>

ድምጻዊውንና ድራመሩን ጄነራል ሳስበው ሳስበው. . . !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ድምጻዊውንና ድራመሩን ጄነራል ሳስበው ሳስበው. . . !!!
አቻምየለህ ታምሩ
 
 «ባጫ ደበሌ እንኳን ከከበሮ መቺነትና ከተወዛዋዥነት ወደ  ጄኔራልነት መዛወርን ሊያቅማማ ወያኔ ካዘዘው ነጩን የሐኪም  ጋውን ለብሶ  ሐኪም ነኝ ከማለት  የማይመለስ    እንደሆነ ተጽፎ  ማንበቤን አስታውሳለሁ!!
«ጀኔራል» ባጫ ደበሌ  ከኦ.ኤም.ኤን. ጣቢያ ጋር  ዛሬ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ አደመጥሁት። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከየመጣው  ጋር ሰልፋቸውን የሚያስተካክሉ ሆድ አደሮች አንድ  ዘይቤ አለ። ከባለፈው አገዛዝ ጋር ከፊት ሆነው በዋና  አጋፋሪነት ሲሰሩ ኖረው  ያ ያገለግሉት የነበረው አገዛዝ በሌላ አገዛዝ  ሲተካ ከአዲሱ አገዛዝ ጋር አሰላለፋቸውን  አስተካክለው  «ባለፈው አገዛዝ ውስጥ የለሁበትም፤ አልነበርንበትም» በሚል  እስኪያልባቸው ያገለገሉትን  አገዛዝ ያወግዙታል።ባጫ ደበሌም ከነዚህ  አይነት ሰዎች የሚመደብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ባጫ ደበሌ ከአንድ አመት በፊት የአማራና የኦሮሞ ልጆች  በባዶ እጃቸው የወያኔን እስካፍንጫው የታጠቀ ጦር  ሲጋፈጡ  መሰረት አታላይ ከሚባል የወያኔ ቅልብ ጋዜጠኛ ጋር በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብሎ  በሰጠው ቃለ መጠይቅ  የወጣቶችን ትግል  አውግዞ «ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ እየተደረገ  ላለው ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ  የሚዳርግ አይደለም» ሲል ተናግሮ ነበር። ከአንድ አመት በፊት ይህንን ያለን ባጫ ዛሬ በኦ.ኤም.ኤን. ላይ ወጥቶ  መኖር ከጀመርሁ ስምንት ወር ሆነኝ አለን!  ባጫ ደበሌ ዛሬ ላይ መኖር ከጀመርሁ ስምንት ወር ሆነኝ   ቢለንም  እንዳይኖር  ያደረገውን  የወያኔ የጭካኔ አገዛዝ ግን  በሁለት እግሩ እንዲቆም ካደረጉት ታማኝ  የወያኔ ሎሌዎች መካከል ባጫ ደበሌ  በግንባር ቀደምትነት ከሚሰለፉት ካድሬዎች ዋነኛው ነው።
ባጫ ደበሌ  እውነተኛ እናቱ ያወጡለት  ስሙ አትንኩት ደበሌ  ነው። አተንኩት ደበሌ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በቅርበት ላይ በምትገኘው የቡራዩ ከተማ ሲሆን እድሜው  ለአቅመ ጉርምስና ሲደርስ  ወንበዴዎቹን ወያኔንና ሻዕብያን  ድባቅ ለመምታት በማሰብ የሰፈሩ  ልጆች  ከሆኑት ከሂቃ ቱፋ እና ታከለ ጂሩ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሰራዊት በዘመነ ደርግ ተቀላቀለ።
