>

የመቐለ ሰልፍ ላይ የዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ሙሉ ንግግር 

የመቐለ ሰልፍ ላይ የዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ሙሉ ንግግር 
የተከበራችሁ የመቐለና አከባቢዋ ነዋሪዎች፣ 
የተከበራችሁ የሃይማኖት መሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች፣ 
የተከበራችሁ ነባር ታጋዮች እና የጦር ጉዳተኞች፣
ክቡራትና ክቡራን፡፡
በቅድሚያ ህገ-መንግስት የፀደቀበትን እለት ለማስታወስ የህገ-መንግስት ጥሰት እንዲከበር ያላችሁ ፅኑ አቋምና ዝግጁነት በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለፅ ለተገኛችሁ ሁሉ ያለኝን አድናቆትና ክብር በመግለፅ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
እናንተ የደማቅ ታሪክ ባለቤቶች ጀግኖች ለዚች ቀን እንኳን አደረሳችሁ፡፡ዛሬ ህዳር 29 የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም የፍትህ ህገ-መንግስታዊ ምላሽ ያገኘበት ቀን ነው፡፡ በእኩልነትና በፍላጐት የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ያላት ኢትዮጵያ ለመገንባት ቃል የገባንበት ቀን ለማስታወስና ህገ-መንግስት ሳይሸራረፍ እንዲከበር የትግራይ ህዝብ ድምፁ እንዲሰማ አደባባይ መውጣት በትግሉ ያረጋገጠው መብቱ መሆኑ ኩራት ሊሰማው ይገባል፡፡
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ 
በደምና በአጥንትህ የክፍለ ዘመኑ ልዩ ታሪክ በማስመዝገብ በጥፋትና መበታተን ላይ የነበረችውን ሃገር በህገ – መንግስት የምትመራ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሃገር እንድትሆን መተኪያ የሌለው አስተዋፅኦ ያበረከተክ በመሆንህ እንደ ህዝብ ክብር ይገባሃል፡፡
በቋፍ ላይ የነበረችውን ሃገር በመስዋእትህ ህልውናዋ እንዲረጋገጥ ተስፋ ሳትቆርጥ የታገልክ በመሆኑ በማንም ሊንቋሸሽ በማይችል የወርቃማ ታሪክ ባለቤት ነህ፡፡
ባደረግከው መተክያ የሌለው ትግል ክልሎች በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ፣ ታሪካቸውና ባህላቸው እንዲያሳድጉ የሚፈቅድ ስርዓት ተመስርቷል፡፡ እንዲሁም በሃገራዊ ጉዳይ ላይ መላ ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት የሚኖሩበት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት እኩልነትና አንድነት ተረጋግጧል፡፡
ከዛም ባለፈ ድህነትና ኃላቀርነት ለማጥፋት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ መሰረተ ልማትና የሌሎች ልማቶችና ታላላቅ እድገቶች በማስመዝገብ ሃገሪቱ በፈጣን ልማት ላይ ስሟ የሚነሳ፣ የምታስጐመጅና ብዙዎች የሚመኟት ሃገር ሆናለች፡፡
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ የሚያኮራውን የለውጥ ታሪክ አካል በመሆን የደርግን ስርዓት በመገርሰስና ፌደራላዊ ስርዓት በመገንባት ላይ የፃፍከው ታሪክ የሚያሳፍር ሳይሆን በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡
ባሁኑ ወቅት በአገሪቷ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖምያዊና ማህበራዊ ችግሮች እየታዩ ነው ያሉት፡፡በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ህገ-መንግስቱ በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀበት፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥሰቶች እየተበራከቱ የመጡበት፣ የሃገሪቱ ሉአላዊነት አደጋ ላይ የወደቀበትና በአለም ላይ ተፈጥሮ የነበረው አኩሪ ገፅታ እየተበላሸ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የማንኛውም ብሄር ተወላጅ የሆነ ዜጋ በነፃነት ወደ ፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራትና ንብረት አፍርቶ ለመኖር የተቸገረበትና ለጥቃት የተጋለጠበት ግዜ ላይ ደርሰናል፡፡
