>

"እየናፈቁ ሞት" (ታደለ ጥበቡ)

“እየናፈቁ ሞት”
ታደለ ጥበቡ
ይሄን በሬሳ ሳጥን ውስጥ የተነሳ የልዑል አለማየሁ ፎቶ ሳዬው ሁሌም አይኖቸ ዕንባ ያቀራሉ፤፤ወስጤ ይንቦጫቦጭብኛል።መቅደላን ያህል ግንብ በጠላት ጦር ሲናድ የ6 አመት ልጅ የነበረው  ልዑል ዓለማየሁ ከእናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ እና የ3 አመት ህጻን ከነበረው ወርቅነህ እሸቱ ጥግ ይዘው ተወሽቀው ነበር ነገርግን  ወዲያውኑ  ተያዙ።
 የእንግሊዝ ጦር አዝማች ናፒር  ለዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሻለቃ ስፒዲን እና ኢትዮጵያዊውን ደብተራ ዘነብን ሞግዚት ከአደረጉ በኋላ መቅደላ ላይ የተከማቸውን አንጡራ ሀብት  በዝሆኖችና በቅሎዎች ጭነው አለማየሁ ቴዎድሮስን እና እናቱን  እትጌ ጥሩወርቅን ይዘው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
 እቴጌ ጥሩወርቅ የአጼ ቴዎድሮስ ሞት፣በጦርነቱ ያለቁት ኢትዮጵያዊን ሀዘን፣የተዘረፈው ንብረትና ተማርከው በግዞት መወሰዳቸው ውስጥ ውስጣቸውን ይበሽቃቸው ስለነበር   አርማጭሆ በረሃ ሲደርሱ  በጠና ታመሙ።የኢትዮጵያን ምድር ለቀው ሳይወጡ ግንቦት 15 ቀን 1860 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈች። በሕመም እያቃሰቱ ሳሉ ግን ስለ ልጃቸው ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጀነራል ናፒርን አስጠርተው የሚከተለውን ነገሩት።
“እኔ እንግዲህ መሞቴ ነው፤ የዓለማየሁን ነገር አደራ፤ አባቱ ከመሞታቸው በፊት እንግሊዝ ሀገር ሔዶ እንዲማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ደጃዝማች ዓለማየሁን ውሰዱና አስተምራችሁ ወደ ሐገሩ ላኩልን። ውለታችሁን ግን አምላክ በሰማይ ቤት ይክፈላችሁ” ብለው በተናዘዙ በሁለተኛው ቀን አረፉ።አስክሬናቸውም ወደ ሸለቆት ገዳም ሔዶ ተቀበረ።
 በዚህ ወቅት የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት የልዑል ዓለማየሁ አያት አንድ ደብደቤ ለእንግሊዟ ንግስት ላኩ። ደብዳቤው የልዑል ዓለማየሁን ጉዳይ መሠረት ያደረገና አያቱ ምን ያህል እንደተጨነቁለት የሚያሳይ ነው። ተክለጻዲቅ መኩሪያ ይህን ደብዳቤ አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ በሚከተለው መልኩ አቅርበውታል።
“በስመ አብ. . . ከወይዘሮ ላቂያዬ የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት፣ የደጃዝማች ዓለማየሁ አያት የተላከ። ይድረስ ለእንግሊዝ ንግሥት። አንባቢው እጅ ይንሳልኝ፤ መድኃኒዓለም ጤና ይስጥልኝ፤ መንግሥትዎን ያስፋ፤ ጠላትዎን ያጥፋ። ሶስት ደጃዝማቾች፣ አራተኛ እቴጌ ጥሩወርቅ ሞተውብኝ የቀረኝ ደጃዝማች ዓለማየሁ ነው። አደራዎን ይጠብቁልኝ። እግዝአብሔር አባቱንና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል። እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ። እርስዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፤ አላሰደግሁትምና። እርስዎ ያሳደጉት ስለ እግዚአብሔር ብለው”በማለት የልዑል ዓለማየሁ አያት ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ ደብዳቤ ላኩ።
< ምስሉ ላይ የሚታዬው ከሬሳ ሳጥኑ ላይ የተነሳ ፎቶ ነው።
የእንግሊዝ ሠራዊት ከእቴጌ ጥሩወርቅ ቀብር በኋላ ጉዞውን ቀጠለ።በፓርት ሱዳን በኩል ከዚያም ሰኔ 3 ቀን 1860 ዓ.ም  ፌሮዝ እየተባች በምትጠራ የእንግሊዝ የጦር መርከብ ወደ እንግሊዝ አገር ገሰገሱ።ከአንድ ወር የባህር ጉዞ በኋላ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፣ ሻለቃ እስፒዲ እና ደብተራ ዘነብ ወደ ለንደን ሲደርሱ፣ አብሯቸው የነበረው የሶስት ዓመቱ ወርቅነህ ደግሞ ከሞግዚቱ ከኮሎኔል ቻርልስ ቻምበርሊን ጋር ሆነው ወደ ሕንድ ሐገር ጉዞ ጀመሩ። አለማየሁ በ3 አመት የሚበልጠውን ጓደኛውን ወርቅነህን እና እናቱን በሞት በማጣቱ ሀዘን ተሰማው።ብቸኝነት ባይተዋርነት….
