሱ ያወጣል)
#በኢህአዴግ ውስጥ የተቀጣጠለው ለውጥ ፋና ወጊው ህውሓት ነው። ሌሎቹ ድርጅቶች አባታቸው ህውሓትን አድንቀውና በአርአያነት ወስደው ጥልቅ ተሀድሶ ለማድረግ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የአንዳንዶቹ ትምህርት አቀሳሰም ( አዴፓና ኦዴፓ) እንደ ሰነፍ ተማሪ በመሆኑ ለውጡ ተንገራግጮ እንዲቆምና እንዲቀለበስ አድርገዋል።
( * በተለይ በረከት በፓርቲ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ከስድስት አመት በፊት ሲጐተጉት እንደነበረ እና የለውጥ ፍኖተ ካርታ ስሎ እንደነበር በቁጭት ይናገራል)
#የፓለቲካ እስረኞች ፍቺ መነሻ ሃሳብ ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ያቀረበው ህውሓት ነው። ሌሎቹ ድርጅቶች የተወያዩት ህውሓት ባፈለቀላቸው አዲስ ሃሳብ እንጂ ከመጀመሪያውም በአጀንዳ የያዙት አልነበረም።
( * በተለይ አስመላሽ ወልደስላሴ በቁጭት ውስጥ ሆኖ የፓለቲካ እስረኞች ፍቺ ህውሓት መስዋእትነት የከፈለበት እንደሆነ ይናገራል። ይሁን እንጂ አስመላሽ እነ ፕሮፌሰር መረራ እና እስክንድር ነጋ ይፈቱ በሚል በአቶ ሐይለማርያም እና ” ቲም ለማ” አቋም ሲወሰድ ከኮሚቴው ራሱን ማግለሉን በፍፁም አይነግረንም።)
#የኢትዮ – ኤርትራ ግንኙነት እንዲጀመር መነሻ ሃሳብ ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ያቀረበው ህውሓት ነው። ሌሎቹ ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተወያዩት እና ያፀደቁት በህውሓት አቅራቢነት ነው።
( * እዚህ ላይ አቶ በረከት የተፈጠረው ግንኙነት አቅጣጫውን መሳቱን እና ኢህአዴግ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እጅ መዳፍ መውደቁን ህውሓትን አስፈቅዶ ሊናገር ይችላል።)
#ከሌሎቹ አካባቢዎች ተለይቶ በትግራይ ውስጥ መረጋጋት እና ሰላም የሰፈነው በትግራይ ህዝብ ተሳትፎ እና የህውሓት ቁርጠኛ አመራር ሰጪነት ምክንያት ነው። ፀረ -ሰላም ሀይሎች የትግራይ ህዝብ እና ህውሓት ላይ ጦርነት የከፈቱት የራሳቸውን አካባቢ መቆጣጠር ስለተሳናቸው ነው።
( * እዚህ ላይ ጌታቸው ረዳ የህውሓት ህገ መንግስት እየተጣሰ እንደሆነ፣ ከዚህ በኃላ ህውሓትና የትግራይ ህዝብ የህገ መንግስት ጥሰትን በቸልታ እንደማይመለከቱት ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።)
#ልማታዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንግስታችን በኒዮ ሊብራል ሃይሎች እየተጠለፈ ነው።
( * በተለይ አቶ በረከት የኒዮ ሊብራልን ምንነት፣ ማንነት፣ እንዴት መንግስት በእነዚህ ሀይሎች ተጠልፎ ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደገባ ሰፊ ገለፃ ሊሰጥ ይችላል)
ምክረ -ሃሳብ
በእኔ እምነት ይሄ ሁሉ ዲስኩር ከመቀሌ ተሻግሮ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ግፋ ቢል ለአንድ ሁለት ቀን የፌስቡክ አጀንዳ ሊሆን ይችላል። አይደለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ፣ አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ የመቀሌው ስብሰባ በተጠናቀቀ ማግስት መግለጫ ቢሰጥ ውይይቱ ከመቀሌው አዳራሽ መሻገር አይችልም። እናም ለአቶ ሐይለማርያም ቅርበት ያላችሁ የቀድሞ ወዳጆቼ ምክረ ሃሳቤን አድርሱልኝ። የተንጫጫውን ተልባ በአንድ ሙቀጫ ውቀጠው በሉት!!
Filed in: Amharic