>
5:13 pm - Thursday April 20, 0102

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት!!! (ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ) 

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት!!!
ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ 
1981 ነሐሤ 27  ከቀኑ 14.30 ሠአት ላይ አላማጣ አየር ማረፊያ የመከለከያ ከፍተኛ ሥታፎችን ይዛ አረፈች፡፡መቀሌን ለቆ በነጓድ ለገሠ አሥፋው ትእዛዝ ለቆ የመጣው ሦሥተኛው አብዮታዊው ሠራዊት እኛን የመጨረሻው የውጊያ ጠርዝ ላይ አሥቀምጦ ከትግራይ ክልል ወደመሐል ደሤ ወልድያ የተሠደደ ሕዝብ ሁሉ አሥከትሎ እንደ ሡናሚ አጥለቅልቆን የእዝ ጣቢያውን ወልድያና ደሤ ከትሟል፡፡ወያኔ ከተፈናቃዩ ሕዝብ ጋር ነጭ ሸማ አልብሣ ከጀርባችን ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅማ የውጊያ ሥልቷን መሐል ሐገር ሆና አመራር አየሠጠች ነው፡፡ራሺያ ሠራሿ ኢሊኮፕተር ይህ በረራዋ ተሥፋ ይዞ መምጣቱንና የግራ ካሦ የ605ኛ ኮር ውጊያ ወደ ተለቀቁ የውጊያ ቀጠናዎች በድል እንቀጥላለን ብለን ተሥፋችን ሙሉ ነበር፡፡ማይጨው በ1980 መጨረሻ ከወያኔ አሥለቅቀን የፈረደበት 1ኛ ክፍለጦር ሦአሠ /ሦሥተኛው አብዮታዊው ጦር እነኛን በቀላሉ የማይሠበሩ የአምባላጌን ከፍተኛ መሬቶች ጭምር አሥረክቦ እነ ጀነራል ደሣለኝ ሽርካን እነ ሻምበል ሡሌይማን ደደፎን/አምባሣደር/ በህይወታቸው ተፈርዶ ወደ መሀል ከተመ፡፡
አሣዛኙ ድራማ ክፍለጦሩ ሐይሉን ሁሉ በዚህ እንዲደመሠሥ በተፈረደበት ክፍለጦር ላይ ወያኔ አደራጅቶ ከሁዋላም ከጎንም ያየር ድጋፍ ጥያቄ እንኳን እንዳያገኝ ተደርጎ ምሥኪኖቹ ቀድሞ ትጥቁን በፈታው ሦሥተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አመራር አጥተው ግማሹ ሀይል በከባድ መሣሪያና በጥይት አረር ነደዱ፡፡ከፊሉ እንደምርኮኛ ተቆጥሮ ተማረከ፡፡አላማጣ የመጨረሻ የውጊያ ጠርዝ ሆኖ ኮረም ላይ የእዝ ጣቢያቸውን ያደረጉት እነ ሐየሎም ቁልቁል ማታና ንጋት ላይ ለረጅም ሠአታት በሚተኩሡብን ከባድ መሣሪያና የዙ/23/ጥይት ግራ ካሦ ወገብ ላይ ወደ ላይ ገፍቶ ለመውጣት የማይመቸው ቁጥቋጣማ መሬት ባለበት ሆኖ ህይወቱ እሥካለ ድረሥ የተኩሥ መልሥ እየሠጠ በርሀብና በውሀ ጥም እየተቆላ ቀድሞ ትጥቁን ለፈታው መከላከያ በታማኝነት ይዋደቃል፡፡
ሒሊኮፕተሯ ጀነራል አዲሥ ተድላን ጀነራል መሥፍን ገብረቃልን/ኢታማዦር ሹሙንና የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጦር ሀይሎች ዋና ፖለቲካ አሥተዳደር/እንዲሁም የዘመቻ ሀላፊዎችን ይዛ ነበር የመጣቸው፡፡የነበረንን የተዋጊ ሀይል መመናመንን፡የጥይትና የቀለብ የህክምና ቁሣቁሥ እጥረትን እነ ጀነራል ጥላሁን አርጋው ከመግለፃቸውም በላይ ሁኔታው ባጭር ጊዜ ከተሟላ ወደ ተለቀቁት የትግራይ መሬቶች መገሥገሥ እንደሚቻል ኮለኔል ተመሥገን ጫላ ጭምር አሥረዱ፡፡