በዚህ አጋጣሚም በሁሉም የአገራችን አከባቢዎች በማንነታቸው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የተሰማንን ሃዘን ደግመን በመግለፅ፣ ከጎናቸው በመሆን አቅማችን በፈቀደው ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደምንታገልና እንደምንደግፍ ልንገልፅላችሁ እንወዳለን፡፡
ክቡራትና ክብራን
ዘመኑ የተገላቢጦሽ ሆነና ከህውከትና ብጥብጥ ውጭ ህዝብ ማስተዳደር የማይችለውን የለዉጥ አመራር ፣ በሰላምና ባግባቡ ህዝቡን የሚያስተዳድረውን ደግሞ ፀረ ለውጥ ተብሎ ታርጋ ተለጥፎበታል፡፡
ለአገሩ የለፋና ለውጥ ያመጣ የሚረገምበትና የሚወቀጥበት አገሩን የካደና የወጋ ደግሞ የሚሸለምበትና የሚከበርበት የተገላቢጦሽ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
ህዝብ የሚፈልገውን ሰላም የሚያረጋግጥ፣ ልማት የሚያመጣና መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍን ሲሆን በተገላቢጦሽ ዘመን ለውጥ የሚባለው ደግሞ፣ ህገመንግስቱን የሚጥስ፣ ሰላሙን የሚያደፈርስ፣ ልማቱን የሚያስተጓጉልና መልካም አስተዳደርን የሚያጠፋ ነው፡፡
የዘመን ተገላቢጦሹን መስመሩ ለማስያዝ ደግሞ አስፈላጊውን ትግል መደረግ አለበት፡፡ እንደ ሚታወቀው የሩቅም የቅርቡም የትግራይ ህዝብ ታሪክ ለአገሩ ትርፍ መስዋእት የከፈለ እንጂ ልዩ ጥቅም እንኳንስ ሊወስድ የሚገባውንም እንኳን የሚጠይቅ አይደለም፡፡
ስለ ሃገር ሲል ብዙ ችግሮችን ተሸክሞ የሚኖረና በሆደ ሰፊነትና  ትእግስት የሚጓዝ አስተዋይ ህዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ታጋይና ኩሩ የትግራይ ህዝብ ትላንት በትግል ያሸነፋቸውና  ተስፈኛ ሃይሎች የውሸት ታሪኮችና ስም የማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ በትግራይ ህዝብ ላይ የኢኮኖሚና ሌሎች ጫና በመፍጠር ሊያንበረክኩት ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት እነዚህ ስርዓቱን ለማፍረስ የሚተጉ አካላት የሁሉም ችግሮች ምክንያት ከትግራይ ተወላጆችና ድርጅቱ ህወሓት ጋር ማስተሳሰር ቀላል ሆኖ አግኝተውታል፡፡
ጅራፍ ራሱ መትቶ  ራሱ ይጮሃል እንዲሉ ራሳቸው ሃገርን ለማፍረስ ሁከት እየፈጠሩ በትግራይ ተወላጆች ላይ በየግዜው ብዙ ግፍ እየፈፀሙ ጉሮሮአቸው እስኪሰነጠቅ የሁሉም ችግሮች ምክንያት ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ነዉ ይላሉ፡፡
በመሃል አገርም ይሁን ባዋሳኝ የአገሪቱ ክፍሎች ኮሽ ባለና ይላል ብለው ባሰቡት ቁጥር የሚያሳብቡት በማን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቀጣይም ካገር ውጭም ለሚፈጠሩ ሁከቶች በሰበር ዜና መነሻው ያው አመለኛው ነው ማለታቸው አይቀርም፡፡
ይህ የእብደት አካሄድ ለአንድ ወገን ብቻም ሳይሆን ሁሉም ላይ ጉዳት የሚያደርስና የሚያጠፋ አስተሳሰብ በመሆኑ፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር በማጋጨት ስልጣን ለመያዝ እና ለማደላደል የተሰማሩትን አካላት የሰላምና የልማት ፈላጊዉ ህዝብ ስርዓት ሊያስይዛቸው ይገባል፡፡
የትግራይ ህዝብ ለሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብር አለው፡፡ በተለይ የትግል ጓዱና የቅርብ ጐረቤቱ የሆነውን የአማራ ህዝብ ደግሞ ያከብረዋል፡፡ የአማራ ህዝብ ፅንፈኞቹን ስርዓት ለማስያዝ ጥረት እያደረገ መምጣቱን የምናውቅ ሲሆን ለዛም አድናቆትና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
ፅንፈኛ ሃይሎች የአማራን ህዝብ እንደማይወክሉ ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቀጣይነት ያለው ትግል ካልተደረገ፣ ተያይዘን እንድንጠፋ የሚቃሙጡ ሃይሎች ትልቅ አደጋ እንደሚያደርሱ አውቀን ሁላችንም እንድንመክታቸውና በደል የፈፀሙትንም በህግ እንዲጠየቁና ስርዓት እንዲይዙ ለማድረግ መታገል አለብን፡፡
 
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ 
ህግና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ይከበር፣ ብሄር መሰረት ያደረገ ጥቃት ይቁም፣ የሚሉትንና ሌሎች መፈክሮች አንግበህ ድምፅህን ሰሚ እንዲያገኝ ስትታገል ቆይተሃል፣ አሁንም እየታገልክ ነው፣ ለወደፊትም የምትታገል ይሆናል፡፡
