>

አምባሰል አማራን የመዝረፊያ ምሽግ! (ሚኪ አምሐራ)

አምባሰል አማራን የመዝረፊያ ምሽግ!
ሚኪ አምሐራ
* በረከት ስምኦን እና ታደሰ ሊከሰሱ ነው ሲባል ቀደም ብያ ያጣራኋት ዘገባ ትዝ አለችኝ። ጋሽ መርማሪ ፖሊስ ይህን ዘገባ ከግምት ያስገባዉ ዘንድ እንጠይቃለን።
አምባሰል ንግድ ሥራዎች የእነ በረከት የመዝረፊያ ምሽግ ነዉ፡፡ እንዴት ለሚሉ?
አምባሰል ኪሳራ ዉስጥ በነበረበት ወቀት አንድ ሙሉጌታ ቦጋለ የሚባል ሰዉ ከደሴ ያስመጡና ስራ አስኪያጅ አደረጉ፡፡ ከዚያ አትራፊ ሆነ፡፡ በዓመት ወደ ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ማትረፍ ጀመረ፡፡ የሙሉጌታ አስፈላጊነት እዚህ ላይ አበቃ፡፡ ከዚያ ሙሉጌታን ዳሽን ቢራ መደቡት፡፡ እሱም ከገባ በኋላ ሲያየዉ ከኅሊናዉ ጋር የሚያጣላዉ ሲሆን እምቢ ብሎ ወጣ፡፡ ሙሉጌታ ዳሽንን አልፈልግም ሲል አንድ አሁን ኮምቦልቻ ላይ የተከፈተ የልብስ ስፌት (ጋርመንት) ፋብሪካ አቋቁምልን አሉት፡፡ አቋቋመላቸዉ፡፡ ከተቋቋመ በኋላ ሙሉጌታ ከጥረት ወጣ፡፡
አምባሰል አትራፊ መሆኑ ሲረጋገጥ ምትኩ በየነን ከጥረት ጽሕፈት ቤት አዉጥተዉ ሥራ አስኪያጅ አደረጉት፡፡ ምትኩ በየነ ማለት የዋግኽምራ ዞን አስተዳዳሪ ሆኖ በተከዜ ግድብ ምክንያት ለሚነሱ ሰዎች ከተከፈለዉ ካሳ ጋር በተያያዘ በሙስና ሲጠረጠር በረከትና ታደሰ አቶ አያሌዉ ጎበዜንና እና የጸረ ሙስና ኮሚሽነሩን አሊ ሱሌይማንን አግባብተዉ (ወይ አስፈራርተዉ) እንዳይታሰር አደረጉ፡፡ ሌሎቹ ከእሱ ጋር አብረዉ የወሰኑት ግን ተከሰሱ፡፡ እነሱ ሲከሰሱ እሱ አዲስ አበባ የጥረት ጽሕፈት ቤት ሀላፊ ሆነ፡፡ ቀጥሎ የአምባሰል ንግድ ሥራ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፡፡ ምትኩ በየነ የ”ማዘር” (የብርሃኔ አበራ) የእህት ልጅ ነዉ፡፡ ለበረከት ሚስት (የአሰፉ ፈንቴ) የአክስቷ ልጅ፣ለታደሰ ሚስት (ነጻነት አበራ) የእህቷ ልጅ ነዉ፡፡ “ማዘር” እና የታደሰ ሚስት እህትማማቾች ናቸዉ፡፡
አምባሰል በራሱ በሚያገኘዉ ትርፍ ስላልረካ በጥረት ሥር ላሉ ድርጅቶች በሙሉ ግዥ ፈጻሚ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ይህ የሆነዉ ምትኩ ሥራ አስኪያጅ ከሆነ በኋላ ነዉ፡፡ አምባሰል በመላዉ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለገበሬ ያቀርብ ነበር፡፡ በቅርቡ ነዉ በመንግሥት በኩል እንዲቀርብ  ተደርጓል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ዘይት፣ስኳር ወዘተ ያቀርባል፡፡ እዚህ ላይ የአብቁተ ጉዳይ መዘለል የለበትም፡፡ አብቁተ (አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም) ሲጀመር ሥራ አስኪያጁ ታደሰ ካሳ ነበር፡፡ ከዚያ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነ፡፡ ታደሰ ወደ ጥረት ሥራ አስኪያጅነት ሲዛወር ነዉ ሌላ ሥራ አስኪያጅ (መኮነን-ወይም ሩኒ) የመደቡት፡፡
