>
5:13 pm - Thursday April 20, 3437

በጨለማው ጊዜ "ብርሃን ይሁን!" ያሉ ሰው ብርሃን ሲበራ "ጨለማ ናፈቀኝ!" አሉ!!! (ጌታሁን ሽመልስ)

በጨለማው ጊዜ “ብርሃን ይሁን!” ያሉ ሰው ብርሃን ሲበራ “ጨለማ ናፈቀኝ!” አሉ!!!
ጌታሁን ሽመልስ
 
አስራት አብርሃም “የፀጥታ ኃይሎችን የገደለው ኮ/ል ደመቀ ተፈትቶ ለምን  ጀኔራል ክንፈ ይታሰራል?”   ብሎ  “ተከራክሮ” ከተከራካሪዎቹ መካከል ስዩም ተሾመ ተገቢውን መልስ ሰጥቶታል። – ሊንኩ ተያይዟል።
አቶ አሥራት አብርሃ በኤል ቲቪ ብቅ ብለው አዝናኑኝ ሆድ ያማውን ብቅል ያወጣዋል ይላሉ አበው።በኤል ቲቪ ውይይት ያደርጉ የነበሩት ወገኖች የቅዱስ ጊዩርጊስ ፤ የአበሻ ፤ የሜታ ፤ የራያ ብቅል ንካክቷቸዋል ለማለት ሳይሆን የተሰወረ ነገር በሆነ ምክኒያት ይጎለጎላል ለማለት ብቻ ነው። አቶ አሥራት አብርሃን የማውቃቸው በጨለማው የህወሓት አገዛዝ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ አንስተው ፍትህን ፤ነጻነትን  አንድነትን፤ዕኩልነትን፤ ሰብአዊነትን አስመልክቶ ሲፋለሙ የቆዩ መሆናቸውን አውቃለሁ።
የእርሳቸው ፓርቲ የሆነው አረና የደረሰበትን መጉላላት አውቃለሁ። እርሳቸውም በአረና ፓርቲ ውስጥ አመራርና ጸሐፊ የነበሩ መሆናቸውን አውቃለሁ። አረና እያለ ለምን አረናን እንደተዉ አላውቅም።ይሁን እንጂ በአጋጣሚ በኤል ቲቪ አዲስ ቋንቋ እየተናገሩ ስሰማቸው ተዝናናሁ።ድሮ የሰማኋቸው፤ በጨለማው ጊዜ የማውቃቸው አቶ አሥራት አብርሃ መሆናቸውን ማመን ከበደኝ። በጨለማው ጊዜ ብርሃን ይሁን ያሉ ሰው በአሁኑ የለውጥ ጊዜ ምነው ብርሃን ሲበራ ጨለማ ናፈቀኝ እንዳሉ አልገባኝም።
ምሁር ናቸውና እስኪ ወደታሪክ አውድማ ልመልሳቸው:-
* እንግሊዝ ፀሐይ የማይጠልቅበት መንግሥት ገንብታ ነበር!
*  ቱርክ አውሮፓንና መካከለኛውን ምሥርቅ መንግሥቴ ነው ብላ ነበር!
* ፈረንሳይ አፍሪቃንና ሌሎች አገሮችም በራሷ መንገድ መርታ ነበር!
* ሂትለርም የጀርመን ሕዝብ ያለበት ሁሉ ግዛቴ ሊሆን ይገባል በማለት ተወጣጥሮ ነበር!
* ጃፓን ቻይናን የሚያክል አገር ደቁሳ ለመግዛት ሞክራ ነበር!
* እስፔንና ፖርቱጋል ደቡብ አሜሪካንና እስያን አስገብረው ነበር!
በመጨረሻ ሁሉም ወደ እውነተኛው ልካቸው ተመልሰዋል።በጦር ያስገበሯቸውንና የበዘበዟቸውን አገሮች በለመዱት መንገድ መግዛትና ከሰው ደረጃ አስወጥቶ መግዛት እንደማይችሉ ሲረዱ አሁን ይበዘብዟቸው የነበሩትን አገሮች ሁሉ  በስምምነት፤ በድርድር፤ በውል፤ በእኩልነት አብረዋቸው እየተጓዙ፤ እየኖሩ ነው።
አዲሱ የዓለም የኑሮ ዘይቤ ይህ ሆኗል። ሂትለር ጀርመንን በዓለም እንዲጠላና የነፍሰ ገዳዮች ምሳሌ እየሆነ በየዓመቱ ቢያንስ ቢያንስ በእሥራኤል መንግሥት ይዘከራል። ሁሉም ወደ እውነተኛው መጠናቸው፤ ልካቸው ፤ አቋማቸ፤ መለኪያቸው ፤ክብደታቸው መመለሳቸው አይቀሬ መሆኑን ታሪካ እያስተማረን ነው።
አቶ አሥራት አብርሃም ይህን ተገንዝበው ትግራይ ላይ የደረሰው በሂትለር፤ በእንግሊዝ፤ በጃፓንና በሌሎች የደረሰው ዓይነት ነው። ሁሉም ወደ መጠኑ፤ ወደ ልኩ ፤ ወደ ተጨባጭ ሁኔታው መመለሱ አይቀሬ እንደሆነ ሁሉ ህወሓትም ወደሚመጥነው ደረጃና ሚዛን ደርሷል።
አፓርታይድ እስከቻለ ድረስ ደቡብ አፍሪቃንና ሕዝቧን በልማትና በማሰልጠን ሰበብ መዘበረ ፤ዘረፈ፤ ጨፈጨፈ ጊዜው ሲደርስና የተሻለ አመራር ሊሰጥ የሚችል ሲመጣ እጁን መስጠት ግድ ነው።
ጊዜው አይፈቅድለትምና ካለው ከዓለም አካሄ ጋር ሊራመድ የሚችል(ሰብአዊነትን የሚያስከብር፤ የኢኮኖሚ እኩልነትን የሚደግፍ፤ሰውን በሰው ደረጃ የሚዳኝ)ይተካዋል።