እንደ ልማድህ ሁሉንም ፀረ ህዝብና ፀረ ህገ-መንግስት ሴራዎች ተግባራት መስመርህንና አላማህን አጥብቀህ በመያዝ እንደምትመክታቸዉ አያጠራጥርም፡፡
ከዛሬ ነገ የአገሪቷ ሁኔታ ይሻሻላል፡ ይለወጥም ይሆናል በማለት በተሰፋ ላይ ተስፋ ሰንቀህ ቆይተሃል፡፡ ሁሉም ያልፋል በማለትም በደልን ታግሰሃል፡፡ ይሁን እንጂ በቁጥርና በአይነት የህገ-መንግስትን ጥሰት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡
የትግራይ ህዝብ ህገ-መንግስቱን ሳይሸራረፍ እንዲከበር እንደ ህዝብ አንድ ሁኖ  መሰለፍ ብቻም ሳይሆን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲነግስና የአገራችን የለውጥ ሂደት በትክክለኛው መስመር እንዲጓዝ የብሄር ብሄረሰቦችና መላ ህዝቦች መብትና ጥቅም እንዲከበርም ከመላው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ለመታገል ዝግጁነታችንን ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡
የትግራይ ህዝብ የውስጥ አንድነትህን በማጠናከር ዳግም ታሪክ በምትሰራበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁሉንም በትእግስትና በአርቆ አሳቢነት ሁሉም እንደሚያልፍ በማመን እንተጋለን፡፡
የትግራይ ህዝብ አሁንም እንደ ትላንቱ ሰላም የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲ የተረጋገጠባትና በልማት አርኣያ የሆነች ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ርብረብ ከመላ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን የድርሻህን ልትወጣ ይገባል በግዚያዊ ችግሮች ወደ ኃላ ሳትል ወደ ፊት ገስግስ፡፡
ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ የሚደረግ ማናቸዉም ሴራ በፅናት እንድትመክትና ከመላው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመተሳሰር የታወከውን ሰላም እንድታስተካክል፣ ስርዓቱን እንድታድስና የጀመርነውን ጉዞ እንድታስቀጥል በቁርጠኝነት ልትታገል ይገባል፡፡
ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማደፍረስ የሚተጉ ሃይሎችን ስርዓት እንዲይዙ የህዝባችንን ፍላጎት የሆነውን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ትግል ያስፈልጋል፡፡
ህዝባችንን ለሁሉም ክፉም ሆነ ደግ በንቃትና በጥንቃቄ ድህነትህን ጠብቅ፡፡ መወላገድ ቢበዛም እንኳን በፅናት እንደልማድህ ትሻገረዋለህ፡፡
 
የተከበራቹ ወጣቶች 
የተፈጠረውን ችግር ተሸክማችሁ የህገ-መንግስት ጥሰትን ነቅታችሁ በመታገል የራሳችሁ ታሪክ መፃፍ ጀምራቹሃል፡፡ በማህበራዊ ሚድያ ከምታደርጉት ተሳትፎ ባሻገር እያሳያችሁት ያላችሁ ወኔና  አቋማዊ ትግል የሚያኮራ ነው፡፡ በርቱ፣ ቀጥሉበትም፡፡
ሊከፋፍሉን በሚፍጨረጨሩት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝና አንድነታችሁ በማጠናከር ስርዓት ያዙ ልትሏቸው ይገባል፡፡
አስመሳዮች እነዳሉ አውቃችሁ ካሁን በሃላ በቃ ስርዓት ያዙ በሉዋቸው፡፡
ወጣቶች የዚህ መድረክ የታሪክ ባለቤትና አርበኞች መሆናችሁን አመላክታቹሃል፡፡ ዕድልና ድጋፍ ብታገኙ ያላችሁ ዝግጁነትና ብቃት አሳያችሁናል በናንተም ኮርተናል፡፡ ለሁሉም ነገር ዝግጁ ሁኑ፣ በአካባብያቹ በመደራጀት ከእለት ንሮአችሁ ጋር በመቀናጀት ሰላማችን እንዳይደፈርስ ህዝባችሁን አገልግሉ፡፡
እናንተ ባለ አደራ ወጣቶች፣ በስሜትና በችኩልነት ሳይሆን በጥንቃቄ፣ በፅናትና አንድነት እስከታገላችሁ ድረስ ድሉ የናንተ ነው፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች
ይህ 13ኛው የኢትዮጵያ ብሄር- ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ፤ የትግራይ ህዝብ እንደወትሮው ለሰላም፣ ተከባብሮ በእኩልነት የሚኖርባት ሃገርና ክልል ለመፍጠር በሚደረገው ትግል የማይናወጥ ዝግጁነት፣ ፍላጎት እና አቋሙ ለማንፀባረቕና በዋነኝነት ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የህዝብ ልጆች ተከፍሎበት የተመሰረተውን ህገ-መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ እንዲጠብቅና እንዲተገበር ያለው ፍላጐት ለመግለፅ ነው፡፡
