>
5:13 pm - Sunday April 19, 2409

የትግራይ ክልል መስተዳድር ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጫማ እንለካካ እያለ ይሆን? (ቬሮኒካ መላኩ)

የትግራይ ክልል መስተዳድር ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጫማ እንለካካ እያለ ይሆን?
ቬሮኒካ መላኩ
በየትኛውም አለም ህግ  ለነፃነት ትልቅ ዋልታና ማገር ነው።  እንደ ግሪካዊ ፈላስፋ አርስቶትል አስተምህሮ የአንድ ልኧላዊ አገርና ህዝብ እንደሰንሰለት የሚያያይዘው ተቀዳሚ እሴት ህግና ፍትህ ነው። የመንግስት የመጀመሪያ ስራ ህግን ማስከበርና ህግን ማስከበር ነው። ያለ ህግና ፍትህ ማንኛውም ማህበረሰብ በሰላምና በፀጋ ሊኖር አይችልም።
ወደድንም ጠላንም  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ  ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ ከምእራብ ጫፍ እስከምስራቅ ጫፍ ለሚኖረው መቶ ሚሊዮን ህዝብና  ለአስተዳደራዊ ግዛቱ ይሆን ዘንድ ህገመንግስቱና  አለም ሁሉ እውቅና የሰጠው  መሪ ነው።
የትግራይ ክልል የአገሪቱን ህጋዊ መሪ በቦምብ ጥቃት ለመግደል  የሞከረንና የፍርድ ቤት መጥሪያ የተቆረጠለትን  ወንጀለኛ አቅፎ መያዙ ሳያንስ በክልሉ ቁንጮ ከሆኑት ስልጣኖች አንዱን ሰጥቶታል።  ጌታቸው አሰፋ እስካሁንም ድረስ የትግራይ ክልል የፀጥታ ሃላፊነቱ ቦታ ላይ እንደተቀመጠ ነው። ክልሉ ይሄን ወንጀለኛ ከሁለት ወር በፊት መሾሙን እንጅ ከተሾመበት ቦታ ማንሳቱን አላሳወቀም።ይሄ ለሰሚውም በጣም የሚያስገርም ነው። የአገሪቱን መሪ ለመግደል በመሞከር የተከሰሰን ግለሰብ  ሹመት ተሰጥቶት  በነፃ ማንቀሳቀሱ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጫማ እንለካካ እያለ ይሆንበነገራችን ላይ በዚህ ደረጃ በወንጀል የሚፈለግን የፍርድ ቤት ማዘዣ የወጣበትን ሰው መንግስታዊ ሹመት እየሰጡ ለወንጀለኛ “ህጋዊ” ምሽግ በመገንባት በአለም ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች።
ያለነው ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የሚባል አገር እንጅ በደቡብ አሜሪካ ኮኬይን ማፊያ የሚመራ Banana Republic ውስጥ አይደለም።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጌታቸው አሰፋን ከወሸቀበት ቀሚስ ውስጥ አውጥቶ ማስረከብ አለበት። መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህይወት ለማጥፋት የሞከረን ወንጀለኛ በአስቸኳይ ካልያዘ በየቦታው በተራ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ  ወንጀሎችን  ይቆጣጠራል ተብሎ አይጠበቅም። መንግስት አሁንም የትግራይ ክልል እየፈፀመው ያለው አስከፊ ህገመንግስታዊና ህጋዊ ጥሰትን በአስቸኳይ ተገቢውን ቅጣት በማሳረፍ እርምት ካልወሰደ ለሌሎች የፌደሬሽኑ ክልሎች የሚሰጠው ፕሪሲደንት እጅግ አደገኛ መሆኑ መታወቅ አለበት።
Filed in: Amharic