ልዑል ዓለማየሁ እናቱን ቀብሮ ከጓደኛው ወርቅነህ ተለይቶ ለንደን ከገባ በኋላ ሻለቃ እስፒዲ ወደ ዊንድሶር ቤተ-መንግሥት ንግስቲቷ ዘንድ ይዞት ሔደ። ንግሥቲቷም ዓለማየሁን ትክ ብለው አዩት። አቀፉት። ከዚያም የተሰማቸውን ስሜት በሚከተለው መልኩ እንደገለፁት ስለ አለማየሁ ቴዎድሮስ ሰፋ ያለ ጥናት የሰራው  ፈቃድ ሐብቴ ፅፎታል።
“ጊዜው በጋ ነበር። ውድ ዓለማየሁ! የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፣ ያጌጡ የአብሲኒያ ልብሶችን ለብሶ ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ብቅ አለ።ከፍ ያለ ደስታ ተሰማኝ። ቀረብ ብዬ አቀፍኩት።ሁልጊዜ ስለ አባቱ የምንሰማው ቁጣ ግን ከፊቱ አይነበብም።በጣም አይናፋር ሆኖ አገኘሁት። በእንግሊዝኛም ትንሽ አነጋገርኩት”በማለት ንግሥት ቪክቶሪያ ፅፈዋል።
 ሻለቃ ስፒዲ የአለማየሁ ሞግዚት በመሆኑ ባለው የወር ደሞዝ ላይ 400 ፓውንድ በየዓመቱ ተጨመረለት። ካፒቴን ስፒዲ ከእንግሊዝ ወደ ሕንድ ሀገር በስራ ተቀይሮ ሲቀየር አለማየሁም አብሮ ተጓዘ።በዚህን ጊዜ የእንግሊዝ ሊብራል መንግሥት የገንዘብ ሚኒስትር ሮበርት ላው  ዓለማየሁ ከሕንድ ሐገር እንዲመለስ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ለግላድስተን ታህሳስ 18 ቀን 1870 ዓ.ም ደብዳቤ ጻፈ። የፃፉትን ደብዳቤ ፈቃድ ሐብቴ አግኝቶት ይፋ አድርጎታል። ደብዳቤው ወደ አማርኛ ሲመለስ እንዲህ ይላል፡-
“ጠቅላይ ሚኒስትር ግላድስተን
10 ዳውኒንግ መንገድ ለንደን
በመጀመሪያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤንነት እየተመኘሁ ስለ ዓለማየሁ ጉዳይ ይህን መፃፍ ተገድጃለሁ።በአሁኑ ሰዓት ግልጽ ሊሆንልዎት የሚገባው ነገር ቢኖር ዓለማየሁን በሞግዚትነት የተረከቡት ሻለቃ እስፒድና ሚስቱ ሳይሆኑ መላው የእንግሊዝ ሕዝብ ነው። ስለ ዓለማየሁ የወደፊት ሕይወት እነ ሻለቃ እስፒዲ ከሚሰጡን ሃሳብ ወጣ ብለን መንግሥታችን ዘላቂ መፍትሔ መሻት ያለበት ይመስለኛል።
በመጀመሪያ ዓለማየሁን ከሕንድ አገር ማስመጣት ይኖብናል፤ ለወደፊቱ በአብሲኒያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና ይጫወታልና። የኛ መንግሥት ጥሩ ጓደኛና ጥቅም አስጠባቂ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ዙፋን ወራሽ ስለሆነ እንደ ሕንድ በመሰለ በሽታ፣ ድንቁርናና ኋላ ቀርነት የፊጥኝ ባሰረው ኅብረተሰብ መካከል ማቆየቱ ተገቢ አይመስለኝም። አሁንም ቢሆን እስካሁን ድረስ እዛው እንዲቆይ “መደረጉ በጣም አዝናለሁ። በአስቸኳይ ወደ እንግሊዝ ሐገር እንዲመጣ ካልተደረገ ግን መጀመሪያውኑ ዓለማየሁን ለማሳደግና ለማስተማር ከአገሩ ማስወጣቱ ቁም ነገር አልነበረውም ማለት ነው።
ሻለቃ እስፒዲና ሚስቲቱ አንዳንዴ የሚናገሩት ገና የሚያደርጉትን አያውቁም። እኔ እርስዎን ብሆን ባልና ሚስቱ የሚሉትን አልሰማም። የዓለማየሁ ከነሱ ጋር መቆየት ከራሳቸው የኢኮኖሚ ጥቅም ጋር የተገናኘ በመሆኑ መቼውኑ ቢሆን እውነትንና ለዓለማየሁ የሚበጀውን ነገር መናገር አይፈልጉም።