ከናንተ ጋር አብረን በመታገላችን ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሃገር በመመሰረት፣ ህዝብ በራሱ የሚተዳደሩበት ስርዓት በመፍጠር አከባቢው የሚያለማበት እና ከልማቱ በደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ሃገራችን በፈጣን እድገት፣ ልማትና ዴሞክራሲ ላይ ትገኛለች፡፡ ተስፋ ያላትና ሌሎችም የሚመኟት ሃገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ የሚያደናቅፍ ችግሮች ገጥመውናል፡፡
በክልላችንና በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ጣልቃ ገብነት በዝቶ አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም አሁንም እንደ ትላንቱ የሚጋጥሙትን ችግሮች ፈትተን የሃገራችንን ህዳሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የትግራይ ህዝብ እንደ ወትሮው ፀንቶ ከጎናችሁ ሆኖ እየታገለ ይገኛል፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ ሃገራችን ማለቅያ ወደ ሌለው ጥፋትና ችግር ከመግባቷ በፊት እየታዩ ያሉትን መሰረታዊ የህገ-መንግስት ጥሰቶች በጋራ እንድናወግዝና እንደንታገላቸዉ የትግራይ ህዝብና መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በሌላ በኩል የህዝብን ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረግና ጀሮ ዳባ ልበስ ማለት ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ካሁን ወድያ ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ሊቀጥል ኣይገባም፤ የህዝብ ድምፅ ይሰማ ወይም እንዲሰማ ይሆናል፡፡
ክቡራንና  ክቡራት
የኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት የሰላም ጉዞ ስርዓት እንዲይዝ በማድረግ ለሁለቱም ህዝቦች የሚጐዱ አካሄዶች ወደ ጐን በመተው የጋራ ጥቅማችንን በዘላቂነት የሚረጋግጥና የተሟላ ስምምነት ላይ እንድንደርስ በበኩላችን የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥልበታለን፡፡
ኤርትራውያን ትግራይ ውስጥ ሳይሸማቀቁ መንቀሳቀስና መስራት እንደሚችሉ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማንል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡
ተልእኮአችን የወደፊት ጉዞአችንና ታሪካችን ብሩህ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ባለፈው በሁለታችን በኩል የባከነውን ግዜ ለማካካስ ቆርጠን እንነሳ፡፡ ተበታትነን ሳይሆን ተዋህደን፣ እየተጠላለፍን ሳይሆን ተጋግዘን ተደብቀን ሳይሆን በጋሃድ፣ በሴራ ሳይሆን በመተሳሰብ ወደፊት እንቀጥል፡፡
#ክቡራትና ኩቡራን
የትግራይ ህዝብ ታሪክ እንደሚያመለክተው፤ የውጭና የውስጥ ችግሮች ባስተማማኝ ሁኔታ እየመከተ ድል በድል እየተጐናፀፈ የመጣ ህዝብ ነው፡፡
የህዝባችንን አንድነት ይዘን የመልካም አስተዳደርና ልማት ችግር እንዲፈታ እንታጋል፡፡ ሁሉም በተሰማራበት ለውጥ ለማምጣት መስራት አለበት፡፡ የቁጠባ ባህል በማጐልበት ከብክነት ተቆጥበን፣ ለተፈናቀሉ ና ሌሎች ችግሮች ያሉባቸው ወገኖቻችንን እንርዳ፡፡
በትግራይ ውስጥ የመልካም አስተዳደር እና ልማት ለውጥ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህ አለማድረግ ግን በትግራይ ህዝብ ላይ ትልቅ በደል ማድረስ በመሆኑ፤ ለትግራይ ህዝብ አክብሮት አለኝ የሚል በሙሉ በስራው ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት፡፡ ቀን ከ ለሊት ይትጋ፡፡ ምክንያት ማብዛትና የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ማለት ይቅር፡፡ ብዙ ከመናገር ብዙ መስራት ብለን ለስራ እንሰማራ፡ ህገ-መንግስታችን በትግላችን ይከበራል፡፡
ክብርና ሞጎስ ለትግሉ ሰማእታት!
አመሰግናለሁ!
Filed in: Amharic