>

ጌታቸው አሰፋ ከተንፈራገጠ የሚረግጠው የትግራይ ህዝብን ነው !!! (ካሳ አምበሳው)

ጌታቸው አሰፋ ከተንፈራገጠ የሚረግጠው የትግራይ ህዝብን ነው !!!
ካሳ አምበሳው
የአንድ ሀገር የደህንነት መ/ቤት ከሌሎች መስሪያ ቤቶች የሚለየው በተቋማዊ በአወቃቀሩ (Organizational Structure) ነው፤ በደህነንት መ/ቤት ውስጥ ከላይ ወደታች ግንኙነት(Vertical Communication) እንጂ የጎንኞሽ ተግባብቶሽ (Horizontal communication) የሚባል ነገር የለም፤ ይህ ማለት ከስር ያለ የደህነነት ሰራተኛ የሚያውቀው ከሱ በላይ ያለውን (ሪፖርት የሚያቀብለትን) ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል፤ በስልጣን ወደ ላይ ከፍ እየተባለ በተመጣ ቁጥር መዋቅሩን በተሻለ የማውቅ እድል ይጨምራል፤ በደህንነት መ/ቤት የጽዳት ሰራተኛ ጭምር ተመልምላ ትገባለች እንጂ የስራ ማስታወቂያ ወጥቶ የሚቀጠር አንድም ሰው የለም፤ የደህነንት ሰራተኛ የሚጠራበት ቁጥር እንጂ ስም የለውም፣ አድራሻም እንዲሁ…..፤  ይህ እንግዲህ የደህንነት መ/ቤት ተፈጥሯዊው ባህሪ ነው፤
ከእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ባልሰፈነበት ሀገር የደህንነት ሹም ንጉስ ይሆናል፤ ይህ በተለያዩ ሀገራት የታየ ሀቅ ነው፤ ኤድጋር ሁቨር የአሜሪካንን የፌደራልን የምርመራን ቢሮ ከ50 አመት በላይ በዕርስትነት ይዞ ከፕሬዝዳንት እስከ ጋዜጠኛ ቁም ስቅል ሲያበላ ኑሯል፤  እረ እንደውም ጆኔፍ ኬኔዲን ያስገደለው እሱ ነው ይባላል፤ [በነገራችን ላይ CIA ከመመስረቱ በፊት የደህነንት ስራ ሲሰራ የነበረው FBI ነበር]
ዛሬ KGB ተብሎ የሚጠራውን በቀደመ ስሙ NKVD ተብሎ የሚታወቀውን የሶቭየት ህብረትን የስለላ ድርጅት የመራው ላቫርኒቲ ቤሪያ ከሰማይ በታች ያቆመው ሀይል አልነበረም፤ ጆሴፍ ስታሊን ያቀደውን ብቻ ሳይሆን ያሰበውን ጭምር ሲፈጽምለት የነበረው ቤሪያ የኋላ ኋላ አለቃውን [ስታሊንን] ሀኪም ከልክሎት እንዲሞት ፈረደበት፤ ከደቃቃዋ ጆርጅያ ተነስቶ መዳረሻውን ሴንት ፒተርስበርግ ያደረገውና በመጨረሻም መላውን ሶቭየት ህብረትን በመዳፉ ያስገባው ቤሪያ ከስታሊን በላይ የሚፈራ ሰው ነበር፤
 ወደ ህወሓት ስንመለስ….
ህወሓትን አዲስ አበባ ያደረሰው የደህንነት አቅሙ እንጂ ወታደራዊ ብቃቱ እዳልሆነ መዘንጋት የለበትም፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ብዛቱን፣ እቅዱንና አሰፋፈሩን ብቻ ሳይሆን የበላው እና የጠጣው ጭምር በሰዓታት ይደርሳት ነበር፤ ወታደራዊ ተቋማትን አልፈው ሊቀመንበር መንግስቱ ሀ/ማሪያም ቢሮ ገብተው እንደነበር ለቀመንበሩ ጭምር ተናግረዋል፤ “የራሴ ጸሐፊ የወያኔ ሰላይ ነበረች” ብለዋል፤ “War is 90% information” እንዲል ናፖሊዮ ቦናፓርት ወያኔን ሚኒሊክ ቤተመንግስት ያደረሳት ጦርነት ሳይሆን ስለላና መረጃ ነው፤ ይህ ቡድን ጫካ እያለ ይህን ያህል የደህንነት እና የመረጃ መረብ መዘርጋት ከቻለ መንግስታዊ ካባ ሲደርብ የሚቆጣጥረው የደህንነትና የመረጃ መረብ ምን ያህል ውስብስብ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፤
ዛሬም ቢሆን የሀገሪቱ የደህነንት መዋቅር ጌታቸው አሰፋ እጅ ነው፤ ጄነራል አደም መሐመድ የተረከበው የደህንነት መ/ቤቱን ህንጻ እንጂ መዋቅሩን አይደለም፤ ለይስሙላ እንኳን የሰራ ርክክብ ሲደረግ አላየንም፤  ጌታቸው መቀሌ የገባው አደም ከመሾሙ አስቀድሞ ነው፤
በአጭሩ………
ጌታቸው አሰፋ ዛሬም ቢሆን ሀገሪቷ ውስጥ ሽብር የመፍጠር አቅም አለው፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አድርጎ የሾመው ክልሉ ሰው አጥቶ ወይም ክልሉ የተለየ የጸጥታ ስጋት ስላለበት ሳይሆን ለጌታቸው እኩይ ተግባር ምቹ ሁኔታ ለመፍጥር ነው፤ የሆነው ሆኖ ጌታቸው ኔትወርኩን ማንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው፤ የጊዜ ጉዳይ ነው፤ በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ! የጌታቸው አቅም እነ አሉላ ሰለሞንና ዳንኤል ብርሀነ እንደሚያስቡን ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚችል አይደለም፤ ለዛ እጅግ በጣም ረፍዷል፤ ጌታቸው ከተንፈራገጠ የሚጎዳ ህዝብ አለ፤ የትግራይ ህዝብ! የጌታቸው ፍርግጫ የሌላው ህዝብ ልብስ ሊያቆሽሽ ይችል ይሆናል የትግሬን ደረት ግን ሳያፈልስ አይመለስም፤ ያንን ደግ ህዝብ ከዚህ ይሰውረው!
Filed in: Amharic