>
5:13 pm - Sunday April 19, 1096

‹‹ሺህ ዝንብ መሶብ አይከፍትም›› (ተፈሪ መኮንን)

‹‹ሺህ ዝንብ መሶብ አይከፍትም››
ተፈሪ መኮንን
 …ይህን የሰላም የፍቅር የህብረት ዜማችንን የማይወዱ ወገኖች አሉ፡፡ እንደ ዓመለኛ በሬ፤ እንደ ጨካኝ አውሬ ዙሪያችንን እየዞሩ፤ የዘመናት የፍቅርና የመተሳሰብ ቅርሳችንን ሊነጥቁን አሸምቀው ያደባሉ። ሺህ ዘመናት አሻግሮ ከዚህ ያደረሰን የአብሮ መኖር እሴታችንን፤ የመተሳሰብና የመተጋገዝ የቤተሰብ መንፈስ የሚታይበት ወጋችንን፤ የአባት የቅደመ አያት ልማዳችንን አፍርሰው፤ እንደ ውሻ አናክሰው ሊያጫርሱን ይመኛሉ፤ ሌት እና ቀን ድብ እንቅ ይላሉ!!!
ውድ የሐገሬ ሰዎች!!!
ይድረስ ከምወዳችሁ የሀገሬ ሰዎች ኑሮ እንዴት ይዟችኋል። የቅዱሳን ጸሎት -ዱኣ ይሁናችሁ፡፡ ሰላም፣ ፍቅር እና ማስተዋል አይንሳችሁ፡፡ የአባቶች ዱኣ ጸሎት ይጠብቃችሁ፡፡ ‹‹ኤባ›› አባገዳ ሰላሙን ያብዛላችሁ። የአምላክ በረከት፣ ፀጋና ረድኤት አይራቃችሁ። አቦ የኢትዮጵያ አምላክ ብልጽግና እና አንድነቱን ያድላችሁ።
ውድ የሐገሬ ሰዎች፤
ዛሬ ይህን ደብዳቤ ስጽፍላችሁ ታግዬ፤ እንዳይመስላችሁ የተፋታሁ፤ ከአያሌ ወራት ዝምታዬ፤ በጽንፈኛ ፖለቲከኞችና በዘረኞች ላይ ካወጅኩት ኩርፊያዬ፤ እንዳይመስላችሁ ያመለጥኩኝ፤ ግፈኞችከፈጠሩብኝ ቁጣዬ፡፡ አሁንማ መች ኩርፊያ ብቻ፤ አሁንማ መች ቁጣ ብቻ፤ አሁንማ መች ንዴት ብቻ፤ ትዝብትም አሳጥቶኛል የመንፈስ እረፍት ዳርቻ፡፡
ውድ የሐገሬ ሰዎች፤
በገጽ አልተገጣጠምን – በአካል አታውቁኝ ይሆናል። ግን በጋራ ታሪክና በወል ባህል ደም ተዛምደናል፡፡ ከደም የወፈረ የአንድነት ውሃ ጠጥተን፤ በህገ መንግስት ተካይደን፤ በቃል ኪዳን ሰነድ እምነት ተጋምደን፤ በአንድ ሐገር ማህፀን ተኝተን፤ የአንድ ምድር ጡት ጠብተን፤ ዋድ ሳናፈርስ ዘመናት ፀንተን ኖረን፤ የፀረ ኮሎኒያሊስት የነጻነት ተጋድሎ ሸማ ደርበን፤ በገዢዎች ቀንበር አብረን ጎብጠን፤ በጋራ ትግል የገዢዎችን ቀንበር ሰብረን ወጥተን፤ የአምባገነኖችን ሰንሰለት በጣጥሰን፤ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች….›› ብለን፤ ህገ መንግስት አውጀን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ የህብረት ገመድ ፈትለን፤ ምን ቢቀጥን በማይበጠስ የደም፣ የባህል፣ የወግ፣ የትውፊት፣ የታሪክ፣ የዕድለ-ፈንታ ፍንጅ ተሳስረን፤ በሺ ዓመት ጣመን ያልዛለ የአብሮነት መንፈስ ፈጥረን፤ በአንድነት ጋዘና ከፍቅር ህብስት ተካፍለን፤ በፈጣሪ ቸርነት እስራ ምዕቱን ተሻገርን፤ ይኸው ከዚህ ደርሰናል፡፡

