>

ወያኔ የዋለልን ውለታ ምንድን ነው? ለመሆኑ ውለታ ውለታ የሚሉንስ ምኑን ይሆን?  (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ወያኔ የዋለልን ውለታ ምንድን ነው? ለመሆኑ ውለታ ውለታ የሚሉንስ ምኑን ይሆን? 
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እነዚህ ሰዎች ግን እብድ ናቸው ወይስ ምን የሚሉት ዓይነ ደረቅነት ነው??? ደርግን አስወግደው እነሱ መተካታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ውለታ ነው ወይስ በደል???
ደርግ ከዝርፊያ የጸዳ ነበር እነሱ ግን የሀገርን ካዝና አራቆቱ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ተከፍሎ ከማያልቅ የዕዳ ማጥ ውስጥ በማስመጥ አሁን በአካል የሌሉትንና ገና ወደፊት የሚመጡትን የሚቀጥሉትን ትውልዶችን ሳይቀር አራቁተው በመዝረፍና አገሪቱን በአጽሟ በማስቀረት በዓለም ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የሌብነት፣ የዝርፊያና የውንብድና ዓይነት ለዓለማችን አሳዩ፡፡
ደርግም በዜጎች ላይ ሰቆቃ (ቶርቸር) በመፈጸም የሚታወቅ ቢሆንም ቶርቸር የሚፈጽመው ግን ሰለባዎቹን ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ነበር፡፡ ደርግ በታሪኩ የፍርድ ቤትን ነጻነት ተጋፍቶ አያውቅም ነበር፡፡ የሚፈጽማቸው የቶርቸር (የሰቆቃ) ዓይነቶችም ከወያኔ የሰቆቃ ዓይነቶች ያነሱ ነበሩ፡፡ በደርግ የቶርቸር ዘመን ወንድ ልጅ አልተደፈረም ወይም ግብረሰዶም አልተፈጸመበትም ነበር፡፡
በወያኔ ዘመን ግን ፍርድ ቤት ወይም የፍትሕ አካል የሚባል ጠፍቶ ፍርድ ቤቱ የወያኔ አንባገነናዊ ፈቃድ ብቻ የሚፈጸምበት፣ የወያኔ ኢፍትሐዊ ጥቅም ብቻ የሚጠበቅበት እጅግ ነውረኛና አሳፋሪ ተራ የዱለታ መድረክ ሆነ፡፡ እሱም አልበቃው “ከምን ጋር የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለት!” እንዲሉ በበሬ ወለደ ውሸቱ፣ ዓይን በሚያወና ክህደቱ፣ ምን ይሉኝን በማያውቀው ቅጥፈቱ፣ ነውረኛነት በተሞላ ዕብለቱ ለሕዝቡ መጥፎ አርአያ በመሆንና ሥነ ሥርዓት፣ ሥነ ምግባር፣ መታመን፣ መታፈር፣ ይሉኝታ፣ ለክብር ዋጋ መስጠት ወዘተረፈ. ከማኅበረሰቡ እንዲጠፋ በርትቶ በመሥራት እነኝህ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ወድመው ማኅበረሰባችንን ጉድ አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ አጭበርባሪነት፣ አወናባጅነት፣ አታላይነት፣ ክህደት፣ ዕብለት የብልሹ ሥነምግባር መገለኛነታቸው ቀርቶ ብልጠት፣ ብልህነት፣ አዋቂነት፣ አስደናቂ ችሎታ ተደርጎ የተቆጠረበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ወያኔ ከደርግ በተለየው የሰቆቃ ዓይነቱ ማለትም ወንዶችን የመድፈር ጥቃትን ዋነኛ ቅስም የመሥበሪያ ዘዴው አድርጎ ተጠቅሟል፡፡
ደርግ የትኛውንም ዘር በጠላትነት አልፈረጀም የዘር ማጥፋት ወንጀልም አልፈጸመም፡፡ ደርግ በጠላትነት አይቶ ያጠቃው ብሄር ብሄረሰብ የሚባል ነገርም የለም።
እንደውም ወያኔ ትግሮችን ከጎኑ ለማሰለፍ እንዲረዳው ደርግን የትግሬ ጠላት አድርጎ ይለፍፍ እንጅ ደርግ ትግሬን በማባበል የመያዝ ስትራቴጂ (ስልት) ይከተል ስለነበረ ትግሬ በተለየ የተጠቃበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ለማባበል ብሎ በሚያደርጋቸው ነገሮች ትግሮች በተለየ ተጠቃሚ የሆኑበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡
ወያኔ ግን በማኒፌስቶ (በዓላማ አቅድ) አማራን “ጨቋኝ አማራ የማጠፋት ጠላቴ ናት!” ብሎ በመነሣት ከበረሃ ጀምሮ እስከዚህች ሰዓት ድረስ በበርካታ ሚሊዮኖች (አእላፋት) የሚቆጠር አማራን በግልጽና በስውር በሚፈጽመው አረመኔያዊ ጥቃቶች አጥፍቷል፡፡
ደርግ የፈጸማቸው ግፎች የሀገርን ዓይን ያጠፉ ቢሆንም የሀገር ፍቅር ስሜት ግን ነበረው፡፡ የሀገሪቱን ህልውናና አንድነት ለድርድር አያቀርብም፡፡ ወያኔ ግን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” በሚለው አስተሳሰቡ የራሱን ጥቅም ከሀገር ጥቅም አስበልጦ ዓይቶ በሀገሪቱ ህልውና ላይ በመቆመር ሕገመንግሥት በሚለው የውንብድና ሰነዱ ላይ ሳይቀር ኢትዮጵያን በታኝ አንቀጽ በማስቀመጥና በዚያ በማስፈራራት የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ሲጠቀምበት ኖረ፡፡ እሱ የማይገዛት ኢትዮጵያ ከመጣችም እንድትፈርስ ለማድረግ አሴረ፡፡
ኧረ ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል ወገኖቸ??? እና ታዲያ ደርግ ከወያኔ ሽህ ጊዜ የተሻለ በሆነበት ሁኔታ የወያኔ “ምንስ ቢሆን ባለውለታቹህ አይደለሁም ወይ???” የሚለው ፈጽሞ የማይጠበቅ ዜማ ከየት መጣ??? ነው ወይስ ደርግ እንደ ጥሊያን ባሕር ተሻግሮ የመጣ የባዕድ ወራሪ ኃይል ነው??? አልገባኝ አለኮ በእውነት!!! የምሬን ነው እባካቹህ የገባቹህ ካላቹህ የወያኔን ውለታ ብታስረዱኝ???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic