>

 የ <<ፊንፊኔ ኬኛ>> ቅዥት አንዱ አካል !!! (ኤልያስ አዲሴ)

 የ <<ፊንፊኔ ኬኛ>> ቅዥት አንዱ አካል !!!
ኤልያስ አዲሴ
* “በሁሉም መልኩ እናንተን ተጠቃሚ የሚያደርግ ህግ እናወጣለን” ብሎ ሰምተናል፡፡ ተመልከቱ አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡ ግን የአንድ ኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ህግ እናፀድቃለን የሚለው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ተብዬ ነው!
በፊንፊኔ ምክር ቤት እንወከል!
 ~ ፊንፊኔ ውስጥ እየኖርን ቴሌቪዥን የለንም! 
 ~ መሬታችን ተውስዶ ግን ተመልሰን በእኛው መሬት ላይ ጥበቃ ሆነናል!
 ~ ፊንፊኔ የእኛ ሆና ግን ከፊንፊኔ ተጠቃሚ እንዳንሆን ተደርገናል፡፡ እናም የቀበሌ ቤት ወይ ደግሞ ኮንዶሚኒየም ለልጆቻችን ቅድሚያ ይሰጥ!
~ የፊንፊኔ አነስተኛና ጥቃቅን ቢሮ ለእኛ ልጆች ቅድሚያ ሰጥቶ ያደራጅ!
 ~  ህገ-ወጥ ግንባታ ብሎ ያፀዳው መሬት ከእኛ የተዘረፈ ስለሆነ ወይ መንግስት ካሳ ይክፈለን አለያ ደግሞ ወደ ባለቤቶቹ ይመለስ!
—-
 ከላይ በጥቂቱ ለማንሳት የሞከርኳቸው ጥያቄዎች ዛሬ ከታከለ ኡማ ጋር ሊወያዩ አዳራሽ የተጋሩና ገበሬ ናቸው የተባሉ ሰዎች ያነሷቸው ናቸው፡፡  እውነት ለመናገር እንደ ከንቲባነቱ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር የተወያየበት መድረክ እንዳለ መረጃው የለኝም፡፡ ግን ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር የምክክር መድረክ ሲያዘጋጅ ይህ ለሶስተኛ አለያም አራተኛ ጊዜው ነው፡፡
 በአዲስ አበባ ጥግ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታቸውን እየቆረጡ ቸብችበዋል፡፡ አሁንም የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ያማረረው ህዝብ ያለችውን ጥሪት አሟጦ ይገዛል መንግስት ደግሞ ህገ-ወጥ ነህ ብሎ ላዩ ላይ ያፈርሳል፡፡ ይሄን ነው እንግዲህ መሬታችንን ተቀምተናል የሚሉት፡፡
  ከሰምኑ እንኳ ካራ ቆሬ አካባቢ በርካታ የአማራና ደቡብ ተወላጆች ከአካባቢው ነዋሪ ኦሮሞ መሬት ገዝተው የኖሩ ቢሆንም ህገ-ወጥ ተብለው ግን የጣዱትን ሳያወጡ እላያቸው ላይ ተንዷል፡፡ መሬት የመንግስትና ህዝብ ሆኖ መሸጥ መለወጥ አይቻልም ከተባለ ሻጭን ህጋዊ አድርጎ ገዥን ህገ-ወጥ የሚያደርገው የህግ ማዕቀፍ ከየት ነው የመጣው? ለኮንዲምንየም በሚል የተነሱትም ቢሆኑ ግምት ተሰጥቷቸው ሄደዋል፡፡ ግምቱ ደግሞ በህጉ የተቀመጠና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገዛበት ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ጋር የተገፉት?
 ከሰሞኑም የኦሮሞ ተወላጅ ወጣቶችን የሰበሰበው ኢንጅነር ታከለ በሁሉም መልኩ እናንተን ተጠቃሚ የሚያደርግ ህግ እናወጣለን ብሎ ሰምተናል፡፡ ተመልከቱ አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡ ግን የአንድ ኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ህግ እናፀድቃለን የሚለው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነው፡፡ በቅርቡ እንደሰማሁት ደግሞ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የኦሮሞ ተወላጅ ወጣቶች (ቄሮ) አደረጃጀት እየተቋቋመ ነው፡፡
የመታወቂያ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲቀየር የተደረገውና አዲስ ህግ እየጸደቀ የሚገኘውም ለዚሁ ተግባር እንዲመችና <<ፊንፊኔ የኦሮሞ ነች>> የሚለውን ህልም እውን ለማድረግ ነው፡፡ እንዴት ካላችሁኝ ደግሞ ከኦሮምያ ሁሉም አቅጣጫ ለሚመጡ ሰዎች የከተማዋን የንዋሪነት መታወቂያ በመስጠት በቀጣይ ለሚካሄደው ቆጠራ ዝግጁ በማድረግ የከተማዋን ዲሞግራፊ በመቀየር ሌላውን መግፋት ነው፡፡
ዛሬ ከታከለ ኡማ ጋር የተወያዩትም በአዲስ አበባ ምክር ቤት እንወከል ፤ የአነስተኛና ጥቃቅን አደረጃጀቶች ውስጥ ቅድሚያ ይሰጠን ፤ የቀበሌ አለያም ኮንዲምንየም ቤትም እንዲሁ የሚሉ ጥያቄዎችም የዚሁ <<ፊንፊኔ ኬኛ>> ቅዥት አንዱ አካል ነው፡፡ ኢንጅነር ታከለም ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጥያቄዎች የሚመልስ ህግ እናፀድቃለን ብሏል፡፡
Filed in: Amharic