>

ጠያቂ እና ሞጋች ያልሆነ ህዝብ አምባገነንነትን ያነግሳል - ጀርባውንም ለጭቆና ያመቻቻል!! (የሽሀሳብ አበራ)

ጠያቂ እና ሞጋች ያልሆነ ህዝብ አምባገነንነትን ያነግሳል – ጀርባውንም ለጭቆና ያመቻቻል!!
የሽሀሳብ አበራ
ፖለቲካ የራስን እውነት መፍጠር ነው፡፡የትህነግ እውነት የትግራይን ህዝብ አሳምኗል፡፡ በ17 የፖለቲካ ፓርቲ የተቸረቸረው የኦሮሞ ፖለቲካም ወደ  አንድ ጅምላ ድርጅት እየመጣ ነው፡፡ ኦዴፓ እነ ኦነግን ከያዘ የያዘው እውነት የኦሮሞን ህዝብ ያሳምናል፡፡ ኦዴፓ  የተቆራረጡ ፓርቲዎችን እየደመረ ሲሄድ ብሄርተኝነቱ  የበለጠ እየከረረ ይሄዳል፡፡ ኦሮሞነት ብቸኛ የፖለቲካው አልፋ እና ኦሜጋ ይሆናል፡፡ የኦዴፓ የፖለቲካ እውነት ለኦሮሞ ህዝብ እየተስማማ መሄዱ አይቀርም፡፡
 ….
አዴፓ
….
አዴፓ ወደ ትናንቱ እየተመለሰ ነው፡፡ ትናንቱ ናፍቆት የሚሾማቸው  ሰዎች  ከአዳሪነት እና ከአጎብዳጅነት ጋር የቆየ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡የአዴፓ አሿሿም መስፈርቱ በህዝብ መጠላት፣አዳሪነት፣ራስ አልባነት ያደረገ ይመስላል፡፡
 …
በወሲብ፣በዝምድና፣በአበልጅነት፣በመጠጥ ጓዳዊነት የተገነባው የአዴፓ መዋቅር በተለይ ወረዳዎች ላይ በህዝብ እየተናጠ ነው፡፡አዴፓ 1986 እና ዛሬ አንድ እና ያው ሆኖ ቆሟል፡፡
 …
አዴፓ የራሱ እውነት የለውም፡፡እውነትን ከሌሎች ይበደራል፡፡በብድር መምራት አልሰለችህ ብሎት አሁንም የዞን እና የወረዳ መዋቅሩ እክል ገጥሞታል፡፡
የከረመው የአዴፓ እውነት ከትህነግ የተዋሰው ነበር፡፡ የትህነግ እውነት ደግሞ አማራ ደመኛ ጠላቴ ነው፡፡ነፍጠኝነት እና ትምክህተኝነት የጠላቴ ባህሪዎች ስለሆኑ እፋለማለሁ የሚል ነበር፡፡ ብአዴን ይሄን የትህነግ እውነት ሳያላምጥ ውጦ ትምክህተኛ፣ነፍጠኛ፣የድሮ ስራዓት ናፋቂ፣ምናምን እያለ የራሱን ህዝብ ሲያሳቅቅ ኖረ፡፡ ብአዴን ከአማራ ህዝብ ተክለ ስብዕና  በተቃራኒ የኃሊት የሚንደረደር ድርጅት ነበር፡፡
 …
የትህነግ ተረክ በአማራ ህዝብ ተጋድሎ እንደ ጠዋት ጤዛ ሲተን፣አዴፓ  የራሱን እውነት ሳይሰራ ከነ ዶክተር አብይ አስተዳድር ጋር ሳያመነታ ተደመረ፡፡
 ….
ትናንት ከትህነግ እውነት ጋር የተጣባ አመራር ዛሬ ከነዶክተር አብይ እውነት ጋር ለመጣባት እየተሯሯጠ ነው፡፡
 …
አዴፓ የአማራን መሰረታዊ ጥያቄ እፈታለሁ፡፡የማንነት ጥያቄ ሳይቀር አስመልሳለሁ ብሎ ነበር፡፡ማለቱ ደግ ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄን ለማስመለስ ከቀበሌ እስከ ዞን የሰየማቸው ካድሬዎች ወልቃይት የአማራ አይደለም ብለው ሲምሉ እና ሲገዘቱ የኖሩ ናቸው፡፡ ከአማራ ስነ ልቦናዊ ባህሪ የተፋቱ እና ከትምክህት ፣ከነፍጠኝነት የራቁ ናቸው ተብለው የተገመገሙትን መርጦ ስልጣን ሰጥቷል፡፡ስለዚህ አዴፓ የአማራን ህዝብ ጥያቄ ለመሸከም ቀርቶ ለመስማት ሳይከብደው አይቀርም፡፡ አዴፓ የትናንቱ ብአዴን  ከመሆን የሚያድነውን ሃይል አልያዘም፡፡ እንቧለሌ እየተጓዘ ነው፡፡አዴፓ  ከ 1985 ዓም ሳጥኑ አልወጣም፡፡
 …
ወትሮውንም ቢሆን፣ የአማራ ህዝብ ብአዴን መርቶ የተወሰነ አማራ እንዲሆን አደረገው እንጂ በራሱ የመቀየር ሞራል አልነበረውም፡፡ምክንያቱም ብአዴን እውነትን ተውሶ ለመምራት የሚሻ ፣የራሱ ህልውና ያልነበረው ድርጅት ነው፡፡
….
አሁንም የአማራ ህዝብ አዴፓን መምራት አለበት፡፡ መሪው ካልቀደመ ተመሪው መሪ ይሆናል፡፡ የአማራ ተማሪዎች ፣ሀኪሞች፣ወጣቶት ማህበራት ….መጠናከር አለባቸው፡፡
 ….
የሸዋ እና የጎንደር የአማራ ወጣቶች ማህበር እየፈረጠመ ነው፡፡ ወሎ እና ጎጃም ላይ ግን በአማራነት የተየራጀ  የወጣት  ማህበር የለም፡፡ይህ በአስቸኳይ መፈጠር አለበት፡፡ከዚያ ጠቅላላ አንድ ማዕከል ብቻ ያለው የአማራ  ወጣቶች ማህበር ይመሰረታል፡፡
  …
አምባገነንም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መሪን የሚፈጥረው ህዝብ ነው፡፡ ጠያቂ እና ሞጋች ያልሆነ ህዝብ አምባገነንነትን ያነግሳል፡፡ ጀርባውንም ለጭቆና ያመቻቻል፡፡
..
ዲሞክራሲን ለማስፈን በአማራነት ልዮ ልዮ አደረጃጅቶች  ነቅቶ መጠየቅ አማራጭ የለሽ አማራጭ ነው፡፡ አሁንም ነገም፣ ሆነ ከነገ ወዲያ የአማራ ብሄርተኝነት ለአማራ ችግር ሁሉ መፍትሄ ነው፡፡
 …
የአማራ ችግሮች የሚፈቱት የሰላም ሚኒስቴር እየከወነ እንዳለው በእናቶች ልመና፣በሃይማኖት አባቶች ስብከት አይደለም፡፡ በስብከት የሚፈታ ችግር የለም ፡፡መፍትሄው ፖለቲካዊ ብቻ ነው፡፡
ፖለቲካ  መፍትሄ  ለሆነው ችግር  ደግሞ መደራጀት የችግሩን ግማሽ በራሱ ይፈታል፡፡የውስጥ አንድነት ከደረጀ በዙሪያ ያለው ጆፌ ሁሉ ሊጋፋ አይችልም ፡፡
Filed in: Amharic