ውድ የሐገሬ ሰዎች፤

ዛሬ ይህን ደብዳቤ የጻፍኩት፤ ይህን ጦማር የከተብኩት፤ ሐሳባቸው ጥልቅ – ነገራቸው ጥብቅ የሆኑት፤ አንድም ብዙም ሆኖ መኖርን አሳምረው የሚያውቁት፤ ጎምቱ አባቶቻችን አውርሰውን የሄዱት፤ የህብረት – የሰብእና ሐይማኖት፤ ጓሚያ – ጮርቃ በሆነ እናበረጋ ሰራሽ ፖለቲካ፤ በምን ግዴ – በስንፍና – በአፍለኛ ስሜት እየተቦካ፤ ውል ያጣ የፖለቲካ ትዳራችን አድሮ ቃሪያ ሲሆን እያየሁ፤ ግራ ቢገባኝ፤ መቸገሬን ለመግለጽ ነው፡፡
አዎ ‹‹ሐምሌ ቢያባራ በጋ ይመስላል›› ይላሉ አበው። ደግሞ ዘፋኙ ‹‹አያውቁንም … እኛን አያውቁንም›› ብሏል፡፡ የየሠፈሩን ቋንቋ የሚናገሩ፤ አንክርዳድ በበዛበት የፖለቲካ ጠላ የሰከሩ፤ በእኔ እበልጥ እኔ አበልጥ ፉክክር የታወሩ፤ ሥልጣን የጨበጡ ጥቂት ሹማምንትና ልሂቃን፤ ግብዝ ፍቅራቸው በደራ ጊዜ ተስማምተን የምንኖር፤ ጤዛ ፍቅራቸው በርዶ በቀዘቀዘ ጊዜ በጠላትነት የምንገፋፋና የምንጠፋፋ ህዝቦች መስለን መታየታችን ይቆጨኛል፡፡
  ማተብና አንገት፤ ክታብና ደረት እንደሆኑ ሺህ ዘመናት የዘለቁትን ኢትዮጵያውያን በጉልት ፖለቲካ መቸርቸር ባይቻልም፤ ‹‹ቀጥኜ ቢያዩ ጅማት ለመኑኝ›› እንዲሉ ሆኖ፤ ፖለቲከኞቻችን በእጅጉ ደፈሩን፡፡ እኛም ብዙ ተሳሳትን፡፡ እናም የማን ልጆች መሆናችን ለጠፋብን እኛ እና ትልቅ ቁም ነገር ለዘነጉ ገዢዎቻችን ተግሳጽ እንዲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች ይህን ጦማር ሰድጃለሁ፡፡ እግረ መንገድ ልጆቻችን በጣም የሚወዷትን ህዳር 29ን እዘክራለሁ፡፡
ውድ የሐገሬ ሰዎች
አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት ቃል ገብተን፤ የሺህ ዘመናት ህብረታችንን በህገ መንግስት ቃል ኪዳን አጽንተን፤ ሐጋጌ ህግ በሆኑት የኢትዮጵያ ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የተገለጸውን የአብሮ መኖር ታሪካችንን ለማድመቅ እና ለማክበር እንጂ ለመለያየት አንድ አልሆንም፡፡ በአንድ ስም የምንጠራ፤ የአንዲት ሉዓላዊት እና በነጻነት ጸንታ እና ታፍራ የኖረች ሐገር ውድ ልጆች እንጂ የክልል ጭቃ ሹሞች ገባሮች አይደለንም፡፡ ወትሮም ‹‹ሺህ ዝንብ መሶብ አይከፍትም›› ነው የተባለ፡፡ በኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል ጸንቶ የኖረ ግንኙነት