>

'እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ ...!!!' (ውብሸት ታዬ)

‘እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ …!!!’
ውብሸት ታዬ
   በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩት ሜ/ጄ/ል ክንፈ ዳኘው እና ወዳጆቻቸው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ‘የጨዋ ልጅ’ ስለሆኑ ለምን እጃቸው ላይ ካቴና ገባ፤ ከተደረገስ ለምን የወርቅ አልሆነም? ዓይነት የሞልቃቃ ሹማምንትና ገና በትናንቱ ሰመመን ውስጥ ሆነው የሚዘባርቁ አንዳንድ ልጆች አየሁ!
 
 
‘የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ!’ አሉ:-
በዚህ ምስል ላይ ከግራ የመጀመሪያው አዛውንት በዝዋይ ግዞት ጨለማ ቤት ለ11 ዓመታት ማቀው የወጡ የሕዝብ ልጅ ናቸው። ኮሎኔል አበበ አስራት ይባላሉ።
   በመከላከያ ውስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የነበሩ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን መከራ በዝምታ አልፈው ስለማያውቁ በ1997 ዓ.ም ከቅንጅቱ አቶ በድሩ አደም ጋር ስለሕዝቡ ነፃነት መክረዋል ተብለው ከላይ በተጠቀሱት ጄ/ል በተቀናበረ ክስ 17 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ናቸው። ሕዝብ ነፃ አውጥቷቸዋል ። በግዞት ቤቱ ሕይወታቸው ያለፈ አባሪ ግን አላቸው።
   በምስሉ ከቀኝ ወደግራ ሁለተኛው ደግሞ በ1990 ዓ.ም አገር ተወረረች ሲባል በደሙ ድንበሯን ሊያስከብር ኑሮውን በትኖ ወደሰሜን ያቀና የያኔው ወጣት፤ ከ18 ዓመታት የግፍ እስር በኋላ ጎልምሶ በሕዝብ ትግል የወጣው ዳውድ አባተማም ነው። ፍርዱ ሞት ነበር። ሰበቡ በጦሩ ውስጥ ለአንድ ቡድን ያደላ የተንሸዋረረ  የብሔር ወገንተኝነት አለ የሚል ነበር። በውጊያ ወቅት እንደዚያ ያልካቸውን አዛዦች ሕይወት አጥፍተሃል የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ በአራት መስመር ውሳኔ የሞት ፍርድ ተሸክሞ ለ18 ዓመታት በዝዋይ ግዞት ጨለማ ቤት ቆይቷል። ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ተፈጽሞበታል።
   ከቀኝ የመጀመርያው ደግሞ ካፕቴን በሃይሉ ገብሬ ነው። የ1997ቱን የሰኔ 1 ቀን የንጹሃን ጭፍጨፋ በመቃወም የሚያበራትን ተዋጊ ሄሊኮፕተር ከረ/ካፕቴን አብዮት ማንጉዳይ ጋር ይዘው ወደጅቡቲ በመሄዳቸውና ተላልፈው በመስጠታቸው ለዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተዳረገ የሕዝብ ልጅ ነው። ሁለት ዓመት በደብረዘይት አየር ሃይል ውስጥ እጅና እግሩ በሰንሰለት ታስሮ የደረሰበትን መከራ መግለጽ ይከብዳል ። በኋላ ለ12 ዓመታት በዝዋይ ግዞት ጨለማ ቤት ቆይቷል። ፍትሕ ለሕዝብ ባለ ለ14 ዓመታት ፍትሕ ነፍገውታል። ወገኖቼ ግፉ ተዘርዝሮ አያልቅም ።
ይህ ማለት በፍጹም እንዳደረጉ ይደረግባቸው ማለት አይደለም። ፍትሕ ይበየን ሲባል ‘እሽ አትበሉን የሹም ዶሮ ነን’ የሚሉትን አጉል መሞላቀቅ ይተው ነው። እኛንም በቃ ብሎን ሰላሙን፣ ፍቅሩንና ዴሞክራሲውን ያድለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic