>

የኤርትራ ህልም! (ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

የኤርትራ ህልም!
ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
ኤርትራ የአብረሃ ደቦጭ ሀገር! የሞገሥ አስገዶም ሀገር! የዘርዓይ ደረስ ሀገር! የሎሬንዞ ታዕዛዝ ሀገር! የደጃች ሀረጎት ሀገር! በአይበገሬ ጀግንነታቸው ድፍን አፍሪቃን ያኮሩ አርበኞች የበቀሉበት ምድር!
—-
ኤርትራ ድሮ ከእኛ ጋር ነበረች፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሤ ለሁላችንም አስፈላጊ የነበረውን የፌዴሬሽን ፎርሙላ ሰረዙትና ህዝቡን አስቀየሙት፡፡ ደርግ ደግሞ የራሳችንን ህዝብ እንደ ባዕድ እየቆጠረ በመትረየስ አጨደው፡፡ በታንክ ደመሰሰው፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቱ “አደይ ኤሪቲሪያ”ን እየዘመረ ወደ ባርካና ሳህል ነጎደ፡፡ ራሱን አደራጅቶ ጀብሃና ሻዕቢያ ሆኖ መጣ፡፡ ውጤቱም 1983 ላይ ታየ፡፡
የደርግና የኃይለ ሥላሤ መንግሥታት ያደረጓቸው ነገሮች ሲገርሙን በጣም ግራ የሚያጋባው ሶስተኛው መንግሥታችን መጣ፡፡ ይህ የኛ መንግሥት በጅምሩ ላይ ሰላም ፈላጊ መስሎ ቀረበ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን መንግሥቱ ከሚከተለው ግልጽነት የጎደለው አሰራር የተነሳ በ1990 ሺዎችን ያረገፈ ግዙፍ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ህዝቦች ተጋደሉ፡፡ እነሆ ዛሬም ድረስ ነገሩ ሳይለይለት በጨለማ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
እኛ ግን ተስፋ አንቆርጥም! በአያያዝ ጉድለት የተለየንን ወገናችንን መመለስ እንፈልጋለን፡፡ ህዝቡ ለጊዜው ሪፈረንደም አድርጎ ነጻነቱን ማወጁን እናደግፋለን፡፡ ቢሆንም ህልም አይከለከለምና አንድ ቀን ተቀራርበን በጋራ ስለመስራት እንወያይ ይሆናል ብለን እናልማለን፡፡ የኛ ልጆች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ስለመስራት ያስቡ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜም አሁን የምንመኘው በአንድነት ውብ የመሆን ሚስጢራችን ይመለስልናል ብለን እንመኛለን፡፡ ምን ይታወቃል? ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም፡፡
ወገኖቼ ደጉን ነው የተመኘሁት፡፡ በቅን ልቦና በርትተን ከጸለይንና ከኛ የሚጠበቀውን ካደረግን ሁሉንም የሚችለው ፈጣሪ ህልማችንን እውን ያደርግልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
——-