አትንኩት  ደበሌ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል በመሆን  የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ  ተገንጣዮችን ሊወጋ ወደ ጦር ግንባር ዘምቶ  ብዙም ሳይቆይ በሻዕብያ እጅ ወደቀ።  አተንኩት  በሻዕብያ ምርኮ  በነበረበት ከሌሎች አብረው  ለሻዕብያ  እጃቸውን ከሰጡ  የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት  ጋር በመሆን  ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ሰራዊት ለማጥቃት የሚጠቀምባቸውን  ምሽግ ቆፋሪ  ሆነ።   በዕረፍት ጊዜው ደግሞ  ሻዕብያ ለምርኮኞች ወታደሮች  የባህል ትርኢቶች  ሲያዘጋጅ  በድምጻዊነትና በተወዛዋዥነት ምርኮኞችን ያዝናና  ነበር።
ከአመታት የምርኮ ቆይታ  በኋላ  የኢሕዴኑ የመጀመሪያ  መሪ ያሬድ ጥብቡ አባዱላን፣ ባጫ ደበሌንና ሌሎች የሻዕብያ ምርኮኞችን ከሻዕብያ ምሽግ ቆፋሪነት አውጥቶ ወደ ኢሕዴን ፋኖነት እንዲዛወሩ በማድረጉ ሕይወታቸውን እስከመጨረሻው ድረስ ለወጠው። ከሻዕብያ ምርኮ ወጥቶ ኢሕዴንን  እንደተቀላቀለ  አተንኩት ደበሌ የኢሕዴን ኪነት ጃዝ መቺ ሆነ።  በሙዚቃው ዘርፍም  ከእነ በረከት ስምኦንና ሕላዌ ዮሴፍ  የሚመጣለትን መመሪያ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ሕዝቡ እንዲያምጽ ይቀሰቅስ ጀመር።
ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ክንፈ ገብረ መድኅንና መለስ ዜናዊ  ደራ ላይ  የኦሮሞ እንደራሴ የሚሆናቸውን ኦሕዴድን ሲመሰርቱ እናቱ  «አትንኩት» ሲሉ ያወጡለትን  ስሙን  ቀይረው «ባጫ» የሚል የእንጀራ ስም በማውጣት የኦሕዴድ መስራችና የሕወሓትና ሻዕብያ ዘመቻ  መንገድ መሪ አደረጉት።  ባጫ ኦሕዴድ እንደተደረገ  በቅድሚያ የዘመተው  ከመንደሩ አብረውት ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ  ግንባር የዘመቱት የጎረቤቶቹ  ልጆች ሂቃ ቱፋ እና ታከለ ጂሩ  ይገኙበት  ወደነበረው ከነቀምት ወጣ ብላ በምትገኘዋ ጽጌ  የተባለት ስፍራ መሸጎ ይዋጋ የነበረውን  የኢትዮጵያ ጦር  ለመውጋት  ሐዋዝ የሚባል የወያኔ ክፍለ ጦር መሪ የሚመራውን የወንበዴ ጦር መንገድ በመምራት ነበር።
ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገባ  ባጫ መንገድ ይመራው የነበረው የሻዕብያና የሕወሓት ጦርም  ከጽጌ ወደ ነቀምት ገብቶ  ወለጋን በመቆጣጠር  ኢሕዴን የሰጠውን ከበሮ መምቺያ እንጨቶችን ግራና ቀኝ ወርውሮ  በመለስና ክንፈ የኦሕዴድ መሥራችና የዘመቻ መሪ የተደረገውን  ባጫ  ደበሌን የወለጋ አስተዳዳሪ  ተደርጎ ተሾመ። ከወያኔ ትዕዛዝ እየተቀበለ ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ወገኖቹን የቻለውን ያህል ካንገላታና  የወያኔ ታማኝነቱን  በሚገባ ካረጋገጠ በኋላ ከአስተዳዳሪነት ወደ  ወያኔ ጄኔራልነት ዝውውር አደረገ። አንድ የኢሕዴን ጓዱ «ባጫ ደበሌ እንኳን ከከበሮ መቺነትና ከተወዛዋዥነት ወደ  ጄኔራልነት መዛወርን ሊያቅማማ ወያኔ ካዘዘው ነጩን የሐኪም  ጋውን ለብሶ  ሐኪም ነኝ ከማለት  የማይመለስ አይነት ሎሌ  እንደሆነ ጽፎ  ማንበቤን አስታውሳለሁ።