አብቁተ ከጥረት ከፍተኛ አክሲዮን አለዉ፡፡  ገበሬዉ ገንዘብ ከሌለዉ ከአብቁተ እንዲበደር እየተደረገ ማዳበሪያና ሌሎች እቃዎችን ይገዛል፡፡ ወለዱ ደግሞ 18% ነዉ፡፡ ይሄ አራጣ እንጂ መደበኛ ባንኮች የሚሰጡት ዓይነት አገልግሎት አይደለም፡፡ በማናቸዉም ሁኔታ የወለድ መጠን ከ12 በመቶ መብለጥ አይችልም፡፡ እነ አብቁተ ግን አስራ ስምንት አደረጉት፡፡ የአብቁተ ገቢም ለመንግሥት አይደለም፡፡ በቅርቡ (እነ ታደሰ ከጥረት ሲታገዱ) ነዉ ወደ ልማት ድርጅት እንዲዛወር የተወሰነዉ፡፡  እንግዲህ በአምባሰል በኩል እየሸጡ ትርፍ ያጋብሳሉ፡፡ ገባያዉ ሲያንስ በአብቁተ በኩል ብድር ያመቻቻሉ፡፡ ብድሩን ለአብቁተ መክፈል የማይችል ገበሬ በሬዉ፣የቤት ጣሪያ ቆርቆሮ ሳይቀር ተነቅሎ ይሸጥበታል፡፡ የአብቁተም ትርፍ፣የእነ አምባሰልም ትርፍ አምባሰል ለሚኖር ገበሬ እንዳይመስላችሁ፡፡ ትርፉ እምጥ ይግባ እስምጥ ይፋ አልተደረገም፡፡ እነ በረከት፣ታደሰ፣ወንድወሰን፣ምትኩ፣ብርሃኑ ገብረ ሥላሴና ሌሎች አጋሮቻቸዉ ጋር ካዝና ነዉ የሚገባዉ፡፡
እንግዲህ አምባሰል ቀድሞ በሚያገኘዉ  ትርፍ ስላልረኩ ነዉ እነ በረከት የጥረትንም ግዥዎች ሙሉ በሙሉ በአምባሰል በኩል እንዲገዛ የወሰኑት፡፡ ከዚያም ጉዳቸዉ ቀጠለ፡፡  እንዴት እንደሚገዙ ሦስት ምሳሌ ብቻ እንጥቀስ፡፡
ምሳሌ አንድ የብቅል ገብስ 
ጥረት በስሩ ከሚያስተዳድራቸዉ ድርጅቶች መካከል አንዱ የብቅል ፋብሪካ ነዉ፡፡ ለዚህ ፋብሪካም አምባሰል የብቅል ገብስ ከአገር ዉስም ከዉጭም መግዛቱን ቀጠለ፡፡ አምበሳል አንድ ኩንታል ገብስ በአማካይ ከ1100 እስከ 1300 ብር ይሸምታል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ተመሳሳይ የብቅል ፋብሪካዎች (ለምሳሌ አሰላ የብቅል ፋብሪካ) ግን አንድ ኩንታል ገብስ ከ700 እስከ 800 ብር ነዉ የሚገዙት፡፡ የእነ እንቶኔን ድርሻ ከአንድ ኩንታል ላይ ምን ያህል እንደሆነ አስሉት፡፡
ምሳሌ ሁለት የፕላስቲክ ጥሬ እቃ
ጥረት ለሚያስተዳድረዉ የፕላስቲክ ፋብሪካ ጥሬ እቃዉን አምባሰል ይገዛል፡፡ የሚገዛዉ ደግሞ ከቻይና ነዉ፡፡ አንድ ኪሎ የፕላስቲክ ጥሬ እቃ በኪሎ ከ58 እስከ 64 ብር ይገዛል፡፡ ተመሳሳይ ጥሬ እቃ፣በተመሳሳይ ጊዜ እና በኋላም ከቻይና መጥቶ መርካቶ ላይ የሚሸጠዉ ግን በኪሎ ከ45 እስከ 48 ብር ነዉ፡፡ ቻይና ከፋብሪካዉ ወይም ከጅምላ ነጋዴ አምባሰል በ64 ብር፣የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ከእነ ትርፉ እና ግብሩ ሁሉ አስልተዉ መርካቶ ላይ በጣም ሲወደድ 48 ብር ይሸጣሉ፡፡ ያዉ ሸማቹ አምባሰል ሲሆን 64 ብር ይሆናል፡፡ ከአንድ ኪሎ እነ እንቶኔ የስንት ብር ፈርቅ እንደሚይዙ አስቡት! ኋላ ላይ የፋብሪካዉ ትርፍም ያዉ ከእነሱ አይዘልም፡፡
ምሳሌ ሦስት የቆርኪ ቆርቆሮ