ምን እንደጣለብኝ እንጃ! ያንን ምድር እጅግ ሲበዛ እወደዋለሁ፡፡ እኔ ለተወለድኩበትና አብዛኛውን ዕድሜዬን ለጨረስኩበት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልል ጎረቤት ከሆነችው ሶማሊያ ይልቅ በ1600 ኪ.ሜ. የምትርቀው አስመራ ናት የምትናፍቀኝ፡፡ ስለሶማሊያ የተጻፈ መጽሐፍ ማንበብ ብዙም አይማርከኝም፡፡ ስለ ኤርትራ የተጻፈ መጽሐፍ ካጋጠመኝ ግን ሳላየው አላልፍም (ይህ ግን ሶማሊያን ከመጥላት እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ)፡፡
ታዲያ በርካቶቻችሁም እንደኔው ትመስሉኛላችሁ፡፡ ለምሳሌ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲታተም የቆየው የበኒ አምሩን ወጣት የሚያሳየው ፖስተር ዛሬም ድረስ ከኛ ጋር ተሳስሮ ነው ያለው፡፡ አሁንም ድረስ በበርካታ ስፍራዎች ተለጥፎ አይቼዋለሁ፡፡ በፌስቡክም እርሱን እንደ ፕሮፋይል ፒክቸር የሚጠቀም ኢትዮጵያዊ ሞልቷል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራን ሙዚቃ የሚያዳምጡ ሰዎች በሽ ናቸው፡፡ ደራሲ መሐመድ ሳልማን መቐለ ሄዶ ያየው ነገር ቢያስገርመው “በኤርትራ ሙዚቃ የምትጨፍር ከተማ” የሚል አስደናቂ ወግ ጽፎ እውነቱን አስረድቶናል፡፡ መንግሥታት ቢጣሉ እንኳ ህዝቦች ምንጊዜም እንደሚነፋፈቁ ከዚህ በላይ የሚያስረዳ ዋቢ ያለ አይመስለኝም፡፡
——–
ማርታ ሀይሉን አስታወሳችኋት? አዎን! ማርታን “ብራ… ነው… ብራ ነው”፤ “አዘዞ”፤ “ሎጋ ..ና እናውጋ” በተሰኙት ዘፈኖቿ እናውቃታለን፡፡ ከማርታ ዘፈኖች ዘወትር ቀልቤን ይገዛ የነበረው ግን የትግርኛ ዜማዋ ነው፡፡ አዝማቹ እንዲህ ይመስለኛል፡፡
ካብ አስመራ ድንገት ርእዮ
ምጽዋ ገባሁ ልበይ ሕብዮ፡፡
እንተርጉመው እንዴ?… ግድ የለም ማርታ ራሷ እንዲህ እያለች በአማርኛ ተርጉማዋለች፡፡
“ከአስመራ ድንገት አይቼው
ምጽዋ ገባሁ ልቤን ሰጥቼው”፡፡
አዎን! ትናንት የኛ ናት ስንላት ለነበረችው ኤርትራ ነው እንዲህ የዘመርንላት፡፡ ዛሬም ብንዘምርላት እንከበራለን እንጂ አንወቀስም፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ደረጃ ነው የተለያየነው፡፡ ሁለት ፓስፖርት እንዲኖረን ነው የተደረግነው፡፡ ሁለታችንም ግን አንድ ህዝቦች ነን፡፡ በደምም ሆነ በባህል በጣም የተዋሃድን የአንድ መሬት ብቃዮች ነን፡፡ ሁለታችንም የተዋብን የሴምና የኩሽ ህዝቦች ውቅር ነን፡፡ እንደኛ የሚያምር ህዝብ በትኛውም ዓለም የለም፡፡ የጀበና ቡና፣ ዶሮ ወጥ፣ ድፎ ዳቦ፣ የስጋ ፍትፍት፣ አምባሻ፣ ወዘተ…. ሁለታችን ዘንድ ብቻ ነው ያለው፡፡
—–
በርግጥ እላችኋለሁ፡፡ በምንባብና በወሬ እንጂ በአካል የማላውቃት ኤርትራ ትናፍቀኛለች! ያ በታሪክ ምዕራፎች “ምድሪ ባህረ ነጋሽ” እየተባለ ሲጠራ የኖረው ጀግና መሬትና ህዝብ ይናፍቀኛል፡፡ ያ የሰሜኑ በረኛ እያልን ስንመካበት የነበረው ህዝባችን ይናፍቃል፡፡
እውነትም ኤርትራ ! የዳማት ታሪክ ውቅር! የመጠራ አብያተ መንግሥታት ከርስ! የሀውልቲ ፍርስራሾች ቀብር! የአዱሊስና የዙላ ወደቦች መዘክር! የሱዋኪምና የዳህላክ ሱልጣኖች ደብር!
