>

የተከበራችሁ አክቲቪስቶች! ምን ይመስላችኋል? (ደረጀ ደስታ)

የተከበራችሁ አክቲቪስቶች! ምን ይመስላችኋል?
ደረጀ ደስታ
እስኪ ደግሞ ኑ! ሌላ ተስፋ እስኪመጣ ይኸኛውን ተስፋ እንቁረጠው። የምሬቱንም አረን “እንቀልድ’’። ይህ ነገር እሚሆን አይመስልም። ነገሩ ሁሉ የበላይነትን የማረጋገጥ ጨዋታ እየመሰለ ነው። ስለዚህ እንዲህ እናስብ።
እነሆ መፍትሄው:- አሁን መንግሥት የኢንዲስትሪ ዞን ብሎ መሬት ከልሎ ይሰጣል። ስለሆነም የመፍትሔ ዞን እሚል አንድ በጣም ሰፊ ቦታ ይከለል። እዚያ ቦታ ላይ አንድ ትልቅ የመነታሪኪያ አዳራሽ እሚገነባበትና ሌላ ደግሞ ብርቅዬ የዱር አራዊት እንደሚከለሉበት አንድ እጅግ ትልቅ ተራራ ሜዳና በረሃም ያለበት የፍልሚያ ወረዳ ተፈልጎ ይዘጋጃል ። እዚያ ቦታ ላይ እነዚህ አንዳቸውን ሌላኛቸውን ማስገበር እሚፈልጉ የኦሮሞ፣ የአማራ የትግራይና የሌሎችም ብሄር ብሔረሰብ ተፋላሚ አርበኞች  እንዲገቡ ይደረግ። ሁሉም ጎጠኞቹን ቡድኖቻቸውን ይዘው ጣቃ ጣቃ እሚያህል ባንዲራቸውን እያነገቡ ይግቡ። መንግሥት እሚያስፈልጋቸውን ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስከ ጦር ጎራዴ ሜንጫ ሳይቀር አዘጋጅቶ ይስጣቸው።
እንደየምድባቸው እሚዳኛቸውም ከፈለጉ የፍልሚያ ፌዴሬሽን ይቋቋምላቸው። ለአጀቡም በጥባጭ ቀስቃሽና ሰላም በታኝ የሆኑ ጎሰኛ አክቲቪስቶች እየተመረጡ ይሂዱላቸው። የፍልሚያ ጭፍጨፋው፣ ጨዋታቸውና የሰማዕት ተጋድሏቸው በቀጥታ ቴሌቪዥን ይተላለፍ። ተጋድለውና ተሸናንፈው የበላይነት ዋንጫቸውን አንስተው ሲጨርሱ ተመልሰው ይምጡ።
ከዚያ በኋላ በብሔረሰብነታቸው ምርጥና የበላይ፣ በጎሰኝነታቸው አቻ እማይገኝላቸው የጀግኖች ጀግና የሆኑትን ብሄሮች አምነንና ገብረን እናድርላቸዋለን። በቃ ከዚያ በኋላ ሲያልቅ ይንገሩን። እዚህ ሰላም ወዳድ ፣ ተቃቅፎና ተስማምቶ አዳሪ፣ ለነፍስ እምንፈራና እምንራራ ሆነን እምንኖር፣ የማንነት ችግር የሌለብን ዜጎች መካከል ገብተው እንዳያስቸግሩን መንግሥት ሥፍራውን በማመቻቸት እርምጃ ይውሰድ። እሚፈልጉት ሥልጣንም ስለሆነ ለአሸናፊው ወገን ሥልጣን እንደሚለቀቅም ቃል እንግባላቸው።  ስለዚህ መሬቱን እምንሞትበት እንጂ በሰላም እማንኖርበበት ስለሆነ ሰዎቹም የልማትና የሀሳብ ሳይሆን የጦር ሜዳ ጀግኖች ናቸውና ይገዳደሉበት።
ሰብአዊ የመገዳደል መብታቸው ከተሟላላቸው ሌላ ምን ያስፈልጋቸዋል? ካልሆነ ግን ዛሬ ፖሊስ መግደል የጀመሩ ነገ ምን ሊያመጡ ይችላሉ። ፖሊስ ሰው ብቻ አይደለም ተቋም ነው። ፖሊስ መግደል ህግና ተቋም መግደል ብቻ ሳይሆን ግልጽ ጦርነት ነው። ነገ መንግሥት ተቆጥቶ እያደነ ቢገድላቸው፣ እኛንም አገርንም አብሮ አሳስቶም ሆነ አምታቶ መግደሉ አይቀርም። ስለሆነም ባስቸኳይ አንፈታም ያሉትን መሣሪያቸውን ታጥቀው አናስረክብም እሚሉትን ሌቦቻቸውን ታቅፈው ወደ ውጊያ ካምፓቸው እንዲገቡ አስገዳጅ ምርጫውን ያሳውቃቸው። አያይ እኛ መነጋገር እንጂ መገዳደል አንፈልግም ካሉም እዚያው ከተሠራው ትልቁ የመነታረኪያ አዳራሽ ገብተው ተከራክረውና ተማምነው የጠፋባቸውን ማንነታቸውን አግኝተውና አረጋጠው እስኪወጡ እዚያ ይቀመጡ።
እኛም ትንሽ ትንፋሽ እንውሰድ።  ካለበለዚያ ግድያው፣ ክርክሩ፣ ግርግሩ፣ ንትርኩ፣ ሰልፉ፣ ጩኸቱና ሁከቱ ማለቂያ ስለሌለው ጎሰኞች ተሸናንፈው እስኪተማመኑ እኛ ህይወት ላይኖረን ነው። ስለዚህ የአመጽ ሊቅ የሰላም ጠንቅ የሆናችሁ፣ መበተን እየቻላችሁ የበተናችሁትን መልሶ መሰብሰብ ያቃታችሁ አክቲቪስቶች መፈክራችሁ – ወይ ተሸናነፉ ወይ ተቃቀፉ! እሚል ቢሆን ምን ይመስላችኋል?
Filed in: Amharic