>

ለምን ሰው ጌታቸው አሰፋ እና መቀሌ ላይ ያተኩራል?  (ስዩም ተሾመ)

ለምን ሰው ጌታቸው አሰፋ እና መቀሌ ላይ ያተኩራል? 
ስዩም ተሾመ
አሁን ላይ የብዙዎችን ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የአቶ ጌታቸው አሰፋ መታሰር እና መቀሌ ላይ እየሆነ ያለው ነገር ነው። ለምን ለሚለው ጥያቄ የሚከተሉትን ሶስት ምክንያቶች መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፡-
1ኛ) የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ኃላፊ የነበረው አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ስር ውሏል። ነገር ግን በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀም ትዕዛዝና መመሪያ ሲሰጥ የነበረው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ መቀሌ ውስጥ #ተደብቋል።
2ኛ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት የፀረ-ሽብር መምሪያ ኃላፊ የነበረው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥሮ ታስሯል። ነገር ግን የሰኔ 16ቱን የቦንብ ፍንዳታ በበላይነት በማስተባበርና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ወንጀል የተጠረጠረው አቶ #ጌታቸው_አሰፋ መቀሌ ላይ ተደብቋል።
3ኛ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞኖች ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ የደህንነት ኃላፊዎች በአከባቢው ህዝብ ውስጥ ለወንጀለኞች መደበቂና መሸሸጊያ የሚሆን ጥጋት ቦታ ስለሌለ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ነገር ግን በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት የአንድ መምሪያ ሃላፊ የነበረውና የሀረሪ ተወላጅ የሆነው ዶ/ር #ሀሺም_ቶፊቅ መሃመድ የእስር ማዘዣ ሲወጣበት ከአዲስ አበባ ተደብቆ የሸሸው ወደ ሀረር ሳይሆን መቀሌ ነው።
በዚህ መሰረት የአብዛኛው ሰው ትኩረት አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የሆነው ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ ለተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድራጊና ፈጣሪ ስለነበረ ነው፡፡ የአብዛኛው ሰው ትኩረት መቀሌ ላይ የሆነው ደግሞ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጨምሮ በእሱ ትዕዛዝና መመሪያ መሰረት በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎች ወደ መቀሌ ሸሽተው የሚደበቁ በመሆናቸው ነው። ስለዚህ መቀሌና የክልሉ መስተዳደር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ሁሉንም ተጠርጣሪ ወንጀለኞች አሳልፈው እስካልሰጡ ድረስ ዓይናቸን ከእነሱ ላይ አይነቀልም፡፡
Filed in: Amharic