የሀኬተኛ ፖለቲከኞች ሒሳብ ማውራረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ሟች መሆናቸውን የሚዘነጉ ፖለቲከኞች፤ አስታዋሽ መቅጠር አለባቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ የፖለቲካ ጂጌ መስርተን፤ በእምነት፣ በመከባበበር፣ በፍቅርና በአንድነት መኖራችንን እንቀጥላለን፡፡ የአንድ ሐገር አፈር ፈጭተን ያደግን የአንዲት እናት ልጆች ሆነን እንዘልቃለን፡፡ ከአንድ ኢኮኖሚ መሶብ በልተን፤ በአንድ ስርዓተ ትምህርት ተኮትኩተን፤ ከአንድ የዕውቀት ምንጭ በተለያየ የቋንቋ ፅዋ እየጠጣንወደ ብልጽግና እጓዛለን፡፡
በሐዘን፣ በደስታ ተደጋግፈን፤ በተለያየ የባህል ዜማ የህብረት መዝሙር እየዘምርን፤ ከአንድ የፖለቲካ ሰማይ በሚወርድ የፍቅር ጠል ተጠምቀን፤ ዕጣ ፈንታችንን በአንድ ምሰሶ ደግፈን፤ እንደ ጸጋ – መክሊታችን በየዘርፉ ተሰማርተን፤ ለአንድ ሐገር ብልጽግና፤ በአንድ ወንፈል ተደራጅተን፤ ከድህነት ጋር የሞት – ሽረት ትግል ገጥመን፤ የጋራ ራዕይ ሰንቀን፤ ‹‹ፌዴራል›› ተብሎ የሚጠራ የጋራ ቤት ገንብተን፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሐገር አውራ እናደርጋታለን፡፡
 ይህን የአንድነት ጋዘና – ይህን ደቦ ጠብቀን፤ እርስ በራስ ተከባብረን፤ በአንድ ጎጆእናድራለን፡፡ የጋራ ዳስ ቀልሰን፤ በየመስኩ ተሰማርተን፤ ከአንድ ገበታ የአንድ እናት ጉርሻ እየበላን፤ በፖለቲካ ገበያ ተናግደን ተከራክረን፤ በቀንስ-ደምር ተጨቃጭቀን፤ ደግሞ አገና ተማተን ተጨባብጠን፤ እጅ ለእጅ ተሳስመን፤ ትከሻ ለትከሻ ተጋጭተን፤ ደህና ሰንብት ደህና ግባ ተባብለን፤ በአንድነት አደባባይ፤ አበቅቴ ቆጥረን ተገናኝተን፤ ከርሞ ለመገናኘት ተቃጥረን፤ ክረምቱን ከርመን፤ በጸደይ ወራት አበቦች አጊጠን፤ የመኸር አዝመራችንን በየጎታችን ከተን፤ ህዳር በመካያው ተመልሰን እንመጣለን፡፡
ውድ የሐገሬ ሰዎች፤
ዛሬ ይህን ዛንታ የደጎስኩት፤ የታሪክ ደረባ የከፈትኩት፤ የምታውቁትን በማነብነብ ከቶ ላደክማችሁ አይደለም፡፡ በዋዛ በወዘበሬታ፣ በቧልት ጊዜ ለማባከን አይደለም፡፡ ገና በመነሻዬ ‹‹እንደምን ሰንብታችኋል›› ማለቴም፤ የአምና የታች አምና ክራሞታችሁን ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም፡፡  ታች አምና ሰማዩ ጠል ነፍጎን፤ ኤልኒኖ በሚሉት አጉርጥ፤ አየር ንብረት ተዛብቶብን፤ ከክፉ አንጋዳ ጥሎን፡፡ ‹‹ከጓዳው ከአውድማ፤ አንዲት ጥሬ እንኳን ጠፍታ፤ ወገኔ በድርቅ ተጎድቶ፤ ሰውና እንስሳው ሁሉ መግቢያ አጥቶ፤ አባ መስጠት ገበሬ፤ አርብቶ አደሩ ተቸግሮ፤ የሚቆረጠም ጥሬ አጥቶ፤ የሚጠጣ አንዲት ጠብታ ውሃ እንኳን ተቸግሮ፤ መሳቀቁ አልጠፋብኝም፡፡  ይቅር የታች ያምናው ነገር6፡፡