ኤርትራ የአብረሃ ደቦጭ ሀገር! የሞገሥ አስገዶም ሀገር! የዘርዓይ ደረስ ሀገር! የሎሬንዞ ታዕዛዝ ሀገር! የደጃች ሀረጎት ሀገር! በአይበገሬ ጀግንነታቸው ድፍን አፍሪቃን ያኮሩ አርበኞች የበቀሉበት ምድር!
ኤርትራ የበረከት መንግሥተ አብ ሀገር! የአብረሃም አፈወርቂ ሀገር! የአሕመድ ሼኽ ሀገር! የሄለን መለስ ሀገር! የየማነ ባሪያው ሀገር! የሄለን ጳውሎስ ሀገር! በስርቅርቅ ድምጻቸው የሰውን ልብ እየሰረሰሩ የመግባት ሀይል ያላቸው የጥበብ ከዋክብት የወጡበት መንደር!
ኤርትራ የፊያሜታ ጊላይ ሀገር! የስዕላይ በራኺ ሀገር! የኦቦይ ተኽሌ ሀገር! የተክላይ ዘድንግል ሀገር! የሆቴል ፓራዲዞ ሀገር! የዕቁባይ ሲላ ሀገር! የምንወደው ደራሲያችን በዓሉ ግርማ በ“ኦሮማይ” መጽሐፉ እንደ ፊልም ግልጥልጥ አድርጎ እየተረከልን ዝንተ-ዓለም እንድንወዳት ያደረገን የቀይ ኮከብ ትዝታ ወመዘክር!
ኤርትራ የፊዮሪ ሀገር! የሳባ ሀገር! የማርቲና ሀገር! የብርኽቲ ሀገር! ፊያሜታ ጊላይን የመሳሰሉ “ሽኮሪናዎች”ን ያበቀለች ውብ የውቦች እመቤት!
—–
ኤርትራን ስንጠራ በቅድሚያ ወደ አዕምሮአችን የምትመጣው አስመራ ናት፡፡ የአስመራ ናፍቆት ይገድላል፡፡ አስመሪና፣ አስመሪቲ፣ አቲ ጽብቕቲ!…
ውይ ስታምር! “ቀሽቲ” እኮ ናት፡፡ ያኔ በልጅ አዕምሮአችን በዘምባባ ጥላዋ ተሸክፋ በፖስትካርድ ስትቀርብልን “የኛ ውቢት” እያልን እንመጻደቅባት ነበር፡፡ እንቆቅልሽ ስንጫወትና መልሱ ጠፍቶን “ሀገር ስጠኝ” ስንባል እርሷን ለመስጠት እንሰስት ነበር፡፡ ጠያቂውም የዋዘ ስላልሆነ “አስመራ” ካላልነው ለጠየቀን ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ አይነግረንም ነበር፡፡ ከማናውቃቸው “ዋሽንግተን” እና ሮማ ይልቅ አስመራ ነበር የምትበልጥብን፡፡ በትምህርት ቤት መዝሙራችንም እንዲህ እንል ነበር፡፡
ኦኬ ኦኬ ኦኬ ስራ
ሰላም ሰላም ወደ አስመራ
አዲስ አስተማሪ ከጃፓን የመጣ
ማስተማሩን ትቶ በቦክስ የሚማታ
አናግረኝና አናግርሃለሁ
በአሜሪካ ሽጉጥ አዳፍንሃለሁ፡፡
አማርኛም አልችል ትግርኛም አልሰማ
ሰተት ብዬ ልግባ አስመራ ከተማ፡፡
ግጥሙ “አንታራም” የሚሉት የህጻናት ጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን አስመራ ከልባችን እንዳትጠፋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዛሬም በልባችን ነግሳለች አስመሪና!
—-
አስመሪና! እቲ ሽኮሪና! ሰሜናይት ጽብቕቲ! በዓሉ ግርማ ላንቺ ክብር የጻፈው ትዝ ይልሻል? እስቲ እናስታውሰው!
