>

ካባ ለእርኩሰት! የቤተክርስቲያን ውርደት ለሃገር ውድቀት! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

ካባ ለእርኩሰት! 
የቤተክርስቲያን ውርደት ለሃገር ውድቀት!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ቤተመንግስቱን ያጸዳው የለውጥ መዐበል ቤተ ክህነቱን እንዲጎበኝ ግፊት ይፈልጋል:: እንዲያውም ለፖለቲካችን መረን መልቀቅ ለሞራል ውድቀትና ለሌብነት መንሰራፋት ከማንም በላይ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ካህናት ናቸው!
          ቅዱስ መጽሃፍ ” ክብራቸው በነውራቸው  ሆዳቸው አምላከቸው” ያለው እውን ሆኖ አየነው:: የቅድስናው ተክሊል ለውርደት የክብር መገለጫው ካባ ለቀልድ አውደ ምህረቱ  የአህዛብ መድረክ አደረጉት:: ለዘረኛና ለደንቆሮ ነውሩ ክብር ነው:: ሃሰት መገለጫው ማስመሰል የሰርክ ተግዳሮቱ ነው:: የአረመኔው ሽብር ድርጅት የሕወሃቱ መሪ ደብረጺዎን ንግስና ቀረሽ ወረብ ቀረበለት::
የቤተክርስቲያን ጠላት የመነኮሳት አሳዳጅ የአይነኬው የዋልድባ ገዳም ሰላም አደፍራሽ: ሊመከር ሊወገዝ ሲገባ በታቦተ ጺዖን ፊት የማይገባውን አገኘ :: ለክፉቱ ሽልማትን ጥፍር ለማስነቀሉና ንጹሃንን ለማስገደሉ የክብር ካባን ተደረበለት::
ጻድቃን የጸለዩላት ቅዱሳን የተሰውላት የሲዖል ደጆች አያናውጹሽም ተብሎ የተነገረላት ቅድስት ቤተክርስቲያን ለሆዳቸው ባደሩና በመንደርተኝነት በተንበረከኩ የሃይማኖት መሪዎች ደጋግማ ስትወድቅ አየናት:: በተለይ በዘመነ ወያኔ ክብሯ ተገፎና ቅድስናዋ እርቆ ትጠብቅ ዘንድ የተሰጣትን መንጋ ለአራጆችና ለሸቃጮች አሳልፋ ስትሰጥ ቆይታለች:: የጽጽስና መመዘኛው ብሕትውናና ስርዐተ ቤተክርስቲያን መሆኑ ቀርቶ ለትከሻቸው የሚከብደውን የወታደራዊውን ሹመት ካለከልካይ እንደጫኑት መንፈሳዊውንም ምንኩስና በጎጥና በፓለቲካ ታማኝነት ሲቀባበሉት እንደቆዩ እናውቃለን::
ዛሬም ያየንው የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው:: መነኮሳቱ የፖለቲካው ጥገኛ እንጂ የቤተክርስቲያን ጠባቂ አይደሉም:: ጥቂት መንፈሳዊነት ቢኖራቸው አይን ያየውን ጆሮ የሰማውን የወንጀል ተግባር በተጸየፉ ነበር:: እውነተኛ መንፈሳዊ አባት ቢኖር ብልት ሲኮላሽ ወንድ ሲደፈር ሰዶም ሲነግስ ማቅ ነስንሶ ምዕመናንን ሰብስቦ እግዚዖ ባስባለ ነበር:: ግን አባት የሚሆን እውነተኛ የሃማኖት መሪ ባለመኖሩ የመንፈሳዊውን መንበር ለነውረኞች ባላደረጉት::
ታቦተ ጽዮን ቀሳፊ ናት ፖለቲካና የዘር  ድንበር የምታሰምርበት የካድሬ መሰማሪያ ሳትሆን የሰማይ ደጅ የተባለች የቅድስና ስፍራ ናት:: አቅምና ግዜ ፈቀደልኝ ብሎ ማንም እንዳሻው አይሆንባትም:: መጽሃፍም የሚነግረን ይህንኑ ነው:: የካህኑ ኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ታቦተ ጺዎንን ተዳፍረው ሲቀሰፉ አባታቸውም ነውራቸውን አይቶ ባለመገሰጹ ለታቦተ ጺዎን መማረክና እሱም ለሞት መዳረጉን መጽሃፉ ይናገራል:: የሃጢያት ደመወዙ ሞት ነው እንዲል ::በፖለቲካው ሜዳ ሽንፈት ሲገጥም በመንፈሳዊነት ላይ ለመረማመድ መሞከር ከኪሳራ አያድንም:;
ቤተመንግስቱን ያጸዳው የለውጥ መዐበል ቤተ ክህነቱን እንዲጎበኝ ግፊት ይፈልጋል:: እንዲያውም ለፖለቲካችን መረን መልቀቅ ለሞራል ውድቀትና ለሌብነት መንሰራፋት ከማንም በላይ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ካህናት ናቸው:: በዚህ ላይ ውይይት ሊከፈትና ስርዐት እንዲበጅለት እራሱን የቻለ ትግል ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል::…..
አስተዋይ ሕሊና ፈጣሪ ያድለን!!!
Filed in: Amharic