>

የዋሽንግተኑ ስብሰባና  አንድምታው!!!  (ሀይለ ገብርኤል አያሌው)

የዋሽንግተኑ ስብሰባና  አንድምታው!!!
 ሀይለ ገብርኤል አያሌው
 
እንደ መግቢያ:
እኔን ብትጠይቁኝ  ዶ/ር ደብረፂዮን “ከአማራ ህዝብ የሱዳን ህዝብ ይሻለናል!” ሲል እኔ አልሰማሁም። አለ ሲባል ግን ሰምቻለሁ ። እኔን ብትጠይቁኝ ግን …“በብዙ እጥፍ የትግራይ ህዝብ ይበልጥብኛል!” 
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው (ዋሽንግተን ዲሲ)
”በለውጡ ዋናው ነጻ የወጣነው እኛ የኢህአዴግ አባላት ነን!” 
”እሸነፋለሁ ያለው ቡድን መሸነፉን ሳያውቅ እናሸንፋለን ያልነው ሰዎችም እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ሳንሆን ዶክተር አብይን ስንመርጥ አሸነፍን… አሁን እያየን ያለነው የድሉን ውጤት ነው፤ ምን እናግዝ ያላችሁን እስከ ድሉ ፍጻሜ ድረስ አብራችሁን ሁኑ”
ዶር  አምባቸው_መኮነን
ሕወሃት አማራን አከርካሪውን ሰብረነዋል ብላ ደንፍታለች:: ድንፉታም ብቻ አይደለም ይህንን እውነት ብላ አምና ተከታዮቿን ጭምር አሳምናለች:: አማራ ሊጠፋ የማይችል ኢትዮጵያዊ ተክል ነው:: ጠፉ ሲባል የሚገኝ: ወደቀ ሲሉት የሚነሳ ታላቅ ሕዝብ ነው:: ኢትዮጵያ ደግማ ደጋግማ ወድቃ ተነስታለች:: አማራም ኢትዮጵያዊ ነውና ከቶም ወድቆ አልቀረም:: ይህው እንዲህ ደምቆ በግርማ ለመነሳት በቃ::
አማራ ይደራጅ ብለው ቀድመው ትግል የጀመሩት ፕሮፌሰር አስራትና ተከታዮቻቸው መስፈሪያ የለሽ ዋጋ  ከፍለዋል:: የትግሉ መክረር የመስዋዕትነቱ ክብደት ብዙዎችን እሽሽቷል:: ከሁሉ በላይ ግን ትጥቅ አስፈቺውና ትግሉን የጎተተው ሆዳሙና ጥራዝ ነጠቁ የአማራ ወገን ለመሆኑ ያኔ ፕሮፌሶር አስራት ተናግረውት ነበር:: በአማራነት መደራጀት ነውርና  ሃገር አፍራሽ አስተሳሰብ እንደሆነ በሰፊው ተሰብኳል:: በዚህም ግራ የተጋባው ሕዝብ በማንነቱ ተነጥሎ የሚደርስበትን በደል የሚከላከልበት ጥግ አጥቶ ቆይቷል::
ከታላቁ የአማራ ሕዝብ መሪና ተቆርቋሪ አስራት እልፈት በሗላ አማራን ለማደራጀት ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም:: በአማራው ሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረው መከራ ከእሳት ወደ እረመጥ ቢሆንም ይህንን መከራ ተደራጅቶ ለመመከት ለትግል የሚቆም አይደለም ለመደገፍ እንኳ የሚፈቅድ ወገን ማየት ብርቅ ሆኖ ቆይቷል::
