>

የጉር አምባ ጦርነት 165ኛ ዓመት መታሰቢያ  (ልዑል አምደጽዬን ሰርጸ ድንግል)

የጉር አምባ ጦርነት 165ኛ ዓመት መታሰቢያ
 
ልዑል አምደጽዬን ሰርጸ ድንግል
ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ‹‹ዳግማዊ  ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሳቸው በፊት ከግዛት ባላባቶች ጋር ካደረጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች መካከል አንዱ የነበረውን የጉር አምባ ጦርነት ከደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ጋር ያደረጉት ከዛሬ 166 ዓመታት በፊት (ኅዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም) ነበር፡፡
ካሣ ኃይሉ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሳቸው በፊት ከግዛት ባላባቶች ጋር ታላላቅ ጦርነቶችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ ጦርነቶች መካከልም ከደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ጋር በጉር አምባ፣ ከራስ አሊ ጋር በአይሻል እንዲሁም ከደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ጋር ደግሞ በደረስጌ (ቧሂት) ያካሄዷቸው ውጊያዎች ዋናወቹ ናቸው፡፡
ካሣ በልጅነታቸው ወደ ጎጃም ሄደው በደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ቤት ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ደጃዝማች ካሣ ሸፍተው ግዛት ሲያስፋፉ፣ ደጃዝማች ጎሹ ‹‹ድንበር ገፋህ›› ብለው ተጣሉ፡፡ ደጃዝማች ጎሹም ጀግንነት የሚሰማቸውና ብዙ ጦር ያላቸው ስለነበሩ ደጃዝማች ካሳን ለመደምሰስ መዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ደጃዝማች ካሣም ‹‹እባክዎ እኔና እርስዎ አባትና ልጅ ስለሆን መዋጋት አይገባንም፤ ደምቢያን ለቀው ይሂዱልኝ›› ብለው መልዕክት ላኩባቸው፡፡ ኃይለኛው ደጃዝማች ጎሹም ‹‹ምን ሲደረግ?! ወይ ፍንክች!›› አሉ፡፡
የማይቀረው ጦርነትም ኅዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም ጉር አምባ (ጎርጎራ አጠገብ) ላይ ተጀመረ፡፡ ጦርነቱ እንደተጀመረ የደጃዝማች ጎሹ ጦር ጠንከር ብሎ በማጥቃቱ የደጃዝማች ካሣ ጦር መሸሽ ጀመረ፡፡
ደጃዝማች ካሣ ግን ከታማኝ ባለሟሎቻቸው ጋር በመሆን በቆራጥነት መዋጋታቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ መሐል ደጃዝማች ጎሹ ከፊት ቀድመው ‹‹በለው!›› እያሉ እያዋጉ ሳለ በጥይት ተመተው ወደቁ፡፡ መመታታቸውን ያየው ሰራዊታቸውም ገሚሱ እየሸሸ ተበታተነ፤ የቀረውም ወደ ደጃዝማች ካሣ ዞረ፡፡ ደጃዝማች ጎሹም ከቆሰሉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ሞቱ፡፡
ካሣ በልጅነታቸው ወደ ጎጃም ሄደው በደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ቤት ኖረው ስለነበር የደጃዝማች ጎሹን ስርዓተ-ቀብር በክብር አስፈፀሙላቸው፡፡
ከጦርነቱ በፊት ጣፋጭ የተባለው አዝማሪ በደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ሰራዊት መሐል እየተዘዋወረ ስለደጃዝማች ካሣ ‹‹ትንሽነት›› እና ስለ ደጃዝማች ጎሹ ‹‹ትልቅነት››ና ኃያልነት እንዲሁም የሰራዊትብዛት እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበር፡፡
‹‹እስኪ ተመልከቱት ይኸን የኛን እብድ፣
አምስት ጋሞች ይዞ ጉራምባ ሲወርድ፡፡
ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ፣
ወርደህ ጥመድበት በሽምብራው ማሳ፡፡
ወዶ ወዶ፣ በሴቶቹ በነጉንጭት ለምዶ፡፡
ሐሩ ቋዱ ለውዙ ገውዙ አለ ቋራ፣
መንገዱ ቢጠፋ እኔ ልምራ፡፡››
(በግጥሙ ውስጥ የአሁኑ ትውልድ ፈፅሞ የማያውቃቸው ቃላት ስለነበሩ በዘመነኛ አቻ ቃላት ለመተካት ሞክሬያለሁ)
ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ ይኸው አዝማሪ በሰዎች ጠቋሚነት ተይዞ ከደጃዝማች ካሣ ፊት ቀረበ፡፡ ደጃዝማች ካሣም አዝማሪውን ‹‹አንደምን ብለህ ሰደብኸኝ?›› ብለው ጠየቁት፡፡ አዝማሪውም ከጭንቀት የተነሳ ምህረት ያገኘ መስሎት፣
‹‹አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የእግዜር ቁጣ፣
አፍ ወዳጁን ያማል ስራ ሲያጣ፣
ሽመል ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ›› ብሎ በራሱ ላይ ፈረደ፤ አዝማሪውም በሽመል ተደብድቦ ሞተ፡፡
በሌላ በኩል ከጦርነቱ በኋላ የደጃዝማች ካሣ አዝማሪ በሰራዊቱ መሐል እየተንቀሳቀሰ እንዲህ ብሎ ገጠመ፡፡
‹‹ጎሹ አረጀና ልቡ ቢዘናጋ፣
ጉራምባ ወረደ አንበሳን ሊወጋ፡፡
ጎሹ እስከነልጁ ጉራምባ ላይ ወርዶ፣
ያንበሳውን ፊት ቢያይ ወደቀ ተዋርዶ፡፡››
ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ የራስ ኃይሉ ዮሴዴቅ የልጅ ልጅ (የወይዘሮ ድንቅነሽ ኃይሉ ልጅ) እንዲሁም የዳሞቱ ባላባት የደጃዝማች ዘውዴ ልጅ ናቸው፡፡ ልጃቸው ደጃዝማች ብሩ ጎሹ ከአባቱ ጋር ሆኖ ጉር አምባ ላይ ከደጃዝማች ካሣ ጋር እየተዋጋ ሳለ፣ አባቱ ደጃዝማች ጎሹ መመታታቸውን ሲያይ ሸሽቶ ዳሞት ገብቶ ነበር፡፡ በኋላም ተይዞ ድንጋይ ተሸክሞ ደጃዝማች ካሣን ምህረት ጠይቋል፡፡
ምንጮች
፩. አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት (ተክለፃዲቅ መኩሪያ)
፪. የኢትዮጵያ የአምስት ሺ ዓመታት ታሪክ ከኖህ – ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ – መጽሐፍ 1 (ከኖህ – ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) (ፍስሃ ያዜ ካሣ)
[∧ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ተያይዞ የተለጠፈው ምስል በዘመነ መሳፍንት ወቅት ሲካሄዱ የነበሩ ውጊያዎችን ይወክላል የተባለ ምስል ነው]
Filed in: Amharic