ለዓለማየሁ እንግሊዝ አገር እንደተመለሰ የሚገባበት ት/ቤት አዘጋጅቼለታለሁ። ብራይተን የሚገኘው የቻልተንም ኮሌጅ ርዕሰ መምህር የሆነው ጂክስ ብሌስ በራሱ የግል ቤት አስቀምጦ እንዲያስተምረው ተስማምተናል። ጂክስ ብሌስ ዘጠኝ ሴቶች ልጆች ስላሉት ዓለማየሁ መቼውንም ቢሆን ብቸኝነት አይሰማውም ብዬ አምናለሁ።ዓለማየሁን ይህንን የምንኮራበትን የበለፀገ ባህላችንን የምናስተምርበት ከዚህ የበለጠ ዕድል የሚያጋጥመን አይመስለኝም። ከዚህ በተረፈ ግን የርስዎን ትዕዛዝ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ።
ታዛዥዎ
ሮበርት ላው፣ ቻንስለር
ግልባጭ
– ለንግሥት ቪክቶሪያ
ዊንድሶር ቤተመንግት”
ሕንድ ሐገር የሚገኘው ካፒቴን እስፒዲ ደግሞ የተፈጠረውን ጉዳይ አያውቅም። እንደውም ለንግሥቲቱ ደብዳቤ ፃፈ። ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ ሀገር መጥቶ ትልቅ ት/ቤት መማር አለበት፣ ስለዚህ ለእኔም ቅያሬ ይሰጠኝ ብሎ ፃፈ።
የልዑል ዓለማየሁ ጉዳይ የእንግሊዝን ባለስልጣናት ያጨቃጭቅ ገባ። ይባስ ተብሎ ሻለቃ ስፒዲ ወደ ማሌዥያ ተቀየረ። በዚህ ወቅት እነ ሮበርት ላው ልዑል ዓለማየሁን ከካፒቴን ስፒዲ እጅ ለመንጠቅ ምቹ ጊዜ ተፈጠረላቸው። ሮበርት ላው ለባለስልጣናቱ የሚከተለውን ደብዳቤ መፃፉም ይነገራል፡-
“የዓለማየሁን የወደፊት ሕይወት በሚመለከት ቋሚ መመሪያ ሊኖር ይገባል። ይህ ምስኪን ልጅ አጋጣሚ ሆኖ መጀመሪያ በአንድ ወታደር እጅ በመውደቁ እሱ ዛሬ አፍሪካ፣ ነገ ሕንድ፣ ከነገ ወዲያ ቻይና ይሄድ ተብሎ በተወሰነ ቁጥር አብሮ መንገላታት የለበትም።
በአሁኑ ሰዓት ሻለቃ እስፒዲ ወደ ማሌቪያ ፒናንግ እንዲሔድ በመታዘዙ ቀደም ሲል ዓለማየሁን እንዲያስተምር ያደረግነውን ስምምነት እዚህ ላይ ለማስቆም ወስኛለሁ።
በተረፈ ግን ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ወደ እንግሊዝ አገር አምጥቶ ለርዕሰ መምህሩ ለጃክሰን ብሌክ እንዲያስረክብ አስፈላጊውን ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ”በማለት ፃፈ።
ከብዙ ጭቅጭቅና የደብዳቤ ልውውጦች በኋላ ልዑል ዓለማየሁ ወደ ጃክስ ብሌስ ዘንድ ተዘዋወረ።ለአራት ዓመታትም ማለትም እስከ እ.ኤ.አ. 1875 ዓ.ም ከጃክስ ብሌስ ጋር በት/ት ቆየ። ልዑል ዓለማየሁ በተማሪዎች፣ በመምህራንና በባለስልጣናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ልዑል ነበር። የጦር አካዳሚ ትምህርቱንም በሚገባ ተከታትሎ ነበር።
