>

ሕገ መንግስቱ ይከበር!  አዎ ይከበር!!! (በወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ሕገ መንግስቱ ይከበር!  አዎ ይከበር!!!
አዶልፍ ኤክማንም …...
.
ዘግናኝ ጥፋት የፈፀመ የናዚ ፊት አውራሪ ነው፦ አዶልፍ ኤክማን። የሂትለር ቀኝ ከሚባሉት የፍጅት መሃንዲሶች መሃከል አንዱ እና ዋነኛው አዶልፍ ኤክማን በአይሁዳውያን ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ የኦሽዊትዝን ካምፕ ፀያፍ ድርጊት የመራ፤ አይሁዶችን በአሲድ እንዲቃጠል ያደረገ፣ የሰው ልጅ ከመሞቱ በፊት በቁሙ ቆዳው እንዲገፈፍ፣ ተገፎም ጌጥ እንዲሰራበት ያደረገ …ወዘተ ነው፡፡ በዚህም ተግባሩ  ነው “ሳጥናኤል” የሚል ቅጥያ ስም የተሰጠው፡፡
.
ይህ ሰው የጀርመኖችና የጦር ተባባሪዎቻቸው እብሪት ከተነፈሰና የሽንፈትን ፅዋ ከተጎነጩ በኋላ ግን ጠፋ፡፡ ራሱን ለውጦ ወደ አርጀንቲና ተሻገረ፡፡  በአጭሩ፤ በፍጅቱ በደል ከደረሰባቸው አይሁዳውያን ተሰወረ፡፡ አይሁዳውያኑ ግን “ጠፋ” ብለው ዝም አላሉም፡፡ የኤክማንን ዱካ ማነፍነፉን ተያያዙት፡፡
.
ለጊዜው የተሰወረው ኤክማን፣  እስከወዲያኛው ሊሸሸግ አልቻለም፡፡ ራሱን ለውጦ በአርጀንቲና እንደሚኖር ደረሱበት፡፡ የስለላና የደህንነት መስሪያ ቤቶቻቸውን ቀልጣፎች ላኩበት፡፡ አፈፍ አደረጉት፡፡ በአስገራሚና ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ አየር ማረፊያውን አሳልፈው አንከብክበው ወደ እስራኤል ይዘውት መረሹ፡፡ ለፍርድም ቀረበ፡፡
.
በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተፈፀሙ ዘግናኝ ወንጀሎች 15 ክሶች ቀረቡበት፡፡ ጥፋተኝነቱ ተረጋገጠበት፡፡ በሞት እንዲቀጣም ተፈረደበት፡፡ ቅጣቱም በስቅላት ተፈፀመበት፡፡ አስከሬኑም በሚስጥራዊ ስፍራ ተቃጥሎ በሜዴትሬኒያን ባህር ተበተነ፡፡ የአዶልፍ ሄክማን የጥፋት ምዕራፍ ተዘጋ፡፡
.
የእኛው ሀገር “አዶልፍ” ነገርም ልክ እንደዛው የሆነ ይመስላል፡፡ ለጊዜው ተሸሽጓል፡፡ በዚህም የተነሳ “ሕገ መንግስቱ ይከበር” እንላለን፡፡ ሰብዓዊ መብት ጠሰት የፈፀሙ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ አንላለን!
.
ወንጀለኞችን አቅፎ የሚይዝ (ሚለማመጥ) ሕገ መንግስት፣ ሕገ መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡ እናም..ሕገ መንግስቱ ይከበር!
Filed in: Amharic