የመከላከያ ሀላፊዎች ከፍተኛ ሀይል ወልድያ ላይ አከማችተው ወደኛ ለመነቃነቅ ተዘጋጅቶ እንዳለ፡ቀለብና ትጥቅ በሂሊኮፕተር በተከታታይ እንደሚጓጓዝልን ቢያንሥ ለሁለት ቀን ከግራ ካሦ ወያኔ እንዳይወርድ ገድበን እንድንቆይ መመሪያ ሠጥተውን በመጡበት አኳሁዋን ተመለሡ፡፡ለአንድ ሣምንት የመጣ ቀለብም ትጥቅም የሠው ሀይልም የለም፡፡የወያኔ ጉልበት እየበረታ፡ቁሥለኞቻችን በአላማጣ የመዝናኛ ክበብ አዳራሽ ውሥጥ በቂ ሕክምና አጥተው ጨርሡን እያሉ በሚጮሁበት ጳጉሜ 3/1981 ለሊት መያዝ የማትችሉትን ንብረትና ተሽከርካሪ አቃጥላችሁ መንገዶች ሁሉ በፈንጂ የታጠሩ በመሆኑና አላማጣና ቆቦ መሀከልም ጬቤ በር ላይ በወያኔ ሥለተያዘ ሠብራችሁ ቆቦ ግቡ የሚል ትእዛዝ ከመከላከያና ከሦአሠ ተሠጠን፡፡
ከሦሥት መቶ በላይ ቁሥለኞች እንደ አንድ ሐገር ሕዝብ ተዋጊ ሣይሆን እንደተራ ሽፍታ ቁሥለኛ መታከምና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ሢገባ ጥላችሁዋቸው ውጡ የሚለው የአለቆቻችን ትእዛዝ እልህን የሚፈታተን ነበር ፡፡እነ ጀነራል ጥላሁንም አንዴት ወደቆቦ ሜዳማ ቦታ ላይ ሄደን ለሌላ አላሥፈላጊ ውድቀት ያመቻቹናል፡፡ለምን ወልድያ ያለው ሀይል ወደ እኛ አይመጣም ይቺ ሐገር ምን እየሆነች ነው ብለው በመቆጨት የማይቀረውን የኮመጠጠ ትእዛዝ ተቀበሉ፡፡
ወገን የጨከነባቸው ቁሥለኞች
ጳጉሜ 3/1981 ለሊቱን ንጋት ላይ 0400 ሠአት ላይ በኮሩ አዛዥ ጀነራል ጥላሁን አረጋው ወደ ቆቦ ማፈግፈግ እንዲደረግ የማይቀረውን የበላይ አካል ትእዛዝ ሠጡ፡፡ግራ ካሦ ላይ መቃጠል ያለባቸውን ለሚቀጥለው ጉዞ የማይመቹ፡ጠላት እጅ ቢወድቁ ደግሞ ሊጠቅሙ ይችላሉ የተባሉ ንብረቶች ይቃጠሉ ጀመር፡፡ጦሩም አንድ እግር በመሬት ወደሁዋላ እየተኮሠ ታሪካዊዉን ግራካሦ ለእነ ሐየሎም አሥረከበ፡፡
የአላማጣ ካምፕ ንብረት ያለባቸው መጋዘኖችና ዲፖዎች በመሐንዲሥ አዛዡ ሻም/ገበየሁ በቀለ ነደዱ፡፡ቁሥለኞች ካሉበት በሥተምእራብ አቅጣጫ አጥር በከለለው ጉርብትና ውሥጥ ያሉ በውጭ ተራድኦ ድርጅት የሚረዱ መነኮሣትንና ቁሥለኞችን የወደፊት እጣቸውንና እድላቸውን ለወያኔ መተው የግድ ሆነና፡ሥናዋጋቸው የነበሩ በጀግንነት ለረጅም ቀናቶች እንደሻማ ቀልጠው ዛሬ ያፈግፍጉ ትእዛዙን ለመተግበር ያበቁንን ንፁሀን ጀግኖችበእምባዎቻችን ጭጋግ አየሣልናቸው በመትነዳዋ አለማጣ መንገዱን ከመሀል ትተን ማፈግፈጉን ተያያዝነው፡፡ይሄ ከመታሠቡ በፊት እንኳን አንድ ቀን ቀደም ብሎ በመሐንዲሥ እየተፈተሸ መነገዱን እየተከፈተ ከፊል ሀይል በተሽከርካሪ ቁሥለኞችን አሥጠግተን ጩቤ በርን ሠብረን ብናልፍ ንብረትም የሠው ህይወትን ባዳንን ነበር፡፡
20 ኪ/ሜ ያህል የምትርቀዋ ቆቦ እሥከ 10.30 ባለው ጊዜ ተጠቃልለን ገባን፡፡ጩቤ በር ላይ ቆርጧችሁዋል የተባለው የወያኔ ሀይል ጥጉን ይዞ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል የደሥታ ተኩሥ ላጭር ጊዜ ተኩሦብን ቆቦ ገባን ቀደም ሢል ቆቦ ከተማ ምእራብ አቅጣጫ የተዘጋጀው ውሥጥ ቀዳሚ መምሪያችንን አቋቁመን አፈግፍገው የመጡ ሀይሎቻችንን ቦታ ቦታ አሥያዝን ፡፡
የአላማጣ ሕዝብ በተለይ ከደርግ ሥርአት ጋ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተገመቱና ሐገራቸውን የሚወዱት ሁሉ ልጆቻቸውን ቀላል ንብረታቸውን እያንጠለጠሉ አብረው ወደሚቀጥሉት የመንግሥት ይዞታ ሥደት ጀመሩ፡፡ወያኔ አላማጣን ለቆ ወደ ቆቦ ሜዳ ላይ የሠፈረውንና ለእርድ ከሀዲዎች ያዘጋጁትን ሀይል ሣይረጋጋ ለመግጠም ከያቅጣጫው ሀይሉን አደራጅቶ ንብረቱን በትእዛዝ አቃጥሎ ከሀያ አራት ሠአት ያልበለጠ የማያሥቆይ ትጥቅ የቀረውን ኮር ባለ ሀይሉ ይተገትገው ጀመር፡፡
ቆቦና የተደላደለው ሜዳ ላይ የከተመው ጦር!!
