>

የቃሊቲ ክለብ በዝውውር ተጠምዷል!!! (በረከት ያረጋል)

የቃሊቲ ክለብ በዝውውር ተጠምዷል!!!
በረከት ያረጋል
የኘሮፌሽናሉ ገዳይ አጥቂ ጌታቸው ለቃሊቲ ክለብ መፈረም እውን ከሆነ ከቀድሞ የብሄራዊ ደህንነትን አጋሩ ያሬድ ዘሪሁን ጋር በመጣመር የቃሊቲን የአጥቂ መስመር አስፈሪ እንደሚያደርጉት ይታመናል!!
ታምራት ላይኔና ገብረዋህድን የለቀቀው ቃሊቲ የእግርኳስ ክለብ ለ2011 የውድድር አመት ይረዳው ዘንድ በዝውውር መስኮቱ ሳምንቱን ተጨዋቾች በማስፈረም ተጠምዷል፡፡ የሜቴኩ የክንፍ መስመር ተጨዋች ክንፈ ዳኘውን ሠኞለተ በማስፈረም የጀመረው ክለቡ ከቴሌም የክንፈ ዳኘው ወንድም ኢሳያስ ዳኘውን በማስፈረም የግል ንብረቱ አድርጓል፡፡ ክንፈና ወንድሙ ለምን ያህል ጊዜ ለቃሊቲ እንደፈረሙ ባይታወቅም በክለቡ ጫማቸውን ይሰቅላሉ ተብሎ ነው ሚጠበቀው፡፡
የቃሊቲ ሌላ ፈራሚ ተጨዋች የብሄራዊ ደህንነቱ ያሬድ ዘሪሁን ነው፡፡ ረቡዕ ለክለቡ ከመፈረሙ በፊት በዱከም አንድ ሆቴል በመቀመጥ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ወጣቱ ያሬድ ለቃሊቲ ክለብ እንዳይፈርም የንሰሃ አባቱ ያረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ ከያሬድ ጋር በብሔራዊ ደህንነት ክለብ አብሮ ያሳለፈው የስቃይና ማኮላሸት ስፔሻሊስቱ ጌታቸው አሰፋን ለማስፈረምም ቃሊቲ ጥረቱን አጠናክሯል፡፡ ሡዳን እንዳለ የሚገመተው የኘሮፌሽናሉ ገዳይ አጥቂ ጌታቸው ለቃሊቲ ክለብ መፈረም እውን ከሆነ ከቀድሞ የብሄራዊ ደህንነትን አጋሩ ያሬድ ዘሪሁን ጋር በመጣመር የቃሊቲን የአጥቂ መስመር አስፈሪ እንደሚያደርጉት ይታመናል፡፡
ክለቡን ቀደም ብሎ ከተቀላቀለው፣ ያለቀላቸው ኳሶችን assist በማረግ ከሚታወቀው፣ ጅምላ ጨራሹ አብዲ ኢሌና በቅርቡ የክለቡ አባል ከሚሆነው ጌታቸው አሰፋ መካከል ማንን አንበል ያረጉታል የሚለው ጉዳይ ለአሠልጣኙ ከወዲሁ ራስ ምታት ሆኗል፡፡
የቃሊቲ የዝውውር ራዳር በስኳር ኮርፖሬሽኑ አማካኝ ተጨዋች አባይ ፀሀዬ ላይም ያነጣጠረ ሲሆን፤ የክለቡ መልማዮች የተወልደ ገ/መድህንን አቋምን እየገመገሙ ይገኛሉ፡፡ ተወልደ በአየር ላይ ኳስ የመግጨት ኳሊቲው ለቃሊቲ እግር ኳስ ክለብ እንዲታጭ አብቅቶታል፡፡ የኢፈርቱ አንጋፋ ተከላካይ ስብሃት መሸም ካካበተው ልምድ አኳያ ለቃሊቲ እንዲታጭ የክለቡን ጥንካሬ የሚመኙ ተንታኞች እያሳሰቡ ናቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሡ ተጨዋቾች ባሻገር ጥረት ኮርፖሬትን ከለቀቁ በኃላ ክለብ አልባ የሆኑት በረከት ስምኦንና ታደሠ ካሣም ቃሊቲን እንዲቀላቀሉ የኳሱ ቤተሠብ ፍላጎቱን እያሳየ ነው፡፡ አንጋፋው በረከት አስመስሎ የመውደቅ ብቃቱን ተጠቅሞ ለክለቡ በርካታ የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሊያስገኝ እንደሚችል የዘገበችው ጋዜጠኛ ፍፁም የሽጥላ ነች – ከቃሊቲ!
Filed in: Amharic