>
5:13 pm - Sunday April 19, 0009

ትናንት ዛሬ አደለም!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ትናንት ዛሬ አደለም!!!
በእውቀቱ ስዩም
እምቢ በል!!!  አሻፍረኝ በል!! በቀረርቶ አትወሰድ! በመፈክር አትሸወድ!!  ለሚያዋጉ እንጂ ለማይዋጉ ጦርአውርዶች  : እንኩዋን ህይወትህን ትኩረትህን ለመሰጠት አትሞክር!!
ይገርማል!! ያገራችን ገበሬ የሚያርስበት በሬና ማረሻ ጥንታዊ ሰው ከአራት ሺህ አመት በፊት ይገለገልበት የነበረውን ነው:: ይሁን እንጂ ቢቀናው ክላሺንኮቭ ይታጠቃል::  ደሞ ገበሬውን ዘመናዊ ጠመንጃ እንጂ ዘመናዊ ማረሻ ለማስታጠቅ የሚያልም   አክቲቪስት አይተን አናውቅም::
 ዘመናይ የብሄር አክትቪስት ጦርነት በናፈቀ ቁጥር ያባቶቹን ጀብድ  ይዘክራል:: ባባቶቹና በሱ መካከል በሰፊው  የሚያዛጋ የጊዜ ገደል እንደተዘረጋ  አይገባውም:: የድሮ ሰዎች ከማረስ ይልቅ መዋጋት ቢወዱ አይገርምም::  ያኔ ጦርነት ወጭው ትንሽ : ትርፉ ብዙ ነበር:: ጥቂት የተደራጀ ጭፍራ ጥቂት ፈረስና ጦር ይዞ  በሺ የሚቆጠር የቀንድ ከብት መማርክ ይቻል ነበር:: ዛሬ አንድ መንደር አርሶ የሚያበላ  ትራክተር ባስራ አራት ሺህ ዶላር መግዛት ትችላለህ:: አንድ መንደር አፈር የሚያስበላ ታንክ ለመሸመት ከፈልግህ ግን ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅብሃል:: እና  በዚህ ዘመን  ተዋግቼ አተርፋለሁ ብሎ ጉራውን የሚነፋ አዲስ የተመረተ ዴዴብ መሆን አለበት!!!
ድሮ በሰላምም ሆነ በጦርነት ባጭሩ መቀጨት  ያባት የናትህ እዳ ነበር:: በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ከሞት ጋር ያለህ ርቀት ተቀራራቢ ነው:: ይህን የሚያውቁት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በማይጨው ዋዜማ የክተት አዋጃቸው  “ቤትህ ቁጭ ብለህ በሳልና በጉንፋን ከመሞት ጠላትን መክተህ ብትሞት ክብር ነው” ብለው ዜጋውን ጀንጅነውታል:: ልክ ነው!  በህዳር በሸታ ከመሞት በጦርነት መሞት ስም እና ምርኮ ሊያስገኝ ይችላል::
ዛሬ ሰላም  ወጭ ቆጣቢ ነው:: ሰላም ያለው  ብዙ ሀብት  ብዙ እድል ብዙ ተስፋና ብዙ እድሜ  ይኖረዋል:: ታድያ  ለሰላም ሲባል   ወደረኞቻችንን ብንለማመጣቸው ብናቆላምጣቸው  ብንወያያቸው እንዴት ነውር ይሆናል?  ዛሬ መደራደር መወያየት የሚያሳፍርበት  : ውረድ እንውረድ የሚያስኮራበት ዘመን አይደለም::
ዛሬም እንደ ጥንቱ   በርስት ወይም በማንንት ሰበብ የሚደረግ ጦርነት የሚጎዳው ዜጎች እንጂ ጌቶች አይደለም:: ከእምባቦ ከሰገሌ እና ከባድመ ክሽፈት እንዳየነው አገሬው በጦርነት ያልፋል:  አገር መሪው ግን ይተርፋል:: በምባቦ ጦርነት ንጉስ ምኒልክና ንጉስ ተክለሃይማኖት ገጥመው በብዙሺህ የሚቆጠር ባላገር ያአሞራ  ቀለብ ሆነ:: ሁለቱ ሃያላን ግን ታርቀው ተፋቅረው ረጅም እድሜ ኖሩ:: ሰገሌ ላይ የንጉስ ሚካየል ባላገርና  የተፈሪ መኮንን ባላገር ተፈሳፈሰ::  ደሙን ለሁለቱ መሳፍንት የክብር ሲል  አፈሰሰ:: ንጉስ ሚካኤልም ሆነ ተፈሪን ግን ከጦርነቱ ማጠናቀቂያ  ባንድ ድንኩዋን ውስጥ ተቀምጠው ” አባቴ እንኩዋን አተረፈዎ!  ልጄ እንኩዋን አተረፈህ” እየተባባሉ ተቃቀፉ:: በባድመ ጦርነት ያ ሁሉ ወጣት  አላማም ሆነ ኢላማም በሌለው ጦርነት ሜዳ  ላይ ቀረ:: የጦርነቱ ጠንሳሾች ለሙታን ተገቢውን መታሰቢያ ሳያደርጉ ላደረጉት ይቅርታ ሳይጠይቁ በህይወት ይርመሰመሳሉ :: ነገም ከዚህ የተለየ አይሆንም!!
እና እምቢ በል!!!  አሻፍረኝ በል!! በቀረርቶ አትወሰድ! በመፈክር አትሸወድ!!  ለሚያዋጉ እንጂ ለማይዋጉ ጦርአውርዶች  : እንኩዋን ህይወትህን ትኩረትህን ለመሰጠት አትሞክር!!
Filed in: Amharic