ጥረት የቆርኪ ፋብሪካም አለዉ፡፡ ፋብሪካዉ ለቆርኪ የሚሆን ቆርቆሮ (sheet metal) ከጀርመን ማስመጣት ጀምሮ ነበር፡፡ ኋላ ላይ አምባሰል ገዥ ሲሆን ከቻይና መግዛት ይጀምራል፡፡ ከቻይና የሚገዛዉ ከጀርመን ከሚገዛዉ በዋጋ በጣም ዉድ ነዉ፡፡ የጀርመኑ ርካሽ ነዉ፡፡ የጀርመኑ ለቆርኪ መቶ ፐርሰንት ተስማሚ የሚወድቅ የሌለዉ የነበረ ሲሆን የቻይናዉ ግን ማሽኖቹን ሁሉ አበለሻሻቸዉ፡፡ ተሰባበሩ፡፡ ወዳቂዉም በዛ፡፡ አምባሰል ሲገዛ የተሻለዉን በርካሽ ከመግዛት ይልቅ የማይረባዉን በዉድ መግዛት ይመርጣል፡፡ ከዉዱ እነ በረከት ትርፍ አላቸዉና!
አምባሰል ምሽግ ነዉ፡፡ ምሽግነቱ የአማራ ሕዝብን ለመዝረፍ ነዉ፡፡ አምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጅት አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር ላይ ሕንጻ አለዉ፡፡ በጥረት በኩል የሚደረገዉ ዝርፊያ እዚህ ሕንጻ ዉስጥ በመሆን ነዉ እቅድ የሚወጣዉ፡፡ ለነገሩ ይህ ሕንጻ ለእነ በረከት ስምኦን፣ታደሰ ካሳ፣ወንድወሰን ከበደ፣ምትኩ በየነ፣ብርሃኑ ገብረ ሥላሴ ብቻ አይደለም በዋሻነት (በምሽግነት) የሚያገለግለዉ፡፡ ለልጆችና ሚስታቸዉም ጭምር ነዉ፡፡
የበረከት ሚስት፣አሰፉ ፈንቴ የህትመትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተገናኘ ንግድ የምትሠራዉ እዚሁ አምባሰል ሕንጻ ላይ ሆና ነዉ፡፡ ጥረት በርካታ የህትመት ሥራዎች አሉት፡፡ አሰፉም ታትማለች፡፡ ብአዴን ብዙ የህትመት ሥራ አለዉ፡፡ አሰፉ አምባሰል ሕንጻ ዉስጥ ሆኗ ታትማለች፡፡  ባሏ የጥረት የቦርድ ሊቀመንበርና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴና አዛዥ ናዛዥ የነበረ፣ የአክስቷ ባል የጥረት ስራ አስኪያጅ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፣ የአክስቷ ልጅ ባል አምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጂት ሥራ አስኪያጅ፡፡
ለነገሩ በዚህ ሕንጻ ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ድርጅት አለ፡፡ የታደሰ ካሳ ልጅ እና የወንድ ጓደኛዋ ነዉ፡፡ ልጁ ኢንጂነሪንግ ተምራለች፡፡ በዚህ Consultancy Firm ምን ምን እንደተሠራ ወደፊት ይወጣል፡፡
በማዘር ዙሪያ የተሰባሰቡ የወንበዴ ቡድን ያደፈጠዉ አምባሰል ሕንጻ ላይ ነዉ፡፡ አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር ላይ፡፡ ድርጅቱም ሆነ ህንጻዉ የአማራ ሕዝብ ሲዘረፍበት፣ ሴራ እና ተንኮል ሲመከርበት ኖሯል፡፡ ማንም ንጹሕ ሕሊና ያለዉ ሰዉ እንዳይደርስበት ተደርጎ የተዘጋጀ ድርጅትም ሕንጻ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡
አምባሰል ሌላም ጉዶችን አምቆ ይዞ ኑሯል፡፡ እንመለስበታለን!
Filed in: Amharic