አማራ እንደ ሕዝብ በየአቅጣጫው ሲዋከብ አለሁ የሚለው በደሉንና ስቃዩን ቢያንስ የሚያስተጋባለት ተቋም በማጣቱ ለብዙ ችግር ተዳርጏል:: ይህንን ክፍተት ለመሙላት እጅግ አድካሚና እልህ አስጨራሽ ጥረት ተሞክሯል:: በሃገር ውስጥ በነበረው የለየለት ፀረ አማራ ፋሽስታዊ የወያኔ አገዛዝ መላወሻ በመጥፋቱ በይፋ የተደራጀ ትግል ማድረግ ሳይቻል ቆይቷል:: ነገር ግን ጀግኖች አርበኞች በነፍጥ ቆራጥ ታጋዮች በሰላም ባለው ጠባብ መንገድ ተጉዘው ለወገናቸው ድምጽ ለመሆን በመስዋዕትነት የታጀበ ጥረት አድርገዋል::
አሁን ቀን ተለወጠ ክብር ለተሰውት እልፍ አዕላፍ ታጋዮች በደማቸው በዋጁት ነጻነት የጨለመው እንዲነጋ ሆኖኗል:: በነዚህ ጀግኖች መስዋዕትነት ከዘመናት ባርነትና ወያኔዎች  የራሱን ወገን እንዲያጠፋ ያደራጁት ምርኮኛ ቡድን ብአዴን (አዴፓ) ሰንሰለቱ ተፈቶለት ለነጻነት በቅቷል:: አዴፓ  የትላንት በደሉ ቀርቶለት አዲስ ምዕራፍ እንዲጀምር እንድል ተሰጥቶት የለውጡን ሂደት በማሳለጥ ገንቢ ሚና ለመጫወት በቅቷል:: በዚህም የሕዝብን ድጋፍ አግኝቷል:: የበለጠም የለውጥ ጉዞውን በማፍጠን የአማራውን ሕዝብ መብትና ጥቅም እንዲያስከብር ብሎም የኢትዮጵያን አንድነት በጸና መሰረት ላይ እንዲያቆም ከባድ ሃላፊነት ተጥሎበትል::
እነሳሞራ ከእንግዲህ መቼም እይነሳም: ያሉት አማራ በሚደንቅ መነቃቃት ለሃገሩና ለማንነቱ ዘብ እንደሚቆም አሳይቷል:: ዛሬ በዚህ በሰሜን አሜሪካ ያለው የአማራ ተወላጅ የአዴፓ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ በነቂስ ወጥቶ አንድነቱን ለማሳየት ችሏል:: የስብሰባው ሂደት ምንም ይሁን ምን በዚህ እለት የታየው የሕዝቡ ስሜትና ምላሽ የሚደንቅ ነው:: እንግዶቹም እማራነትን ከኢትዮጵያዊነት አስማምተው ያደረጉት ግሩም ገለጻ በእንግድነት የተገኙትን የሌላ ብሄር ኢትዮጵያንን ጨምሮ አርክቷል:: በተለይ በባህል ልብሳቸው አሸብርቀው ስብሰባውን ያደመቁት የኦሮሞ ወገኖቻችን ተሳትፎ አንድነታችንን ከማሳየቱም በላይ ልዩ ውበት ነበረው::
ይህ እለት ሌላ ያሳየው እውነት በአማራነት መደራጀት ያለውን አስፈላጊነት ነው:: የሚገርመው ጠርዝ ይዞ የአማራን መደራጀት ሲኮንን ከኖረው ምሁርና በተደራጀ መልኩ ሲታገሉት የነበሩ አፍቃሪ አንድነቶች ጭምር በጋራ የታደሙበት ስብሰባ ነበር:; የአማራው መደራጀ መሰረታዊ ተልዕኮውና ዋና ግቡ በማንነቱ ላይ የተቃጣውን እደጋ ተከላክሎ በሃገሩ በኢትዮጵያ ከሁሉም ወገኖቹ ጋር በእኩልነትና በጋራ መኖር የሚችልበትን ፖለቲካዊ ስርዐት መፍጠር ነው:: በዚህ ስብሰባም በእኔ እምነት ተሰብሳቢውም ሆነ ሰብሳቢዌቹ በጋራ የተስማሙበት ነጥብ ይህንኑ ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው:
Filed in: Amharic