>
5:13 pm - Friday April 20, 5240

የዜጎች የፍትሕ ጥያቄ በሸገር-መቀሌ የፖለቲካ ጡዘት እንዳይጠለፍ!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

የዜጎች የፍትሕ ጥያቄ በሸገር-መቀሌ የፖለቲካ ጡዘት እንዳይጠለፍ! 
ያሬድ ሀይለማርያም
 
በማዕከላዊ እስር ቤት ከተፈጸመው ባልተናነሰ መልኩ ከጋንቤላ እስከ ዑጋዴን፣ ከጎንደር እስከ ሞያሌ፣ ከአፋር እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከትግራይ እስከ ኮንሶ ባሉት የአገሪቱ ግዛቶች ሁሉ ግፍ በገፍ ተፈጽሟል!
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጥረት ወንጀል ፈጽመው የተደበቁትን ብቻ ሳይሆን ወንጀል ፈጽመው በአደባባይ የሚንጎማለሉትንም ሆነ ወንጀለኞችን የሸሸጉትን መጨመር አለበት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አሥርት አመታት የሰብአዊ መብቶች የተፈጸመው እና ሰዎች በግፍና አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዲሰቃዩ የተደረጉት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ነው። አድራጊዎቹም በሁሉም ድረጃ የሚገኙ ሹማምንት እና የጸጥታ ሰራተኞች ናቸው። የተለየ ቀለም፣ ዘር፣ ኃይማኖት ወይም ሌላ የማንነት መገለጫ የላቸውም። እንደተበዳዩ ስብጥር ሁሉ በደል አድራሾቹም የተሰባጠሩ ናቸው።
በማዕከላዊ እስር ቤት ከተፈጸመው ባልተናነሰ መልኩ ከጋንቤላ እስከ ዑጋዴን፣ ከጎንደር እስከ ሞያሌ፣ ከአፋር እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከትግራይ እስከ ኮንሶ ባሉት የአገሪቱ ግዛቶች ሁሉ ግፍ በገፍ ተፈጽሟል።
ይህን ሰፊ እና ውስብስብ ችግር በይቅርታም ይታለፍ ወይም አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብ ጉዳዩ በጥንቃቄ ተይዞና በገለልተኛ አካል ተመርምሮ፣ ማስረጃ ተጠናክሮ እና የአጥፊዎቹ ማንነት በስም እና በኃላፊነት ደረጃ ተገልጾ ለሕዝብ እና ለአገሪቱ ፓርላማ መቅረብ አለበት።
አሁን በመገናኛ ብዙሃን በተዝረከረከና ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ እየቀረበ ያለው የግፈኞች ስንክ ሳር እና የተበዳዮች ሰቆቃ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ትላንት የወጣው ዛቻና ማሰራሪያ ያዘለ መግለጫ የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ በአግባቡ ከመመልስ ይልቅ ሌሎች ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፤
– ከፍተኛ የመብት ጥሰት የፈጸሙ እና ከተጠያቂነት ማምለጥ የሌለባቸው ሰዎች ከወዲሁ አገር ጥለው እንዲሸሹ እድል ይፈጥራል። የተወሰኑትም በቅርቡ አገር ጥለው መሸሻቸው እየተገለጸ ነው። መንግስት በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ አውጥቶ እና ሰዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ለሚዲያ ዘገባው ቀስ ብሎ ይደረስበት ነበር። ከዛ ይልቅ በሙስናውም ጉዳይ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ የማሰሪያ ማዘዣውን ይዞ መጀመሪያ የሚሮጠው ወደ ሚዲያዎች ነው። እነ እገሌን ለማሰር ማዘዣ ወጥቷል እየተባለ በየሚዲያው በሰነድ በተደገፈ መልኩ የሰዎች ስም ተዘርዝሮ ይወጣል። ይህ ማለት ልንይዛችው ስለሆነ ከቻላችው አምልጡ ማለትም ነው። ከዛ በኋላ ያለው ሰዶ ማሳደድ የቶም እና ጄሪ አይነት ጨዋታ ነው የሚሆነው። መንግስት በሕግ አንድን ሰው ለመያዝ የሚያስፈልጉትን ቅደ ዝግጅቶች ያድርግ እንጂ የሚዲያ ልፈፋው ለምን አስፈለገ?
