>

የህወሓት ቀረርቶ፡ አትዮጵያን ከመበታተን ትግራይን ወደ መገንጠል! (ስዩም ተሾመ)

ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ ዶ/ር ደብረፂዮን “ተከባብረን እንኖራለን ወይም ኢትዮጵያ ትበታተናለች” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ይህን የተናገረው “ተከባብረን መኖር ካልቻልን ትግራይ ከኢትዮጵያ ትገነጠላለች” የሚለውን ለመጠቆም ፈልጎ እንደሆነ ሲገልፁ ነበር። ነገር ግን ዶ/ር ደብረፂዮን ያለው “ኢትዮጵያ ትበታተናለች” እንጂ “ትግራይ ትገነጠላለች” አይደለም።

እንደ ዶ/ር ደብረፂዮን አገላለፅ “ተከባብሮ መኖር” ማለት እንደ አቶ አባይ ፀሓዬ እና ሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው ያሉ የሀገር ዘራፊዎች፣ እንዲሁም ባለፉት አመታት በዜጎች ላይ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሽብር ጥቃት በበላይነት ሲያስተባብሩ የነበሩ እንደ አቶ ጌታቸው አሰፋ ያሉ የህወሓት አመራሮች እና አባላት ከህግ ተጠያቂነት ውጪ መቀሌ ውስጥ ተሸሽገው እንዲኖሩ መፍቀድ ነው። ይህ ካልሆነ ግን እንደ እሱ አገላለፅ “ኢትዮጵያ ትበታተናለች”።

ኢትዮጵያ የምትበታተነው ትግራይ ስለምትገነጠል አይደለም። ዶ/ር ደብረፂዮን ይህን ማለት ቢፈልግ ኖሮ “ተከባብረን እንኖራለን ወይም ትግራይ ትገነጠላለች” በማለት በግልፅ መናገር ይችል ነበር። ከዚያ ይልቅ ዶ/ር ደብረፂዮን የተናገረው ሀገር ሲዘርፉ እና በዜጎች ላይ ግፍና በደል ሲፈፅሙ የነበሩ የህወሓት ሰዎች በህግ የሚጠየቁ ከሆነ “ኢትዮጵያ ትበታተናለች” ነው። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን የሚበታትኗት ላለፉት አመታት በሀገሪቱ ጦር ሰራዊት፣ የፖሊስ፣ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ውስጥ የነበራቸውን የበላይነት እና ልምድ በመጠቀም በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ማስከበር እንዲሳነው በማድረግ በተለያየ አቅጠጫ የእርስ-በእርስ ግጭት እና ጦርነት በመቀስቀስ ሀገሪቷ አንድነቷና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ተስኗት እንድትበታተን ማድረግ ነው።

ባለፉት ሦስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማና በቡራዩ የተነሳው ሁከትና ብጥብጥ፣ በቤተ-መንግስት ዙሪያ የተፈጠረው ግርግር፣… በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ የብሔር ግጭትና ጥቃት፣ በምዕራብ ወለጋ እና በቦረና አከባቢ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች፣ በሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች፣ ሰሞኑን ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው ሁከትና ግጭት በሌላ ምክንያት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚደረገው ያላሳለሰ ጥረት ውጤት ነው።

ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያሉት የህወሓት ሰዎች የእስር ማዘዣ ሲወጣባቸው እንደ ዶ/ር ደብረፂዮን አገላለፅ “መከባበር ቀርቷል” ማለት ነው። ስለዚህ ጨዋታው “ኢትዮጵያ ትበታተናለች” ከሚለው “ትግራይ ትገነጠላለች” ወደሚለው ተቀየረ። ከዚህ በኋላ የህወሓት ቀረርቶና ማስፈራሪያ “ተከባብረን እንኖራለን ወይም ትግራይ ትገነጠላለች” በሚለው ላይ ይሆናል። በተለይ ባለፉት ሦስት አመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ከተከታተልኩ በኋላ አንድ የተረዳሁት ነገር ቢኖር “ኢትዮጵያ ትበታተናለች” የሚለው ከንቱ ዘበት መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ የምትበታተን ቢሆን ኖሮ ከመቼውም ግዜ በላይ ህወሓት በበላይነት በነገሰባቸው ያለፉት 27 አመታት ውስጥ ብትንትኗ በወጣ ነበር። እንደ መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ ጌታቸው አሰፋ እና አባይ ፀሓዬ ያሉ ሰዎች ያላፈረሷት ሀገር መቼም ቢሆን አትፈርስም። ትላንት ያልገነጠሏት ትግራይ መቼም ቢሆን አትገነጠልም። ምክንያቱም ሀገር ለመበታተንና ለመገነጣጠል ከህወሓቶች በላይ ተግቶ የሰራ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

Filed in: Amharic