አስመሪና አስመራዬ
ካብ ሐንቲ ንግሥቲ ይበልፅ መልክእኪ
አማአድዬ ክርእየኪ ከሎኹ ኽአ
አብ ኢደይ ዘሎ ነገር ይወድቕ፡፡
(አስመራ አስመራዬ)
(ከአንድ ንግሥት ይበልጣል መልክሽ)
(በሩቅ ሲያይሽ በውበቷ ስለተማረከ
በእጄ ያለ ነገር ሳይታወቀኝ ይወድቃል)
——
ጸጸራት፤ ፎርቶ፣ ሐዝሐዝ፣ አርበእተ አስመራ፣ እምባጋሊያኖ፣ ኮምቢሽታቶ፣ አዲ ጓእዳድ፣ ቃኘው፣ ማይተመናይ፣ ሰምበላይ፣ ጎዳይፍ፣ ገጀረት፣ ወዘተ… በጽሑፍ የማውቃቸው የአስመራ ሰፈሮች ናቸው፡፡ አንድ ቀን በሆነልኝና ባየኋቸው እያልኩ አልማሁ፡፡ እነዚህ አስገራሚ የአስመሪና ሰፈሮች ብዙ ባለታሪኮችን አብቅለዋል፡፡ ብዙዎች ገድላቸው እየተደጋገመ ሲነገርላቸው እሰማለሁ፤ አነባለሁ፡፡ ለኛ ቅርብ የነበረ አንድ ውድ ልጅ እየተረሳ በመሆኑ ግን አዝኛለሁ፡፡
አማኑኤል እያሱ ይባላል! አስታወሳችሁት አይደል? አዎን! አማኑኤል በኛ ዕድሜ ዘመን ኢትዮጵያ ዋንጫ መብላት እንደምትችል ያስመሰከረው የታላቁ የ1980 የእግር ኳስ ቡድናችን ቋሚ ተሰላፊ ነበረ፡፡ የማሊያ ቁጥሩ 2 ይመስለኛል፡፡ አማኑኤል የያኔው ቡድናችን ባደረጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች ተሰልፏል፡፡ ቡድኑ ዋንጫውን ሲበላም ከጓደኞቹ ጋር ቤተመንግሥት ድረስ ተጋብዞ ተሸልሟል፡፡ አማኑኤልን ያስገኘው ከዚያ ዘመን ዝነኛ ቡድኖቻችን መካከል አንዱ የነበረው የኤርትራ ጫማ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የኤርትራ አንደኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን በተደጋጋሚ ያሸነፈ ነው፡፡
አማኑኤል እያሱ በኢትዮጵያ ትቅደም አንደኛ ደረጃ ዋንጫም ለኤርትራ ክፍለ ሀገር ምርጥ ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ባልሳሳት የ1981 የኢትዮጵያ ዋንጫን ያሸነፈው እነ አማኑኤል የነበሩበት የኤርትራ ክፍለ ሀገር ቡድን ነው፡፡ የአማኑኤል እያሱን ወሬ ለመጨረሻ ጊዜ ያነበብኩት በ1988 ለወዳጅነት ጨዋታ አዲስ አበባ መምጣቱን በማስመልከት በርካታ የግል ጋዜጦች ቃለ-መጠይቅ ባደረጉለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መረጃው የለኝም፡፡ እስቲ የአስመራ ልጆች ወሬው ካላችሁ ስለአማኑኤል እያሱ አንድ ነገር በሉን፡፡
—–
(በመጽሐፉ ውስጥ “የኤርትራ ህልም” በሚል ርእስ ለቀረበው ረጅም የኢትኖግራፊ ወግ የመነሻ መሠረት የሆነው ይህ አጭር ጽሑፍ ነው። ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ መጽሐፉን ይግዙ)።
Filed in: Amharic