– አብዛኛው በደል አድራሽ በመንግስት ቁጥጥር ስር ባልዋለበት፤ ገሚሶቹም የመንግስት ተሿሚዎች ሆነው እየሰሩ ባለበት በዚህ ወቅት ተበዳዮች ፊታቸው እየታየ እና ማንነታቸው እየተገለጸ በመገናኛ ብዙሃን በዚህ መልኩ መቅረባቸው ለበለጠ ስጋት እና አደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋል። ወንጀላቸውን ለመደበቅ የሚጥሩ ባለሥልጣናት የስቃይ ሰለባዎቹን ለማስፈራራትም ሆን ለማስወገድ አቅም እንዳላቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በደላቸውን ከገለጹ በኋላ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው። እነዚህ በመገናኛ ብዙሃን ወጥተው ምስክርነት የሰጡት ሰዎች ተጠርጣሪዎቹ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እስኪውሉ ድረስ የመንግሥት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። ይህ አይነቱ አሰራር በብዙ አገሮች የተለመደ ነው። ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ እና ተበዳይ የሆኑ አቤቱታ አቅራቢዎችን በቀላሉ በማስወገድ ወንጀለኞች ከተጠያቂነት ለመዳን ሙከራ እንደሚያደርጉ ይታወቃል።
– እጅግ ሙያዊ ስነ-ምግባር በጎደለው መልኩ አኬልዳማ፣ አረካዊ አራፋት እና ሌሎች የሃሰት ዶክመንተሪ ፊልሞችን እያቀናበሩ በእነዚሁ ግፉዋን ላይ ስም ሲያጠፉ እና ሲያጠለሹ ለነበሩ መገናኛ ብዙሃን ይህን አይነት አሳሳቢ እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ አገራዊ ጉዳይ አሳልፎ መስጠት ሌላው አላፊነት የጎደለው የመንግስት እርምጃ ነው። እነዚህ ጉዳዮች የቀረቡበት ሁኔታ ከፍትህ ፍላጎት ይልቅ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ለማሳካት በሚመስል መልኩ ነው የቀረቡት። ይህ ደግሞ ብዙ ሰው አገሪቱ ውስጥ ይፈጸም ለነበረው የመብት ጥሰት መጠን፣ ባህሪ እና የፈጻሚዎች ማንነት ላይ እጅግ የተዛባ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርጎታል።
– የዛሬዎቹ ተደማሪ ባለሥልጣናት እና የክልል ፖሊስ እና የደህንነት ሹሞች በአብዛኛው የመብት ጥሰት ወንጀል ተሳታፊዎች ናቸው። ናዝሬት ላይ የወንድ ብልት ያኮላሹት፣ አንቦ ላይ ጥፍር የነቀሉት፣ ደብረ ማርቆስ ላይ እስረኛን በቁሙ አንገቱ ድረስ ቀብረው ከነነፍሱ በላዩ ላይ ፕላስቲክ በእሳት እያቀለጡ ያሰቃዩት፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ እስር ቤቶች በድብደባ ብዛት ታሳሪዎችን አሰቃይተው የገደሉት፣ በድሬደዋ፣ በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በአሳይታ እና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በእሥረኞች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና ስቃይ የፈጸሙት የየክልሉ ተሿሚዎች እና የደህንነት ሠራተኞች ናቸው። አዲስ አበባ ፌዴራል ኮሚሽኑ ቢሮ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ሌሊቱን ሙሉ ሲገረፍ አድሮ ነፍሱ ስታልፍ የራሱን ልብስ ተልትለው ከሰቀሉት በኋላ እራሱን እንደሰቀለ አድርገው አስከሬኑን ለቤተሰቡ የሰጡት የሳሪስ አካባቢ ነዋሪና የአምስት ልጆች አባት የሆነውን የአበራ ይሄን በደለና ድምጽስ ማን በኢቲቪ መጥቶ ይንገርለት። አበራ ይሄ የታሰረው በኦነግ አባልነት ተጠርጥሮ ነው።