ውድ የሐገሬ ሰዎች፤
በ2008 የኤልኒኖ ዲያቢሎስ ጦስ ገጥሞን፤ ሰማዩምጠል እምቢ ብሎ ከልክሎን፤ እነ ቡሬ -እነ ሲሳይ ቀንዳቸውን መሸክም አቅቷቸው፤ እሚነጩት ሣር እሚበጥሱት ቅጠል አጥተው፤ ሞፈር – ቀንበሩን እየሳቡ ቀየን በጩኸት ድምጽ ማድመቅ ረስተው፤ መሬቱን አገማሽሮ በማረስ፤ ሰውን በበረከት ማጥገብ ተስኗቸው፤ ‹‹ኧረ ስንቱን አሳለፍነው›› ጎበዝ!ግና ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት፤ ጥቂት ሰላም አግኝተን ተረባርበን፤ በአንድነት ለልማቱ ተሰልፈን፤ ትንሽ ጥሪት በመቋጠራችን፤ ድርቁ ረሃብ ሳይሆንብን፤ አንዲት ነፍስ እንኳን ሳያልፍብን ያን ክፉ መከራ ተሻገርን፡፡ እና ይህን መነሻ አድርገን፤ ህዳር 29 በሐረሪ ስንሰፍር፤ የጀመርነውን የጸረ ድህነት ትግል ይበልጥ ለማጠናከር ቃል መግባት አለብን፤ ደጋግመን፡፡
ውድ የሐገሬ ሰዎች፤
ድርቁ ክፉ ንፉግ ጠላት ሆኖብን፤ ቀድሞ እንደለመደው ደግሞ በሺዎች ሊያረግፈን፤ እንደ ደመኛ ጠላት ቆጥሮን፤ ሊያስለቅስ ልጆቻችንን፤ ፍርፋሪ ዳቦ ሊነፍገን፤ መጥቶ ነበር የሞት ሠራዊት ጠርቶብን፤ በሰሜን- በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ ከቦን፤ ግራ አጋብቶን አስጨንቆን፤ የሞት ነጋሪት ጎስሞ፤ የሬሳ ክምር ሊያደርገን፡፡ራብ የሚሉት ይህ ክፉ ጠላታችን፤ መጥቶ ነበር ፎክሮ አድብቶ ጎድቦ ሊይዘን፡፡ ግን በህብረት፣ በፍቅር፣ በልግስና በጽናት ቆመን፤ ዓለም ድንቅ እስኪሆንበት፤ በልዩ ትጋት ተንቀሳቅሰን፤ መልሰነዋል ኤልኒኖን ኩም አድርገን፡፡
የኤልኒኖን ሠራዊት መክተን፤ አሳፍረን ስንመልሰው፤ አልሸነፍ በማለታችንን እርር ድብን ያለችው፤  ‹‹ኤልኒኛ›› የሚሏት የጥፋት ውሃ አዝማች፤ በጎርፍ ልታጠፋን ተነሳች፡፡ ግና ወትሮ ዝግጁ ሆነን፤ በአንድ ሐሳብ፤ በአንድ ልብ ነቅተን ቆመን፤ እርሷንም እንደ ድርቁ አሳፈርናት፡፡ ወደ መጣችበት መለስናት። ይህን ሁሉ አውቃለሁ፡፡ እናም አሁን አንዴት ሰነበታችሁ ማለቴ፤ ይህን መከራ በመዘንጋት አይደለም፡፡ የለም በፍጹም፡፡
ውድ የሀገሬ ሰዎች