ባጫ ደበሌ ከኦ.ኤም.ኤን. ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቁ ሞያው ጄኔራልነት  እንደሆነ፤ የተፈጠረውም ለወታደርነት እንደሆነ ሲናገር ሰማሁት። ድፍረቱን አደነቅሁለት። ባጫ ደበሌ ከአስተዳዳሪነት ተነስቶ ጄኔራልነት ተሰጥቶት የምስራቅ እዝ አዛዥ  ተደርጎ የተሾመው   የወታደርነት ሞያ ኖሮት ዳር ድንበር እንዲጠብቅ ሳይሆን የሕወሓትን የምስራቅ ኢትዮጵያ የንግድ መስመር የሚጠብቅ በሕወሓት ታማኝነቱ የማይጠረጠው  ኦሮሞ ሆኖ ስለተገኘ ነው። ባጫ ጀኔራል ተደርጎ በተሾመ ሰሞን በሕወሓት ታማኝነቱ የማይጠረጠር ኃይሌ ጥላሁን የሚባል  ሆዳም አማራም ጀኔርል  ተደርጎ ተሹሞ ነበር። ባጫ  በጄኔራልነት ማዕረግ የተሾመበትን የሕወሓት አገልግሎት እንዲሰጥ  ሲባልም     የአዜብ መስፍን  የምስራቅ ኢትዮጵያ  የንግድ መስመር እንዲጠብቅ ታስቦ  የድሬዳዋ እና የሐረር ተቋማት ኃላፊም  ሆኖ ተደርጎ ተሹሞ ነበር።  በዚህ ኃላፊነቱ ባጫ በርካታ ንብረት በሕገወጥ መንገድ  ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸምና በማስፈጸም በመለስ እና በቤተሰቡ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ሊያገኝ ችሏል።
ባጫ ሞያ ነበረው ከተባለ ተወዛዋዥነት፣ ዳንስ፣ የሙዚቃ መሳሪያ መጫዎትና ድምጻዊነት ነው። ባጫ የሕወሓት  አለቆቹን ተፈጥሮ በለገሰችው የዳንስ ችሎታው ያዝናና የነበረ መሆኑን  በአንድ ወቅት  አንዱ የወያኔ ባለሥልጣን ባሳተመው  መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።
በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት አሰብን ለመቆጣጠር ይገሰግስ የነበረውን የኢትዮጵያ የቀድሞ ተመላሽ  ሰራዊት ከመለስ ዜናዊ በተላለፈ ትእዛዝ ግስጋሴው እንዲገታና ወታደራዊ እቅዱ እንዲኮላሽ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው  ባጫ ደበሌ ነበር።  ባጫ  ደበሌ እንዲህ  ዛሬ የለሁበትም እንደሚለው ሳይሆን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እጁን ሰተት አድርጎ ወደ ሙስና ውስጥ  ሲያስገባ የነበረ «ዲንሾ ኦሮሚያ»  ከሚባለው ተቋም  በርካታ ሚሊዮናትን የዘረፈ እንደሆነ ባንድ ወቅት ወያኔ የከዳው የኦሕዴድ አባል ተናግሮ ነበር።