መንግስት ፍትህ ለማስፈን የጀመረው ጥረት እንዲሳካ እና ሂደቱም በፖለቲካ ሸር ተጠልፎ የታለመለትን ግብ ሳያሳካ ከመንገድ እንዳይቀር ከተፈለገ ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ ከወዲሁ ሊደረግ ይገባል።
አንቦ እና ባህርዳር ላይ የሰው ብልት ያኮላሸ እና ስቃይ የፈጸመ ገራፊን ወንጀለኛ ለውጡን እልል እያለ ስለተቀበለ እና ሰለተደመረ ባላየ እያለፍን ማዕከላዊ ላይ ካተኮርን አካሄዳችን ላይ ሽግር አለ። ማዕከላዊን ባልታሰርበትም ውስጡ ያለውን አደረጃጀት በደንብ አውቀዋለሁ። የመብት ጥሰት ለማጣራት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ኃላፊዎቹ ቢሮም በተደጋጋሚ ገብቼ ያለውን ሁኔታ ለማየት እድል አግኝቻለው። ቦታው አዲስ አበባ ላይ ቢሆንም ግቢው ውስጥ ያለው መንፈስ ግን መቀሌ ያለህ ነው የሚመስለው። ከፈታሽ ፖሊስ እስከ ከፍተኛ ኃላፊ ድረስ ያሉት ሰዎች ነባር ተጋዳላይ እና የህውሃት ደህንነት ኃይሎች ናቸው። ከሌላ ብሔር የመጡ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢኖሩም ቁጥራቸው ከግምት የሚገባ አይደለም። እዚህ እስር ቤት ውስጥ አሳሪውም፣ መርማሪውም ሆነ ደብዳቢው ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች ናቸው። ይሁን እና መዘንጋት የሌለበት እዚህ እስር ቤት የሚመጡት ከፍ ያለ ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።
በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተገለጹትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስፈራሪያነት ወንጀለኞችን ከተደበቁበት እንይዛለን በሚል የለቀቁት የትላንቱ መግለጫ በግልጽ የሚያሳዩት አልደመር ብሎና አኩርፎ መቀሌ በመሸገው የወያኔ የወንጀል ግብረ ኃይል ላይ ነው። ይህ ኃይል ከፍተኛውን የወንጀል አድራጎት መፈጸሙ የሚጠራጠር የለም። በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርት እንዲቀርቡ ስንወተውት ቆይተናል። ወንጀል ከሰሩት ውስጥ የተደበቀው ይህ ቡድን ብቻ ነው። ሌላው በነጻነት እየተንጎማለለና ሹመት ያጽና ተብሎም ቀጥሏል። ይህ አይነቱ አካሄድ የመንግስትን ጥረት ለፍትህ ሳይሆን የፖለቲካ ፍትጊያውን ለማሸነፍ ብቻ እንደ ስልት የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ እንዲታይ ያደርገዋል።
መቀሌ የመሸገው እና እፍረት በተፈጥሮው የማያውቀው የወያኔ ቡድንም ይህን ክፍተት ተጠቅሞ እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት በማስመሰል ዛሬም በሕዝቦች ቅራኔ ለመነገድ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። አሁን የተጀመረው የፖለቲካ መጓተት እና የተዘበራረቀ የፍትህ ሂደት ለእነዚህ የወንጀል ተጠርጣሪዎች መደበቂያ ዋሻ እንዲፈጥሩና ገሚሶቹም ከአገር እንዲሸሹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው።
አሁንም የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይህን ችግር በቅጡ ቢይዘው ይሻላል
Filed in: Amharic