ከዚያ መከራ ተርፈን፤ ገና አንድ ትንፋሽ እንደሳብን፤ በመልካም አስተዳደር ችግር ሆድ የባሳቸው ዜጎች፤ በቁጣ ወደ አደባባይ ወጥተው፤ ወንድም ከወንድምተጋጭተው፤ የዜጎች ደም መፍሰሱን፤ የጋ ወጣቶች ህይወት መቀጠፉን፤ የሐገር የወገን ንብረት መቃጠሉንም አውቃለሁ፡፡ ‹‹የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ›› የሚያሰኝ ችግር ገጥሞን፤ ለሟች ለገዳይ አዝነን፤ በአንድ ዕድር በአንድ መካነ መቃብር ተላቅሰን፤ ሐዘን መቀመጣችንን አውቃለሁ፡፡ እናም ‹‹እንዴት ሰነበታችሁ ያልኩት፤ የወዳጅ ሰላምታዬን ለማቅረብ እንጂ፤ በግብዝነት አይደለም፡፡ ታዲያ ዛሬ ያ ሁሉ መከራ ገለል ብሎ፤ በሐገሪቱ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ፤ የፈራረሰው ተጠግኖ፤ የልማት ትግሉ ቀጥሎ ማየቴ እጅግ አስደስቶኛል፡፡ የሟርተኞች ቃል መክኖ ማየቴ ደስ ይለኛል፡፡
ውድ የሐገሬ /ሰዎች፤
ነቢይ ሁለቴ ይሞታል ይላሉ፡፡ አንድም አስቀድሞ የሚመጣውን ከወዲሁ አይቶ – በመንፈስ፤ አንድም የተፈራው ሞት ሲደርስ -በእውን፡፡ እኔም የነገሩን አያያዝ አይቼ፤ አለመጠን በጣም ሰግቼ ነበር፡፡ ጦማር ወደ እናንተ ለመስደድ ሁለት ሦስቴ ቃጥቼ ነበር። ግና መልዕክቱ የመርዶ መስሎ ታይቶኝ፤ ለእናንተ የጻፍኩትን ደብዳቤ፤ ለራሴ አንብቤ ተውኩት። ከሰንዱቅ ከትቼ ቆለፍኩት፡፡
ጭንቅ እና መከራን ለዘመድ መንገሩ የተገባ ቢሆንም፤ እኔ የምስራች እንጂ መርዶ መቼም ደስ አይልለኝም፡፡ አሁን ግን የምሥራች ልላችሁ፤ እንኳን ለህዳር 29 የብሔር ብሔረሰብ ቀን አደረሳችሁ ለማለት፤ ይኸው ጦማሬን ልኬአለሁ። የሰላም እና የፍቅር መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ እንዳገኛችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ውድ የሀገሬ ሰዎች፤
ይህን የሰላም የፍቅር የህብረት ዜማችንን የማይወዱ ወገኖች አሉ፡፡ እንደ ዓመለኛ በሬ፤ እንደ ጨካኝ አውሬ ዙሪያችንን እየዞሩ፤ የዘመናት የፍቅርና የመተሳሰብ ቅርሳችንን ሊነጥቁን አሸምቀው ያደባሉ። ሺህ ዘመናት አሻግሮ ከዚህ ያደረሰን የአብሮ መኖር እሴታችንን፤ የመተሳሰብና የመተጋገዝ የቤተሰብ መንፈስ የሚታይበት ወጋችንን፤ የአባት የቅደመ አያት ልማዳችንን አፍርሰው፤ እንደ ውሻ አናክሰው ሊያጫርሱን ይመኛሉ፤ ሌት እና ቀን ድብ እንቅ ይላሉ። ህዳር 29 ከአዲስ አበባበሚሰሙት መልዕክት መሸነፋቸውን ይረዳሉ፡፡
በሉ አዲስ አበባ ላይ በፍቅር እና በሰላም መንደር እስክንገናኝ በደህና ሰንብቱ፡፡
ከሰላምታ ጋር
ኢትዮጵያዊው ወንድማችሁ
Filed in: Amharic