በከፍተኛ ሙስና ወንጀም ውስጥ ከተዘፈቁ የወያኔ  ጄኔራሎች መካከል አንዱ የሆነው ባጫ ደበሌ በቦሌ ከለንደን ካፌ ፊት ለፊት  የተንጣላለ  ዘመናዊ  ቤት  ገንብቶ  እንደሚያከራይ  ይታወቃል። በአሜሪካን አገር  ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ  በረብጣ ዶላር ቤት መግዛቱን፤ ባለቤትና አንድ ልጁም በቤቱ  እንደሚኖሩበት፤ ልጁን  እንደ ወያኔ ባለሥልጣናት በሴሚስተር  በርካታ ሺሕ  ዶላሮች  በላይ እየተከፈለ  እንደሚያስተምር ከአመታት በፊት ተጋልጦ እንደነበር አስታውሳለሁ። ባጫ ከሰራዊቱ የተባረረው  ለወያኔ የሚሰጠውን አገልግሎት ስለጨረሰ እንጂ እሱ እንደሚለው የወያኔን የማፍያ ቡድን ስለተጋፈጠ አይደለም። ባጫ ከወያኔ የተባረረው ከሙስና ንጹህ ሁኖ  የማፍያ ቡድንን  ስለተጋፈጠ ቢሆን ኖሮ እንደተባረረ  «ታየር ፕሮቴክተር»  የሚባል   ባለ ብዙ ሚሊዮን ካፒታል የግል ድርጅት አቋቁሞ  የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ  ባልሆነ ነበር።
ባጫ «የማፍያ  ቡድን አባላት»  ስላላቸው የሜቴክ አመራሮች የልቡን ሲናጋር  ነበር። የሚያውቀው እውነት ካለው መናገሩ ባልከፋ ነበር።  ሆኖም ግን  የዘረፋዋ አጋር አድርጋውና  ዝርፊያዋ ችግር  እንዳያጋጥመው  በመከላከያ ሰራዊት  እንዲጠበቅላት ዘበኛዋ  አድርጋ ለብዙ አመታት ኢትዮጵያን ስትገፍ ስለኖረችው ስለ ዘረፋዋ  እመቤት ስለ አዜብ መስፍን  አንድም ቃል ሳይተነፍስ  ቃለ መጠይቁን ጨረሰው። ጋዜጠኛውን ስለሱና ስለ አዜብ ግንኙነት አልጠየቀውም። ባጫ ስለ አዜብ መስፍን የዘረፋ እመቤትነት ቃል ሳይተነፍስ የወረደው ስለማያውቅ ነውን? በጭራሽ ሊሆን አይችልም! የተቋሙ አካል ሳይሆን ስለ ሜቴክ ዘረፋና ስለ ማፍያ ቡድኑ  የአገር ጠላትነት ያን ያህል በርቀት  ሲመሰክር፤ በዋናነት አብራው ስለሰራችው፣  ስለ ቅርብ አለቃውና  ከሜቴክ  በማይተናነስ ኢትዮጵያን ስለዘረፈችው  ስለ አዜብ መስፍን ዘረፋ ቃል ሳይተነስፍ የወረደው ስለማያውቅ ሊሆን አይችልም!  አባቶቻችን  ሲተርቱ «ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም» ይላሉ። ፈስ ያለበት  ዝላዬን ተከትሎ ምን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ በዝላይ አይሳተፍም፤ ዝላይም አይወድም። ባጫም እንደዚያው ነው።
ከታች የታተመው  ዘፋኝ  እናቱ ባወጡለት ስሙ  የሚታወቀው አትንኩት  ደበሌ ወይንም በወያኔ ስሙ ባጫ ደበሌ ነው። ባጫ ይህንን ዘፈን የዘፈነው  ኤርትራ በረሀ ውስጥ የሻዕብያ ምርኮ በነበረበት ወቅት ነው። ያኔ አዲስ አበባን  እንደዛሬው  በፊንፊኔነት የሚያውቃት  ሰው ስላልነበረ   አዲስ አበባ አንፍጫ  ቡራዩ  ውስጥ የተወለደው  ባጫ ደበሌ  እንኳ  አዲስ  አበባን «ሸገር ናፍቀሽኛል፤ ከታጋኖች ጋር [ምርኮ የያዙት ድል አድርገው] መጥቼ እስካይሽ  ድረስ ናፍቀሽኛል» እያለ ነበር የዘፈነው። ይህ የባጫ ደበሌ ዘፈን ከሰበሰብናቸው ታሪካዊ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ምስል ክምችት ላይበራሪያችን የተገኘ ነው።
Filed in: Amharic