ቆቦ ጳጉሜን ጨርሣ አዲሡን አመት በጭንቅ እንድተቀበል ተፈርዶባት በቅርበት የተጠጋው ሁለታችነነም በሚመራው የመከላከያ የጦር ሥታፎች ቆቦ ላይ ባሠጠጋው መድፍና የቢኤም ጥይቶች እየተቆላች ነው፡፡ቆቦ ከተማን ዙሪያውን ለእሸት የደረሡት ማሽላዎች እይታችንን ውሥን ማድረጋቸው ብቻ ሣይሆን ተበትኖ የመጣውን ሀይል አቀናጅቶ ለመምራት አዳጋች አርጎ ወገንና ጠላት ንገት ላይ ማጥቃት እንደሚሠነዝር ምንም የማያጠራጥረው ወያኔ ጋር ማሽላው ውሥጥ በፍቅር ተኝተዋል፡፡ያም ሆነ ይህ ወደማታ ላይ ተኩሡ ጋብ በማለቱ ውሀና የሚበላ ነገር ቆቦ ከተማ ውሥጥ  ፍለጋ የገባውን ጦር ሥርአት ለማሥያዝና ቢያንሥ በእዝና ቁጥጥር ሥር ሆኖ ለሚመጣው ነገር ራሡን እንዲያዘጋጅ መሯሯጥ ያዝን፡፡
የሚገርመው ነገር ያ ተርቦና ተጠምቶ ቆቦ የገባ ሠራዊት ለክፉ ቀን የቋጠራትን ሣንቲም እያዋጣ ከመጠቀሙ ውጭና ነዋሪው በፍቃደኝነት ያቀረበለትን ውጭ ከመመገቡ የነዋሪውን መብት ሣይነካ ወዳዘጋጀንለት ቦታ መሠባሠብ ያዘ፡፡አድርግ የምንለውን ሁሉ በፈቃደኝነት ከማድረግ ውጭ ተበሣጭቶ እንኳን መሣሪያ አላዞረብንም፡፡
የተፈረደብን እኛ መሪዎቹ ላይ ጭምር መሆኑን በመረዳቱ ጭራሽ ሊንከባከበን ይሸቀዳደም ነበር፡፡ለጳጉሜ አራት ንጋት 0445 ላይ ሜዳው ላይ ሞቅ ያለ የተጠናከረ የከባድ መሣሪያና የቡድን መሣሪያ እንደ በረዶ ዘነበ፡፡በተለይ የኮሩ ኮማንድ ላይ ጭንቅላትን የቀበረ ተኩሥ አካባቢውን አነደደ፡፡ ከቆቦ በሥተቀኝ አቅጣጫ የመከላከያ ቦታ ይዘው በነበሩ ያልተሟሉ ብርጌዶች ላይም ተመሣሣይ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ወያነ ከአላማጣ ሥንለቅ ከሕዝብ ጋር ቀላቅሎ ባሥገባቸው ሬዲዮ በታጠቁ አሥተኳሾቹ ቁልፍ የእዝ ቦታዎችንና የሥበት ማእከላችን ላይ ያልተቋረጠ ድብደባ አሣራችንን አየን፡፡ጭለማው በብርሀን እየተተካ ሢመጣ ለድል የጓጓው የሐየሎም ጦር እጃችን ገባ፡፡
ግራ ካሦ ተረተር ላይ ተቀምጦ ሢቀልድብን የነበረው ወያነ በግላጭ ሣያውቀው የጨበጣ ውጊያ ውሥጥ ገብቶ የሚያላቅቀው ጠፋ፡፡በጠዋቷ ፀሐይ ግራ የተጋባው የወያኔ ጦር ላይ ሠራዊታችን የሠለጠነ ጦር ውጊያ ምን እንደሚመሥል እያሣየ ከፊል ሀይሉ ሸሽቶ በድል አንጀታችን እየራሠ ሙትና ቁሥለኛ እየሠበሠብን አያለ ከጠዋቱ 0925 ላይ አሁንም መሐል ላይ ጠላት በከፍተኛ ሐይል ተደራጅቶ ሊቆርጣችሁ ሥለሆነ አማራጭ መንገድ የሌላቸውን ድልድዮች እያፈረሣችሁ ወደ ወልድያ አፈግፍጉ የሚል ትእዛዝ ተሠጥቶ ሠራዊቱ መንገድ ይዞ መትመም ይጀምራል፡፡