ዓለማየሁ ፈረንሳይንና ሌሎች ከተሞችንም ከጎበኘ በኋላ መታመሙ ተሰማ። ንግሥት ቪክቶሪያ ይህን የዓለማየሁን ጤና ማጣት ሲሰሙ ደንግጠው ወዲያው ከሚማርበት ከሳንድረስት ጦር አካዳሚ ወጥቶ ከልዩ ፀሐፊያቸው ቤት ሆኖ ሕክምናውን እዲከታተል የዓለማየሁ ጉዳይ ለሚመለከታቸው ባለስልጣኖች ቴሌግራም ማድረጋቸው ተፅፏል። ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ዓለማየሁን ከነበረበት ኮሌጅ አውጥተው ወደ ንግስቲቱ ልዩ ፀሐፊ ቤት ወሰዱት። ሕመሙ እየጠናበት ሄደ። ልዕልት ቪክቶሪያ ይህን ሕመሙን አስመልክተው የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ፡-
“ውደ ዓለማየሁ በጣም ታሟል። በመጨረሻ የተደረገው ምርመራ ትንሽ የተስፋ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል።ነገር ግን ሕይወቱ አደገኛ ጊዜ ላይ ነው ያለችው።በሳንባ በሽታ በጣም ይሰቃያል።ዓለማየሁ መርዝ አቅምሰውኛል ብሎ ስለሚጠራጠር ምግብና መድሃኒት የመውሰድ ፍላጊቱ ቀንሷል።በዚሁ ምክንያት በየዕለቱ ሰውነቱ እየደከመ በመሔድ ላይ ነው። ከቅርብ ቀናት ጀምሮ ግን ዶክተሩ ያዘዘለትን መድሃኒት መውሰድ ጀምሯል። መርዝ አብልተውኛል የሚለውን ሃሳቡን ትቷል።በተረፈ ግን ለልጅ ዓለማየሁ እንፀልይለት”
መረጃዎችን ከእንግሊዝ ቤተ-መንግሥት የሰበሰበው ፈቃድ ሐብቴ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ በሚከተለው መልኩ ይገልጸዋል።
“የዓለማየሁ ዶክተር የንግሥቲቱን የግል ሐኪምና ሌሎች የታወቁ የህክምና ሰዎችን አነጋገረ። ለንግሥት ቪክቶሪያ የዓለማየሁን ሕይወት ማዳን የማይችል መሆኑን ኅዳር 11 ቀን 1879 ዓ.ም ተነገራቸው። በጣም በጣም በማዘን አንድ የመጨረሻ ደብዳቤ ፃፉለት። ዓለማየሁ አልጋ ላይ ተኝቶ እያቃሰተ የንግሥት ቪክቶሪያን ደብዳቤ ለማንበብ ጥረት አደረገ። የነበረውን ሁኔታ የንግሥቱቱ ልዩ ፀሐፊ ሚስት እንዲህ ብለው ይገልጹለታል. . .
“ዓለማየሁ ደብዳቤው ከማን እንደተፃፈ ለማወቅ የደብዳቤውን አድራሻ መፈለግ ጀመረ። የንግሥት ቪክቶሪያን ስም እንዳየ ፈገግ አለ። ፖስታውን ቀደደና ወረቀቱን ወጣ አድርጎ ትንሽ መስመሮች እንዳነበበ በጣም ስለደከመው ደብዳቤውን ሊያነብ በሚችልበት ቦታ ላይ እንዳስቀምጥለት ጠየቀኝ።አንገቱን ወረቀቱ ወደተቀመጠበት ዘወር አድርጎ የጀመረውን ለመጨረስ ታገለ። አልቻለም። በመጨረሻ እጄን ይዞ ማቃሰት ጀመረ”
በመጨረሻ የሻለቃ እስፒዲንና የጃክስ ብሌስን ሚስት እጃቸውን እንደያዘ በ19 ዓመቱ ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም ከጥዋቱ 3 ሰዓት ላይ ዐረፈ። በንግሥት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ ዓለማየሁ ዊንድሶር በሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተ- ክርስትያን እንዲቀበር ተደረገ። በሞተ በሶስተኛው ቀን ንጉሣዊ ቤተሰቦችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖች በተገኙበት የቀብሩ ስነ-ሥርዓት ተፈፀመ።
ስደተኛው አለማየሁ እንደከፋው፣ሀገሩ ኢትዮጵያ እንደናፈቀችው እንግሊዝ ሀገር ተቀብሮ ቀረ።
የታላቁ ንጉስ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ይህችን አለም በሞት ሲለይ ንግስት ቪክቶሪያ የሚከተለውን ፃፉ።