እኔ እስከምረዳው ድረስ አቶ አሥራት አብርሃ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብና የታሪክ ሂደት ከአእምሯቸው የሚሰወር አይመስለኝም። አንድ የሆነ ነገር አእምሯቸውን አጨልሞ ካልሆነ በስተቀር። በጨለማው የህወሓት ዘመነ መንግሥት ስለዕኩልነት፤ ሰብአዊነትና ኢትዮጵያዊነት እየተከራከሩ በአሁኑ በዶ/ር አቢይ አህመድ አመራር ፤ያውም ኢህአዴግ በመረጠው መሪና የኢትዮጵያን ሕዝብ ባሰባሰበው፤ተበታትኖ የነበረውን በውጭ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ያስተባበረውን፤በየፊናው ህወሓትን ይዋጋ የነበረውን ሁሉ አገራቸው እንዲገቡ ያደረገውን ለመወንጀል ሲዳዳዎት ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን ጤንነትዎንና ከበስተጀርባዎ ያለውን መጠራጠር ጀመርኩ።
ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም ማለትዎ መልካም ነው። ግን አሁን የሚነገር ነገር ሳይሆን ቀደም ሲል ደመቅ ብሎ ሊነገር የሚገባው ነው።ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ህወሓት አማራን በመለየት ከቤንች ማጂ፣ ከጉሙዝ፤ ከጉራ ፈርዳ ፤ከኦሮሞ ክልል ሲፈናቀሉ ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም አልተባለም።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የመከላከያ ኃይላትን ጎንደር የገደለ ከተፈታ ጌታቸው አሰፋም ይቅር ሊባል ይገባዋል ነው ያሉን።በእውነትና በንጹህ ሕሊና ነው አቶ አሥራት አብርሃ እነዚህን ሰዎች የሚያወዳድሯቸው?ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በሌሊት የመጣበትን፤ የሕግ ሽፋን ሳይኖረው የመጣውን እጅህን ስጥ ባለበት ጊዜ ካስፈለገ በብርሃን አድርጉት ያለ ሰው የወሰደው የራስ መከላከል እርምጃ የጨለማውን ሠራዊት በወጣበት እንዲቀር አድርጎታል። ጌታቸው አሰፋ እኮ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ፤እርሱም እንዳለው የህወሓትን ጥቅምና ሥልጣን ለማስጠበቅ በየትኛውም ክልል የሚገኙትን የገደለ፤ ያስገደል፤ ጥፍር ያስነቀለ፤ ቃሊቲና ዝዋይ እንዲወረወሩ ያደረገ የጨለማው ወንበዴ ነው። አቶ አሥራት አብርሃ ይህን ጉዳይ አስተውለውታል?ተመራማሪና ምሁር ነዎትና የሚሳንዎት አይመስለኝም አንድ የሆነ ነገር አዲሱን የደብረጽዩን ገብረሚካኤል ግኝት እንዲያቀነቁኑና እንዲቀላቀሉ ካላደረገዎት።
በህወሓት ሥርዎ መንግሥት ጊዜ በሙስና የታሰሩትን እነገብረዋህድን በምሳሌ ደረጃ አንስተው ክንፈ ዳኘን ከእነርሱ ጋር ሲያወዳድሩ ግራ ገባኝ። በጨለማው ጊዜ ሲከራከሩ የነበሩት ህወሓት ኢፍትሃዊ አሠራር በመፈጸሙ ነው። ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የታሰሩትን እነ አቶ መላኩ ፋንታን አንስተው የሌቦች ቁንጮ፤የኢትዮጵያን ሕዝብ ንብረት ያወደመን ክንፈ ዳኘን ሲያወዳድሩ ትናንትና ስለፍትህ ያቀነቅኑ የነበሩት ከልብ መሆኑን እንድጠራጠር አደረገኝ። ይባስ ብለው የሕጻናትን የመከላከያ ዘዴ መጠቀምዎ በእርስዎና በመሰሎችዎ እንዳፍር አደረገኝ።ሕጻናት አባታቸው ሲገርፋቸው ለምን እኔን ብቻ ለምን እሱን እሷን አትገርፋትም ይላሉ።
አሁን ደግሞ የሕጻናትን ቀመር ተሸክመው፤ያውም በአደባባይ፤ ለምን ኃይለማሪያም ደሳለኝና ደመቀ መኮንን አልታሰሩም ብለው የክርከርዎ ጭብጥ አድርገው ሲያቀርቡ ያሳፍራል። ሕግ መከበር ሲጀምር መልካም ነው እንደማለት ኢትዮጵያዊነቴን እንድጠራጠር አደረገኝ ሲሉ ድሮም በኢትዮጵያዊነት ሲከራከሩ መቆየትዎን ተጠራጠርኩ።ትግራይን ሕዝብ ግን ከወር በፊት አይቼው ከአክሱም፤ አድዋ፤እንቲጮ፤ አዲግራት፤ መቀሌ፤ ህዋኔ፤ ቤትመራ፤ ማይጨው ኢትዮጵ ያዊነቱን አሳይቶኛልና የትግራይ ሰልፍ የደብረጽዮንና የስኳር  ብቻ ነው።
Filed in: Amharic