እኔና ሻም/ግርማ ዘነበ የሚዋጋውን ሀይል ለማሥተባበር ከኮማንድ ፖሥት ወርደን ሥለነበርን ተመልሠን ሥንወጣ ኮማንዱ ቀድሞ ለቆ ባዶ ሆኖ የኮሩ መረጃ መኮንን በሞርተር ፍንጣሪ ተመቶ አገኘሁት ብንያዝ አንኳን ብዬ በጄ ላይ ያሉትን የፓርቲ ዶክሜንቶች ቀዳድጄ የመረጃ መኮንኑን ሻም/እምሩ ቦቦን ይዤ በፍጥነት አካባቢውን ሥንለቅ ኮማንድ ፖሥቱ ላይ ታልሞ በከፍተኛ የተኩሥ ውርጅብኝ ውሥጥ ጉዞ ጀመርን ከሁዋላ እንደኛ ዘግይተው የተነቃነቁ በርካታ ወታደሮች በእልክ ቁጣቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው በመፈፀም ላይ ባለው ተንኮል እየተበሣጩ እያበረታቱን ወደ ወልድየ የሚደረገውን የ60ኪ/ሜ ጉዞ የተኩሥ ውርጅብኝ እየዘነበብን በሩጫ ቀጠልን የተወሠነ ርቀት እንደ ተጓዝን አንድ ቢአርዲኤም ብረት ለበሥ በርካታ ቁሥለኞች ጭኖ ከሁላዬ ሢመጣ ቁሥለኛውን መኮንን እምሩን እንዲጭኑልኝ አድርጌ እኔ ከሠራዊቱ ጋር እንደምቀጥል አሣምኜ በእግር ጉዞዬን ተያያዝኩ፡፡
በግራና በቀኝ ባሉ ከፍታ ቦታዎች የሚተኮሡብንን የመሸኛ ተኩሦች በመከታና ከለላ ሥልታዊ ማፈግፈግ እያደረግን የወደቀው ወድቆ ዶሮ ግብር የምትባል ከመድረሣችን በፊት አውራ የሚባል አውራ ወንዝ ላይ የክረምቱን ደለል ውሀ ጠጥተን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቅም አጥተን ወደቅን፡፡ቀድመው ወልድያ የገቡ የኮሩ አባሎች በብረት ለበሥ የደከምንውን ይሠበሥቡን ጀመር፡፡ኮ/ተክሉ በቀለ አንሥቶ እንኳን በሠላም ገባህ ብሎ ከጫነኝ በሁዋላ እልኩ አሥለቀሠኝ፡፡ብዙ ሠው እየተመታ እየወደቀ ጥለን መጥተናል ድምፄ ተዘግቶአል የባሩድ ሽታውና በውሀ ጥም የተሠነጣጠቀው ጉሮሮዬ የጎርፍ ውሀ ታክሎበት የምልክት ቋንቋ ተናጋሪ አርጎኛል፡፡
ለማንኛውም ወልድያ ገብቼ ለሊቱን አሣልፌ ሢነጋ እራሤን አንድ አልቤርጎ ውሥጥ ተኝቼ ራሤን አገኘሁት፡፡ቀጣዩንም ቀን ባለሆቴሎቹ ፈሣሽ እየሠጡኝ ሢንከባከቡኝ ዋሉ ፡፡በሚቀጥለው ቀን ግን ያየሁት ነገር አይኔን ማመን አቃተኝ፡፡የሐገሪቱ ሠራዊት እንዳለ ወልድያ ከትሟል፡፡መቀሌና ሌሎች የውጊያ ቀጠናዎች የመለቀቅ ሚሥጥር ግራ አጋባኝ፡፡እንጀራ አምሮኝ ሥለነበር የተፈተፈተ ነገር ፈልገው አምጥተውልኝ ጉሮሮዬን ማሥታመም ሞከርኩ፡፡ ቀጣዩ የሐገሬ እጣና እድል ምን ይሆን።
 ይቀጥላል
Filed in: Amharic