“የዓለማየሁን መሞት ዛሬ ጠዋት ሰማሁ። ጥልቅ ሀዘን ተሰማኝ። ባይተዋር እንደነበር ባይተዋር ሆኖ ሞተ።ከመጀመሪያ ጀምሮ ደስተኛ ልጅ አልነበረም። በወጣትነቱ ካሳደጉት ዘመዶቹና ወገኖቹ ርቆ መኖር ለወጣት ዓለማየሁ ከባድ ፈተና ነበር። ጥቁርና (አፍሪካዊ) ሆኖ መኖር በእኛ ኅብረተሰብ አስቸጋሪ መሆኑንም ተረድቶታል።አንድ ቀን ሊያየኝ የመጣ ቀን “ለምን አንዳንድ ሰዎች ትኩር ብለው ያዩኛል?” ብሎ የጠየቀኝ ትዝ ይለኛል። መልስ አልነበረኝም። ወጣቱ ዓለማየሁ ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት እንደነበር ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት ሆኖ ሞተ”።
 
     
“የሰገደላት ውበቱ ፤ ያቺን የቃል መስታይት(2)
ሞቶ ቀደማት ቴዎድሮስ ፤ ቆሞ ስቃዩዋን ላለማየት(2)
ደርሶ ባያስጥለው ፤ ገብርዬ ከስለት
ጀግናው ተፈተነ ፤ በመቅደላ አቀበት
ተዋከበና ፤ ተዋከበና
ወዲህ ዞር ፤ ቢል ሰው የለምና
ገብርዬ ሲወድቅ ፤ ቀኙ ዛለና
አረሩን ስቦ ፤ ጠጣው ያ ጀግና
ተዋከበና ፤ ተዋከበና
ወዲህ ዞር ፤ ቢል ሰው የለምና
የነደደ እሳት ፤ ክንዱን ተ’ርሶ
ጨክኖ ካሣ ፤ ጋተና ኮሶ
ሞተ ‘ላንድ አገር ፤ አንድያ ራሱ
 
ንቃ በመንፈስ ላንድነት ካሣ ተነሳ
አንተ የሞትክላት አገር ክብሯ ሳይረሳ
ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር
ያንዲት ኢትዮጵያ ፤ ዋልታና ማገር
ነፍሱን የሰጣት ፤ ለካ ዓለም ንቆ
አገር ሊያቆም ነው ቴዎድሮስ ወድቆ
አምጡ ቆርጣችሁ ፤ ከሹሩባው ላይ
እንዳንለያይ ፤ ኪዳን እንሰር
ነፍሱን የሰጣት ፤ ለካ ዓለም ንቆ
አገር ሊያቆም ነው ፤ ቴዎድሮስ ወድቆ
አረጀች እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ
ሙሽራ ነሽ ጎንደር ይሰፋል ልብስሽ
ሳይገላገለው ህልሙን በሆድ ይዞ
ሳይገላገለው ሽሉን በሆድ ይዞ
የሚረዳው አጥቶ ብቻውን ተክዞ
ተክዞ ተክዞ
ስንቱን በሆድ ይዞ
የወገቡን እሳት ካፎቱ ላይ መዝዞ
ጠጥቶላት ሞተ ክንዱን ተንተርሶ
አያሳዝንም ወይ
ካሣ ካሣ የቋራው አንበሣ
ዳኘን ዳኘን አንድ ህልም አሳየን
ዝግባ ሚያሳክለን አንድ ፍቅር አጥተን
ዝግባ ሚያሳክለን አንድነትን አጥተን
ከፊት የነበርነው ከሰው ኋላ ቀርተን
አናሳዝንም ወይ
ጎንደርና ጎጃም ፤ ወሎና ትግራይ
ኦሮሞና ተጉለት ሆነን አንድ ላይ
ጉራጌና ሃረር ዶርዜ ወላይታ
ቤኒሻንጉል ሶማሌ አፋር አሳይታ
ግመሌን ላጠጣት እንደ አፋር ተጉዤ
ግመሌን ላጠጣት ቀይ ባህር ተጉዤ
አንድ ገመድ አጣሁ ልመልሳት ሄጄ
‘ያንዲት እናት ልጆች መሆናችን አውቀን
ጎሳና ኃይማኖት ሳይነጣጥለን
ምን ይሳነን ነበር ብንተባበር
አናሳዝንም ወይ
ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር
ያንዲት ኢትዮጵያ ፤ ዋልታና ማገር
ነፍሱን የሰጣት ፤ ለካ ዓለም ንቆ
አገር ሊያቆም ነው ፤ ቴዎድሮስ ወድቆ
Filed in: Amharic