>
5:13 pm - Saturday April 20, 7765

ኢትዮጵያ - ቦይንግ!!! (ደምሰው ማሙዬ)

ኢትዮጵያ – ቦይንግ!!!
ደምሰው ማሙዬ
 
ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ሁላችንም መተዋወቅ የለብንም፡፡ ለአንድ ዓላማ እስከሠራን ድረስ የትም ሆነን፣ ማንም ሆነን በግንባታው ላይ መሳተፍ እንችላለን፡፡ አንድ ዓይነት መሆንም የለብንም፡፡ የተለያየ እምነት፣ ዘርና ፖለቲካ ይዘን፣ በተለያየ ዘመንና ቦታ ሆነን መገንባት እንችላለን፡፡ ብቻ ለአንድ ዓላማ እንሰለፍ፡፡ ለማፍረስ ያይደለ፣ ለመገንባት!
ቦይንግ 747-8፣ ለመገጣጠም ብቻ 4 ወር የፈጀ አውሮፕላን ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚገጣጠሙ ክፍሎች አሉት፡፡ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ሆነው ከጥቃቅን እስከ ግዙፍ፣ ከመካኒካል እስከ ኤሌክትሪካል የሚያመርቱ ከ30 ሺ በላይ ሠራተኞች ይሳተፉበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚተዋወቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡
ብዙዎቹ የአንዱን መኖር ሌላው አያውቀውም፡፡በእድሜ፣ በዜግነት፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በመልክና በዘር ይለያያሉ፡፡ የሚከፈላቸው ክፍያ ይለያያል፡፡ የሚያመርቱትም የአውሮፕላኑን አንድ ክፍል እንጂ ጠቅላላውን አውሮፕላን አይደለም፡፡ ሁሉንም አንድ የሚያደርጓቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ለአንድ ኩባንያ መሆኑና የሚሠሩበት ዓላማ አንድ መሆኑ፡፡ እነዚህን ሁሉ ስድስት ሚሊዮን ተገጣጣሚ አካላት የሚያመርቱት ባለሞያዎች ቦይንግ ለሚባል ኩባንያ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ንኡስ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩት እንኳን ለዚሁ ኩባንያ እንደሚሠሩ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ የሁሉም ዓላማ አውሮፕላን መሥራት መሆኑ ነው፡፡ በዓይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነቺው ብሎን ከሚሠራ ጀምሮ ትልልቁን አካል እስከሚያመርተው ድረስ ዓላማቸው ብሎን፣ ክንፍ፣ በር፣ ሞተር፣ ጎማ፣ ወንበር፣ መሥራት አይደለም፡፡ አውሮፕላን መሥራት ነው፡፡ ያ በሰማይ ሲበር የሚያዩት አውሮፕላን እንደየዐቅማቸው ተሳትፈው እነርሱ የሠሩት አንድ አውሮፕላን ነው፡፡
ምናልባትም የመጨረሻውን ቅርጽ ሲይዝ ብዙዎቹ ላይገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚፈጸመው ሲያትል ፓይነ በተባለው ሜዳ በሚገኘው የቦይንግ ኤቨረት ፋብሪካ ነው፡፡ 13.4 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር የሚጠጋው ይህ መገጣጠሚያ በፕላኔታችን ላይ ለአውሮፕላን ከተሠሩ መገጣጠሚያዎች ሁሉ መሰል የሌለው ነው፡፡ እዚህ ቦታ አውሮፕላኑ ተገጣጥሞ የመጨረሻውን ቅርጽ ሲይዝ ብዙዎቹ ሠራተኞቹ የሉም፡፡  በአንድ ነገር ግን ርግጠኞች ናቸው፡፡ እነርሱ ያመረቱት አካል ተገጣጥሞ አስደናቂውን የቦይንግ አውሮፕላን እንደሚፈጥረው፡፡
ሀገር የምትገነባው እንደዚህ ነው፡፡ በየዘመናቱ፣ በተለያየ ድርሻ፣ ሞያና አስተዋጽዖ የሚችሉትን በሚያበረክቱ ዜጎች፡፡ በአሜሪካም ይሁኑ በጃፓን፣ በአውስትራልያም ይሁኑ በካናዳ፣ በአውሮፓም ይሁኑ በእስያ፣ በአፍሪካም ይሁኑ በዐረቡ ዓለም ለአንዲት ኢትዮጵያ በሚሠሩ ዜጎች፡፡ የሚሠሩት ሥራ እጅግ አነስተኛ መስሎ ይታይ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ገዝፎ የሚታይ ጉልሕ ይመስላል፡፡ ግን ኢትዮጵያ ለምትባል አንዲት ዓላማ፣ ኢትዮጵያዊነት በሚባል አንድ ኩባንያ ውስጥ ሆነው የሚያመርቱ ዜጎች ናቸው ኢትዮጵያን የሚገነቧት፡፡ ምናልባትም አንዳንዶች የእነርሱ አስተዋጽዖ የመጨረሻው ሥዕል ምን እንደሆነ አላዩም፣ ወደፊት አያዩ ይሆናል፡፡ ግን በአንድ ነገር ርግጠኞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም አስተዋጽዖ ትገነባለች፡፡
የእያንዳንዱ ቅንጣት በጥራትና በብቃት መመረት ለአውሮፕላኑ ጥራትና ብቃት ወሳኝ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በተሠማራንበት ቦታ የምንሠራው፣ የምናስበው፣ የምንጽፈው፣ የምንወስነው፣ የምናካሂደው ነገር ጥራትና ብቃት እንዲኖረው ከተደረገ ሀገራችን የጠራችና የበቃች ትሆናለች፡፡ እያንዳንዱ የቦይንግ አውሮፕላን ቅንጣቶችን አምራች ባለሞያ የሚሠራው ነገር ከሌሎች ጋር ተጋጥሞ፣ ተስማምቶና ተዋድዶ አንድ አውሮፕላን ካልፈጠረ ሥራው ዋጋ የለውም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየቦታውና በየዘመናቱ የሚሠራው ሥራ ከሌላው ጋር ተጋጥሞ፣ ተስማምቶና ተዋድዶ አንዲት ኢትዮጵያን ካልፈጠረ ትርፉ ድካም ነው፡፡
ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ሁላችንም መተዋወቅ የለብንም፡፡ ለአንድ ዓላማ እስከሠራን ድረስ የትም ሆነን፣ ማንም ሆነን በግንባታው ላይ መሳተፍ እንችላለን፡፡ አንድ ዓይነት መሆንም የለብንም፡፡ የተለያየ እምነት፣ ዘርና ፖለቲካ ይዘን፣ በተለያየዘመንና ቦታ ሆነን መገንባት እንችላለን፡፡ ብቻ ለአንድ ዓላማ እንሰለፍ፡፡ ለማፍረስ ያይደለ፣ ለመገንባት፡፡
ማንም ብቻውን አውሮፕላኑን አያመርተውም፡፡ እያንዳንዱ ባለሞያ ለአንድ ዓላማ ተሠማርቶ በሚቻለውና በተሰጠው መጠን ይገነባል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት፡፡ ማንም ብቻውን አይገነባትም፡፡ ሁላችንም በተሰጠን መጠንና በቻልነው ያህል አሻራችንን እያሳረፍን እንገነባታለን፡፡ ኑ፣ በጋራ አገር እንገንባ፣ አኮብኩባ ስትበርም እንያት፡፡
Filed in: Amharic